1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የዩክሬን ጦርነት በአፍሪካ ያስከተለው የምግብ እጥረት እና የሱዳን ዳርፉር ግጭት

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 22 2014

በዩክሬን የሚካሄደው ጦርነት በሺ በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ሊርቅ ይችላል ነገር ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት ተፅዕኖው ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞም በአፍሪካ የምግብ ዋጋ መናር፣ ድህነትን እና ረሃብንና እያስከተለ ነው። የእርዳታ ድርጅቶችም ለችግረኞች የሚያቀርቡትን ምግብ በግማሽ እንዲቀንሱ እያስገደዳቸው ነው።

Äthiopien Addis Abeba | Svenja Schulze trifft Monique Nsanzabaganw
ምስል፦ Thomas Koehler/photothek/IMAGO

ትኩረት በአፍሪቃ

This browser does not support the audio element.


በዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅት የዩክሬን ጦርነት ያስከተለው የምግብ ዋጋ መናርና ረሀብ  በአፍሪቃ እንዲሁም በሱዳን ዳርፉር እንደ አዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት ላይ ያተኩራል።አብራችሁን ቆዩ።
በዩክሬን የሚካሄደው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ሊርቅ ይችላል ነገር ግን  ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት ተፅዕኖው ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞም በአፍሪካ  የምግብ ዋጋ መናር፣  ድህነትን እና ረሃብንና እያስከተለ ነው። የእርዳታ ድርጅቶችም ለችግረኞች የሚያቀርቡትን ምግብ በግማሽ እንዲቀንሱ እያስገደዳቸው ነው።
የዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትና  ትብብርን ለማጠናከር  በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋ ጋር የተወያዩት የጀርመን የልማት ሚኒስትር ስቬንያ ሹልዝ እንደሚሉት  በመቶኛ በሚሰላ በእያንዳንዱ የምግብ ዋጋ ጭማሪ  በዓለም ላይ ቢያንስ 10 ሚሊዮን ተጨማሪ ሰዎችን ለድህነት እና ለረሃብ ይዳርጋቸዋል።ለወትሮውም የምግብ ዋስትና አስተማማኝ ባልሆነባት አፍሪቃ የዩክሬን ጦርነት ሁኔታውን እንዲባባስ አድርጎታል።የጀርመን የልማት ሚንስቴር ስቬኒያ ሾልዝ ይህንን ያረጋግጣሉ።
«አፍሪካ ውስጥ የሩሲያ  ጦርነት ያስከተለው ተፅዕኖ ተጨባጭ እና በእጅጉ የሚያጎዳ ነው።የምግብ እና የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ፤ አሁን ያለውን የረሃብ ቀውስ ያባብሰዋል።»
ሹልዝ የተጓዙት በርካታ አደጋዎች ወደ ተጋረጡባት ሀገር ኢትዮጵያ ነው። የ COVID-19 ወረርሽኝ ፣ከዚህ በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥ የተለመደውን የዝናብ ወቅት በጣም አጭር በማድረግ ወይም ከነ አካቴው በማስተጓጎል ባለፉት አሥርተ ዓመታት እጅግ የከፋ ድርቅ እያጋጠማት ነው። በዚህ የተነሳ በሀገሪቱ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት መሬቱ ሁሉንም ውሃ መሳብ ስለማይችል አውዳሚ ጎርፍ በፍጥነት ሊመጣም ይችላል። ከዚህም በላይ በቅርቡ የተከሰተው የአንበጣ ወረርሽኝ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰብሎችን አውድሟል።
«ቬልትሁንጋሂልፈ» የተባለው የጀርመኑ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት  የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ማቲያስ ስፓት እንደሚሉት እነዚህ ቀውሶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ እና ውስብስብ እየሆኑ መጥተዋል። 
ማቲያስ ስፓት አያይዘውም በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ደም አፋሳሽ ግጭት ደግሞ ሀገሪቱን የበለጠ እያዳከመ ነው። ከ112 ሚሊዮን ህዝብ ባለት ኢትዮጵያ ቀድሞውንም 25 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ያልቻሉ እና በእርዳታ ላይ ጥገኛ ናቸው።የሚሉት ሀላፊው የዩክሬን እና የሩስያ ጦርነት ደግሞ በሀገሪቱ እና በአካባቢው ያለውን የምግብ እጥረት የበለጠ እያባባሰው ነው።በዚህ የተነሳ የረዴት ድርጅቶች እንኳ ምግብ ለማቅረብ ተቸግረዋል ይላሉ።
«በአሁኑ ጊዜ  በየቦታው የሀብት እጥረት እያጋጠመ  መጥቷል። በኢትዮጵያ የዓለም የምግብ እርዳታ ድርጅት በተለምዶ የገንዘቡን 80 በመቶ  ለረጅም ጊዜ  መርሃ ግብሮች ሲያውል፤ ቀሪውን 20 በመቶ ደግሞ  ለፈጣን የአደጋ ጊዜ እፎይታ ያውል ነበር። ነገር ግን ያ አሁን በሚገርም ሁኔታ እየተቀየረ ነው። ወደ 50:50 በመቶ ጥምርታ እየተቃረብን ነው።»
በኢትዮጵያ በከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ላለባቸው ህጻናት ምግብ የሚያቀርበው የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ)ም ተመሳሳይ ችግር ገጥሞታል። በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ምክትል ዳይሬክተር ሚሼል ሰርቫዴይ  እንደሚሉት የምግብ ዋጋ ባለፉት ሶስት ወራት ከ10 እስከ 15 በመቶ ጨምሯል። ይህም በድርጅቱ በጀት  ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልፀዋል።ያ በመሆኑ ተጨማሪ  የገንዘብ ድጋፍ ካልተገኜ የእርዳታ አቅርቦቱን ቁጥር በእጅጉ መቀነስ አለብን ብለዋል።
ሚኒስትሯ  አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት ለምግብ ዋስትና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን በሚያበረታታው ጉብኝታቸው ከአፍሪቃ ህብረት ተወካዮች ጋር  ባደረጉት ውይይት በአፍሪቃ የምግብ ዋጋ መጨመር አሳሳቢነቱ ከፍተኛ መሆኑን መረዳታቸውን ገልፀዋል።በአፍሪቃ ብዙ ሀገራት ድጎማ በሚደረግ የዳቦ ዋጋ ላይ ጥገኛ ናቸው።ነገር ግን በርካታ ሀገራት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የብድር ዕዳ  ስላላቸው ፖሊሲው ገደብ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
ሹልዝ እንደሚሉት ዳቦ ለብዙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ካልሆነ፣በሀገራቱ  ተቃውሞን እና  አለመረጋጋትን ይጥፈራል። 
ይህንን ችግር ለመቋቋም የአፍሪቃ የረዥም ጊዜ ዓላማ በሀገር ውስጥ ለአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚ የሆኑ ሰብሎችን ማምረት ነው።
ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በአዲስ አበባ መሀል በሚገኘው የዓለም ባንክ የከተማ አትክልት ልማት መርሀ ግብር አንዱ ነው።ይህ መርሀ ግብር በርካታ ሴቶችን እና ወጣቶችን ቀጥሮ በማሰልጠን እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን እንዲረዱ አድርጓል።
አዲስ ግጥት በዳርፉር ግዛት 
በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር ግዛት በተቀሰቀሰው አዲስ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን እና መቆሰላቸውን የሱዳን ሀኪሞች ማዕከላዊ ኮሚቴ ያለፈው ረቡዕ አስታውቋል። የፌደራል መንግስት ሁለቱን ወገኖች ለመለያየት ተጨማሪ ጦር ልኳል። ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን የተባለው የህክምና ዕርዳታ ድርጅት በቅርብ ጊዜ በተፈፀመው ጥቃት የሶስት ሰራተኞቹ መገደላቸውን አስታውቋል። በአል ገኒና ከተማ የአይን እማኝ ለDW እንደተናገሩት በከተማው የሚገኘው ዋና ሪፈራል ሆስፒታል በግጭቱ ምክንያት ተዘግቷል። ብዙ ተፈናቃዮች ሜዳ ላይ እየተጠለሉ ነው። 
ግጭቱ  የተቀሰቀሰው ባለፈው ሳምንት የተገደሉት የሁለት የአረብ ዝርያ ያላቸው አርብቶ አደሮች  አስከሬን መገኘቱን ተከትሎ መሆኑን በከረኒክ አካባቢ ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። በአርብቶ አደሮች የተወሰደው የበቀል እርምጃ ከ200 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ኤምኤስኤፍ የተባለው የህክምና ዕርዳታ ድርጅት አስታውቋል።
የአረብ አርብቶ አደሮች የቆሰሉ ባልደረቦቻቸውን በከተማው ሆስፒታል እንዲታከሙ ሲወስዱ ደግሞ ጦርነቱ ወደ ዋና ከተማው አልጄና ተዛመተ። የሆስፒታሉ ባልደረባ ዶክተር አደም ዘካሪያስ እንደሚሉት ታጣቂዎቹ በጤና ሰራተኞች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን እና የቆሰሉ ጓድኞቻቸውን  ለማሳከም በጦር መሳሪያ  አስፈራርተዋቸቸው ነበር ።
«በአል ጀኔና ያለው ሁኔታ ውጥረት የበዛበት ሲሆን ፤ዋናው ሆስፒታል የተዘጋው የጤና ባለሙያዎች ተግባራቸውን ለመወጣት ደህንነት ስለማይሰማቸው ነው። አንዳንዶቻችን በዛቻ እና ድብደባ  የቆሰሉ ሰዎችን እንድናክም ተገድደናል።»ብለዋል የጤና ባለሙያው።
በሆስፒታሉ ውስጥ በሥራ ላይ እያሉ ሦስት  ወንድ ሱዳናውያን  በጥይት ተመተው የተገደሉ ሲሆን፤ በከረኒክ ከተማ ከሆስፒታል ጋር የተያያዘው ዋናው መድሃኒት ቤትም ጥቃት ደርሶበት ሙሉ ለሙሉ መዘረፉን የዕርዳታ ድርጅቱ ገልጿል።
የድርጅቱ የመስክ  ስራ አስኪያጅ በክሪ አቡበከር በህክምና ሰራተኞች ላይ የተፈፀመውን ግድያ እና በጤና ተቋሙ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግጋትን ይጥሳል ሲሉ አውግዘዋል።በታካሚዎች ላይ የደረሰው ከፍተኛ እንግልትም ያሳስባቸዋል።
« ይህ በሰዎች ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ እንጨነቃለን። በተለይም በሆስፒታሉ በመውድሙ  እና ሰራተኞቹ በመሸሻቸው የተነሳ  የሚያስፈልጋቸውን የህክምና አገልግሎት ማግኘት ለማይችሉት በኬሬኒክ ለሚገኙ ቁስለኞች።እነዚህ ሰዎች መንገድ ላይ ባለው የደህንነት ስጋት  ወደ አልጄና ለህክምና መምጣትም አይችሉም።» 
በአል ገኒና የማስተማሪያ ሆስፒታል የህክምና ተወካይ ኤሚሊ ዋምቡጉ ጥቃቱን አስደንጋጭ እና አሰቃቂ መሆኑን ይገልፃሉ።
«በጣም ከባድ ቀን ነበር። በአካባቢው ብዙ ተኩስ ይሰማ ነበር። ከጠዋቱ 6 ስዓት ከ45 ነበር የተጀመረው። ወደ ሆስፒታሉ ብዙ ሰው ለህክምና መጥቶ ተመልሷል። ምንም አይነት አማራጭ አልነበረም ።ምክንያቱም ሁሉም ሰራተኞች ለህይወታቸው ስለሰጉ ሸሽተው ነበር።»
ጥቃቱን የተመለከተት ዋምቡጉ፣ ታማሚዎች በሆስፒታሉ ውስጥ በተኩስ ድምጽ በጣም በመረበሻቸው ህይወታቸውን ለማዳን መሮጥ ነበረባቸው ብለዋል።
ዋምቡጉ አያይዘውም የጤና አጠባበቅ እጦት በነፍሰ ጡር እናቶች እና አፋጣኝ እርዳታ በሚሹ ህጻናት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በዚህ መሰሉ ግጭትአሳሳቢ መሆኑን ገልፀዋል።
ሁከቱ አሁንም በሱዳን ውስጥ ያልተፈቱ ግጭቶችን የሚያንፀባርቅ ነው ሲሉ የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን ፎረም ሊቀመንበር ማሪና ፒተር ተናግረዋል ።ፒተር አያይዘውም ግጭቱ በግጦሽ መሬት ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል።
«ለግጦሽም ሆነ ለእርሻ የሚሆን መሬት እየቀነሰ ሄዷል። ከሌሎች ጉዳዮች  በተጨማሪ በግልጽ እንደሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው ቀውስ  ምክንያትም የሚፈጠር ነው። ለዓመታት  ለሀብት ትግል ሲደረግ ቆይቷል። ያስቆጠረ ነው።በእህል ዋጋ ማሻቀብ ምክንያትም የተባባሰ ሊሆንም ይችላል።ምክንያቱም በዩክሬን ጦርነት ሳቢያ የጥራጥሬ ዋጋ ጨምሯል።»
ማሪና ፒተር  እንደሚሉት በዳርፉር ከፍተኛ የነዳጅ እና የዩራኒየም ክምችት እንዳለ ብዙ ማሳያዎች አሉ። ያም ሆኖ የዳርፉርን ሁኔታ ለማርገብ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ያበረክታሉ ተብሎ አይታሰብም።ሰላማዊ መፍትሄ፣ ዲሞክራሲያዊ ልማት እና በአጠቃላይ የሱዳን ህዝብ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መሻሻል የሱዳን ወታደራዊ ኃይል በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ የማይቻል መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።
የዳርፉር ግጭት የተጀመረው በጎርጎሪያኑ የካቲት 2003 ዓ/ም የሱዳን ነፃ አውጭ ንቅናቄና እና የነፃነት እና የእኩልነት ንቅናቄ  የተባሉ ሁለት አማፂ ቡድኖች በዳርፉር  አረብ ባልሆኑ ሱዳናውያን ይደርሳል ያሉትን ጭቆና በመቃወም ከሱዳንን መንግስት ጋር ዉጊያ በጀመሩበት ወቅት ነው።
በዚህ ግጭት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የአረብ ዝርያ የሌላቸው ሰላማዊ ሰዎች  በሱዳን መንግስት ተገድለዋል በሚል የቀድሞው የሱዳን መሪ ኦማር አልበሽር በዘር ማጥፋት፣ በሰው ልጆች ላይ በተፈፀመ ወንጀል እና በጦር ወንጀል በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት  መከሰሳቸው ይታወሳል።

ምስል፦ Liba Taylor/robertharding/picture alliance
ምስል፦ AFP/Getty Images
ምስል፦ AFP
ምስል፦ Thomas Koehler/photothek/IMAGO

 

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW