1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችአውሮጳ

የዩክሬን ጦርነትን ለማቆም የተዘጋጀው አወዛጋቢ ምክረ ሐሳብ ምን ይዟል?

እሑድ፣ ኅዳር 14 2018

በዩክሬን በመካሔድ ላይ የሚገኘውን ጦርነት ለማቆም በቀረበ ምክረ ሐሳብ ላይ ለመወያየት የአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ብሪታኒያ ባለሥልጣናት ዛሬ እሁድ በጄኔቫ ተገናኝተዋል። ምክረ ሐሳቡ ወደ ሩሲያ ያደላ ነው ቢባልም ለፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መንግሥት ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ ጉዳዮችንም ያካተተ ነው።

የዩክሬን ወታደር በጦር ግምባር ቀለህ ሲያዘገጃጅ ይታያል።
በዩክሬን በመካሔድ ላይ የሚገኘውን ጦርነት ለማቆም በቀረበ ምክረ ሐሳብ ላይ ለመወያየት የአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ብሪታኒያ መሪዎች ዛሬ እሁድ በጄኔቫ ተገናኝተዋል።ምስል፦ REUTERS

የአሜሪካ ሴናተሮች በዩክሬን የሚካሔደውን ጦርነት ለማቆም የቀረበው የሰላም ምክረ ሐሳብ የሩሲያ “ምኞት” መሆኑን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እንደነገሯቸው ገለጹ። በካዳና ሐሊፋክስ ዓለም አቀፍ የጸጥታ ፎረም ከአሜሪካ ሪፐብሊካን እና ዴሞክራት ፓርቲ የተውጣጡ ሕግ አውጪዎች 28 ነጥቦች የያዘው ምክረ ሐሳብ የሩሲያን ወረራ የሚሸልም እንደሆነ ተችተዋል።

አሜሪካ የምክረ ሐሳቡ ተቀባይ ብቻ እንደሆነች ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እንደነገሯቸው ሴናተሮቹ ገልጸዋል። “ይህ የሩሲያ ምክረ ሐሳብ ነው” ያሉት ዴሞክራቷ ሴናተር ጂን ሻሒን “ፈጽሞ ተቀባይነት የሌላቸው ብዙ ነገሮች” በውስጡ እንደያዘ ተናግረዋል።

ምክረ ሐሳቡ አሁን ባለው መልክ በመሠራጨቱ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኃላፊነት እንደሌለበት የገለጹት ማይክ ራውንድስ የተባሉ የሪፐብሊካን ፓርቲ ሴናተር በኩላቸው ባለሥልጣናት “እንደ መነሻ” ሊጠቀሙበት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ግን በዶናልድ ትራምፕ የተደገፈው “የሰላም ምክረ ሐሳብ በዩናይትድ ስቴትስ የተዘጋጀ ነው” በማለት የሴናተሮቹን ሐሳብ አጣጥለዋል።

“በመካሔድ ላይ ለሚገኙ ድርድሮች ጠንካራ ማዕቀፍ ያቀርባል። ከሩሲያ ወገን በተገኘ ግብዓት ላይ የተመሰረተ ነው” ያሉት ሩቢዮ በኤክስ በኩል ባሰራጩት ማብራሪያ “ነገር ግን ከዩክሬን ወገን ቀደም ብሎ እና በመካሔድ ላይ ባሉ ውይይቶች የተገኙ ግብዓቶች ላይ የተመሠረተ” እንደሆነ ገልጸዋል። 

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ በምክረ ሐሳቡ ላይ ከዩክሬን እና ከአውሮፓ ሹማምንት ለመወያየት ዛሬ እሁድ ጄኔቫ ገብተዋል። ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም በዩክሬን የሚካሔደውን ጦርነት ለማብቃት የተዘጋጀውን ምክረ ሐሳብ ዩናይትድ ስቴትስ እንድትከልስ ግፊት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ምክረ ሐሳቡ ወደ ሩሲያ ያደላ ነው ቢባልም ለፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መንግሥት ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ ጉዳዮችንም ያካተተ ነው።  

ምክረ ሐሳቡ ለዩክሬን ሉዓላዊነት ማረጋገጫ የሚሰጥ ቢሆንም ክሬሚያ፣ ሉሐንስክ እና ዶኔትስክ ግዛቶችን ለሩሲያ አሳልፎ ይሰጣል። ምክረ ሐሳቡ በእነዚህ ግዛቶች ዩክሬን ከምትቆጣጠራቸው አካባቢዎች ለቃ እንድትወጣ የሚያደርግ ሐሳብ የያዘ ነው።

በኼርሶን እና ዛፖሬዥያ ግዛቶች የሚገኙ ድንበሮች አሁን ውጊያ በሚደረግባቸው የጦር ግምባሮች እንዲቆይ ተደርጎ በሁለቱ ሀገራት መካከል ወታደራዊ እንቅስቃሴ የማይደረግበት ዞን ይሆናል። 

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ በዩክሬን የሚካሔደውን ጦርነት ለማብቃት በቀረበ ምክረ ሐሳብ ላይ ለመወያየት ጄኔቫ ገብተዋል። ምስል፦ Valentin Flauraud/AFP

ሩሲያ ከአምስቱ ግዛቶች ውጪ የተቆጣጠረቻቸውን አካባቢዎች እንደምትለቅ በምክረ ሐሳቡ ተካቷል። ይህ በሱሚ እና ኻርካይቭ ግዛቶች የሚገኙ አካባቢዎችን ይመለከታል ተብሎ የሚገመት ቢሆንም ዝርዝር ጉዳዮች አልቀረቡበትም። 

የሩሲያ ወታደሮች የተወሰኑ የኻርካይቭ እና ድኒፕሮፔትሮቭስክ አካባቢዎችን መልቀቅ ይኖርባቸዋል። የዛፖሬዥያ የኑክሌር ጣቢያ መልሶ ሥራ የሚጀምር ሲሆን የሚያመነጨውን ኃይል ሩሲያ እና ዩክሬን ዕኩል ይካፈላሉ። 

ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (NATO) ለመቀላቀል ያላትን ፍላጎት እርግፍ አድርጋ እንድትተው ምክረ ሐሳቡ ይጠይቃል። ኔቶ ወታደሮቹን በዩክሬን ማስፈር የሚከለከል ሲሆን ወደፊት ላለመስፋፋት ቃል መግባት ይኖርበታል። 

ምክረ ሐሳቡ የዩክሬን ወታደሮች ቁጥር በ600,000 እንዲገደብ የሚያደርግ ነው። ከዚህ ቀደም ሩሲያ የዩክሬን ወታደሮች ቁጥር 100,000 እንዲሆን ሐሳብ አቅርባ ነበር። 

ዩክሬን ሩሲያ በምታካሒደው ወረራ የጦር ወንጀል እንደፈጸመች ለማረጋገጥ የሚሞክሩ ማናቸውም የሕግ ሒደቶችን ማቋረጥ ይኖርባታል። የዩክሬን ስም ባይጠቀስም “ሁሉም የናዚ ርዕዮተ ዓለሞች ውድቅ እንዲደረጉ ወይም እንዲከለከሉ” የሚያደርግ አንቀጽ በምክረ ሐሳቡ ተካቷል። 

ሩሲያ በምዕራባውያን መንግሥታት እንዳይንቀሳቀስ ማዕቀብ ከተጣለበት ጥሪቷ ውስጥ 100 ቢሊዮን ዶላር ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት ኢንቨስት እንዲደረግ መስማማት አለባት። ዩክሬንም ሆነች ሩሲያ እንዳይንቀሳቀስ የተደረገውን ጥሪት ለመጠቀም ሙሉ ቁጥጥር አይኖራቸውም። ከዚህ በተጨማሪ ዩክሬን በጦርነቱ ምክንያት ለደረሰባት ጉዳት ካሳ መጠየቅ አትችልም። 

በምክረ ሐሳቡ ዩክሬን በ100 ቀናት ውስጥ ምርጫ እንድታካሒድ ትገደዳለች። 

አርታዒ ልደት አበበ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW