የዩክሬን እህል ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ የሚፈቅደው ሥምምነት በማብቃቱ ማን ይጎዳል?
ረቡዕ፣ ሐምሌ 12 2015
ለኢትዮጵያ 20 ሜትሪክ ቶን የሱፍ አበባ ዘይት የጫነችው “ሩቢቲ” የተባለች መርከብ ዛሬ ከጅቡቲ ወደብ ትደርሳለች ተብሎ ይጠበቃል። የማልታን ሰንደቅ የምታውለበልበው መርከብ በዩክሬን ኦዴሳ ግዛት ከሚገኘው የቼርኖሞርስክ ወደብ የተነሳችው ባለፈው ሰኔ 25 ቀን 2015 ነበር። የመርከቧ ጉዞ ሩሲያ እና ዩክሬን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ቱርኪዬ አሸማጋይነት የፈረሙት ሥምምነት አካል ነው።
በሥምምነቱ መሠረት ለኢትዮጵያ ከዩክሬን ወደቦች ስንዴ የጫነች የመጀመሪያዋ መርከብ “ብሬቭ ኮማንደር” የተባለች ናት። መርከቧ የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር (WFP) በኢትዮጵያ የተራቡ ዜጎችን ለመርዳት ከዩክሬን የሸመተውን 23 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ከኦዴሳ አጠገብ ከሚገኘው ወደብ ጭና ጉዞ የጀመረችው ነሐሴ 10 ቀን 2014 ነው።
ብሬቭ ኮማንደርን ጨምሮ ባለፈው አንድ አመት ገደማ የዓለም የምግብ መርሐ ግብር አስር መርከቦች ለኢትዮጵያ ከዩክሬን ወደቦች ስንዴ ጭነዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር የሚገኘው የሥምምነቱ ማስተባበሪያ ጥምር ማዕከል መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ 263 ቶን ስንዴ እና 20 ቶን የሱፍ አበባ ዘይት ከዩክሬን ደርሷታል።
ከሥምምነቱ ማን ተጠቀመ?
የዩክሬን የእህል ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ይፈቅድ የነበረው ሥምምነት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በቱርክዬ አደራዳሪነት የተፈረመው በሐምሌ 2014 ነው። በእርግጥ ብርቱ ጦርነት ውስጥ የሚገኙት የሩሲያ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት ፊት ለፊት ተገናኝተው አንድ ሰነድ አልተፈራረሙም። ሁለቱም አንድ አይነት ሰነድ ነገር ግን በተናጠል ሥምምነቱን ከቱርክዬ ጋር ሲፈራረሙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በውሉ ግርጌ በታዛቢነት ፊርማቸውን አኑረዋል።
በዚህ ሥምምነት መሠረት 32.9 ሚሊዮን ቶን የምግብ እህል ከዩክሬን የእህል ጎተራዎች ለዓለም ገበያ ቀርቧል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት በሥምምነቱ ለዓለም ገበያ ከቀረበው የዩክሬን የእህል ምርት 47 በመቶው ስፔን፣ ጣልያን እና ኔዘርላንድስን በመሳሰሉ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ገበያ የተሸጠ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሱዳን ያሉ “ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት” በአንጻሩ ዩክሬን በሥምምነቱ ለዓለም ገበያ ካቀረበችው እህል 27 በመቶው ደርሷቸዋል። የተቀረው 26 በመቶ ቻይና እና ቱርክዬን ለመሰሉ “ከፍተኛ መካከለኛ ገቢ ላላቸው አገራት” ገበያ ቀርቧል። በቆሎ፣ ስንዴ እና ከሱፍ አበባ የተዘጋጀ ዘይት እና ምግቦች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።
ሥምምነቱ ባለፈው ሰኞ ሲያበቃ ዳፋው ይበረታባቸዋል ከተባሉ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ኬንያ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ኢንተርናሽናል ረስኪዩ ኮሚቴ የተባለው የግብረ ሰናይ ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሻሽዋት ሳራፍ “ሥምምነቱ በመኖሩ፣ የዓለም የምግብ ገበያ በሚሊዮኖች ቶን የሚገመት የምግብ እህል ከዩክሬን እንደሚቀርብ ያውቃል። በዓለም አቀፍ የምግብ ገበያዎች ከሚፈጥረው መረጋጋት አንጻር አሁንም ተጽዕኖ አለው” የሚል አቋም አላቸው።
“ሥምምነቱ ባለመራዘሙ የሚፈጠረው አለመረጋጋት አጠቃላይ የምግብ ገበያዎች ጠባይ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል” የሚሉት ሻሽዋት ሳራፍ ዳፋው ሊበረታባቸው ይችላል ብለው ከሚጠቅሷቸው አገሮች መካከል አፍጋኒስታን፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን ይገኙበታል።
ክርስቲያን ኤይድ የተባለው የግብረ ሰናይ ድርጅት አማካሪ ሊዲያ ምቦጎሮ የሩሲያ ውሳኔ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሀ አገራት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ይስማማሉ። “ሩሲያ ከሥምምነቱ በመውጣቷ በገበያው አለመረጋጋት ሊፈጠር እና ዋጋ ሊንር ይችላል። በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለው ቀውስ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ የእህል ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሲጨምር ተመልክተናል። ሁላችንም የኑሮ ውድነት ቀውስ፣ የዋጋ ንረት፣ ከፍተኛ የምግብ እና የነዳጅ ዋጋ አጋጥሞናል” የሚሉት ሊዲያ ምቦጎሮ ተመሳሳይ ሁኔታ በዓለም ገበያ ሊፈጠር ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው።
እንዲህ አይነቱ ሥጋት ሩሲያ እና ዩክሬን በዓለም የበቆሎ እና የስንዴ ገበያ ካላቸው ከፍተኛ ድርሻ የሚመነጭ ነው። በሁለቱ አገራት መካከል በመካሔድ ላይ የሚገኘው ጦርነት በዓለም የእህል ገበያ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ቱርክዬ አሸማጋይነት የተፈረመው ሥምምነት በጦርነቱ የተስተጓጎለው የስንዴ፣ የአበባ ዘይት እና ማዳበሪያ ምርት ወደ ዓለም ገበያ እንዲቀርብ በማመቻቸት ሊፈጠር የሚችል ብርቱ ረሐብ ለመግታት ያለመ ነበር።
ሩሲያ ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታ ሥምምነቱ ሲፈርስ በዓለም የእህል ገበያ የዋጋ ለውጥ እንደታየ በኔዘርላንድስ የሚገኘው ራቦ ባንክ የግብርና ምርቶች ግብይት ጥናት ቡድን መሪ ካርሎስ ሜራ ታዝበዋል። “የስንዴ ዋጋ 10 በመቶ ጨምሯል። ውሳኔው የበቆሎ የመሸጫ ዋጋ ላይም ተጽዕኖ አለው። የበቆሎ ዋጋ በአምስት እና ስድስት በመቶ ከፍ ብሏል” ሲሉ የሩሲያ ውሳኔ ከተሰማ በኋላ በገበያው የታየውን የዋጋ ለውጥ ይዘረዝራሉ።
ሩሲያ ከሥምምነቱ የወጣችው “የምግብ ዋስትና እጦት ባየለበት ጊዜ” እንደሆነ የጠቀሱት ካርሎስ ሜራ “በተለይ በርካታ ደሀ አገሮች ከዕዳ ጫና ጋር እየታገሉ ነው። ስለዚህ ወደፊት የምግብ ዋስትና እጦት የበለጠ አሳሳቢ እንደሚሆን እንጠብቃለን” ሲሉ ተናግረዋል።
የዚህ ሥምምነት ዋንኛ ዓላማ ኦዴሳ እና ቼርኖሞርስክን ጨምሮ ከዩክሬን ሦስት ወደቦች እህል፣ ተያያዥ የምግብ ግብዓቶች እና አሞኒያን ጨምሮ ማዳበሪያ ለሚጭኑ መርከቦች የባሕር ላይ ጉዞ “የደህንነት ዋስትና ማመቻቸት” ነው። የውሉ ፈራሚዎች በንግድ መርከቦች እና በወደቦች ላይ ጥቃት ባለመፈጸም “ከፍተኛ ማስተማመኛ” ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
የሥምምነቱን አተገባበር መርከቦችን ከቱርኪዬ የባህር ወሽመጥ ሲወጡ እና ሲገቡ እየፈተሸ የጦር መሣሪያን ጨምሮ “ያልተፈቀደ ጭነት እና ሠራተኛ” መኖር አለመኖሩን እንዲቆጣጠር መቀመጫውን በኢስታንቡል ያደረገ ጥምር የማስተባበሪያ ማዕከል ተቋቁሟል።
ሥምምነቱ ለምን ተቋረጠ?
ሐምሌ 15 ቀን 2015 የተፈረመው ሥምምነት ለ120 ቀናት የሚጸና ቢሆንም ባለፈው ባለፈው ሚያዝያ ለአጭር ጊዜ እንዲራዘም ሆኗል። በሥምምነቱ አተገባበር ደስተኛ ያልሆነችው ሩሲያ በተደጋጋሚ አቋርጣ ለመውጣት ስትዝት ቆይታለች። ባለፈው ሰኞ ግን የውሉ ጸንቶ የሚቆይበት ጊዜ ማብቃቱን የሩሲያ ፕሬዝደንት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ዲሚትሪ ፔስኮቭ “የጥቁር ባሕር ሥምምነት ጸንቆ የሚቆየው እስከ ዛሬ ነበር። የሩሲያ ፕሬዝደንት ቀደም ሲል እንዳሉት ሥምምነቱ የተፈረመው እስከ ሐምሌ 17 ነው። እንዳለመታደል ሆኖ በጥቁር ባሕር ሥምምነት ሩሲያን የተመለከቱት ጉዳዮች እስካሁን አልተተገበሩም። ስለዚህ ሥምምነቱ ተቋርጧል” ብለዋል።
ፔስኮቭ የአገራቸው ጥያቄ ምላሽ ሲያገኝ “ሩሲያ በአፋጣኝ ወደ ሥምምነቱ አተገባበር እንደምትመለስ” ተናግረዋል። የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው አገሪቱ ወደ ውሉ ልትመለስ የምትችለው “በተስፋ እና ማረጋገጫ” ሳይሆን “በተጨባጭ ውጤቶች” ብቻ ነው።
ይኸ እርምጃ ሥምምነቱ እንዲፈረም ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቱሬዝ “በጥልቅ የሚያሳዝን” ነበር። “በዚህ ሥምምነት መካፈል ምርጫ ነው። ነገር ግን በየቦታው ከኑሮ ጋር የሚታገሉ ሰዎች እና በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች ምርጫ የላቸውም” ሲሉ ዳፋው ማን ላይ እንደሚበረታ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጠቆም አድርገዋል።
ዋና ጸሐፊው “በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ረሐብ ሲገጥማቸው ሸማቾች ከዓለም አቀፍ የኑሮ ውድነት ቀውስን ተጋፍጠዋል። እነርሱ ዋጋ ይከፍላሉ። ገና ከዛሬው የስንዴ ዋጋ ሲጨምር ተመልክተናል” በማለት የሩሲያ ውሳኔ በዓለም ገበያ ተጽዕኖ ማሳደር እንደጀመረ ገልጸዋል።
የሩሲያ ጥያቄዎች ምንድናቸው?
ሩሲያ ለወራት ሥምምነቱ እንዲራዘም የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች አለመሟላታቸውን ስትገልጽ ቆይታለች። ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በሩሲያ የግብርና ባንክ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ እንደሚሹ ከሣምንት በፊት ተናግረው ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንዳሉት የሩሲያ የግብርና ባንክ ስዊፍት ከተባለው ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት ውጪ ሆኖ መቆየቱ የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ካበቁት ምክንያቶች ዋንኛው ነው። የሩሲያ ጥያቄ ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም።
ሩሲያ የግብርና ማሽኖች፣ መለዋወጫዎች አቅርቦት እና የመድን ዋስትና ዳግም መጀመር አለባቸው የሚል አቋም አላት። የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መንግሥት ምግብ እና የአፈር ማዳበሪያ በዓለም ገበያ የሚሸጡ የሩሲያ ኩባንያዎች በማዕቀብ ሳቢያ ከማይንቀሳቀስ የታገዱት ጥሪት እንዲለቀቅ ይፈልጋል። ከቶግሊያቲ እስከ ኦዴሳ የተዘረጋውን የአሞንያ ማስተላለፊያ ቧንቧ መልሶ ሥራ ማስጀመር ሌላ ቅድመ-ሁኔታ ነው።
የዩክሬን ወደቦች ይኸ ሥምምነት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር እስኪፈረም ድረስ ዝግ ሆነው ቆይተዋል። ሩሲያ ወደ ሥምምነቱ ካልተመለሰች አሁንም ወደቦቹ ስንዴ እና በቆሎ መጫን ለመጀመራቸው ማረጋገጫ የለም። የተርኪዬ ፕሬዝደንት ረቺብ ጣይብ ኤርዶኻን ግን የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ሥምምነቱ እንዲቀጥል ፍላጎት አላቸው ሲሉ ተናግረዋል።
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር