1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የዩክሬን ጦርነት ያስከተለው የዋጋ መናር

ሐሙስ፣ የካቲት 24 2014

የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማድረሱ እየተነገረ ነው። የአንድ በርሜን ዋጋ 110 ዶላር መግባቱ የአፍሪቃ ሃገራት የኃይል አቅርቦት ላይ የዋጋ ጭማሪ አስከትሏል። ተጽዕኖው የነዳጅ ሀብት በሌላቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ናይጀሪያ ባሉ የነዳጅ ባለሀብቶች ላይ ሳይቀር ከወዲሁ መታየት ጀምሯል።

Nigeria Tankstelle in Abuja
ምስል፦ AFOLABI SOTUNDE/REUTERS

ጦርነቱ ያስከተለው የዋጋ መናር

This browser does not support the audio element.

ሚሊየኖች በሚኖሩባት የናይጀሪያዋ ሌጎስ ከተማ ነዳጅ ለመቅዳት ያለው ሰልፍ እና ትርምስ በዝቷል። በሰልፍ የተደረደሩት መኪናዎች ጡሩምባ ያሰማሉ እያንዳንዱ ለየራሱ የነዳጅ ቧምቧውን ጨብጦ ለመቅዳት ተጣድፏል። «

«ነዳጅ ማግኘት ልክ ወርቅ ቆፍሮ እንደማግኘት ሆኗል። እሱን ፍለጋ ለሰአታት እንባክናለን፤ በዚያ ላይ ደግሞ ለማግኘትህ እርገጠኛ መሆን አይቻልም። በርካቶች ነዳጁን የሚቀዱት በከፍተኛ ዋጋ ለመሸጥ ስለሚፈልጉ ነው። ናይጀሪያ እንዲህ ሆናለች።»

ዩክሬን ላይ የተከፈተው ጦርነት የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። ዓለም አቀፍ የኃይል ተቋም አባል ሃገራት ለመጠባበቂያ ከተያዘው 60 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ ለማውጣት ቢስማሙም የአንድ በርሜል ዋጋ 110 ዶላር ገብቷል። በዚህ መጠን  የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ከጎርጎሪዮሳዊው 2014 ዓም ወዲህ የመጀመሪያ ነው። ከዓለም ከፍተኛ ነዳጅ አቅራቢ ሃገራት አንዷ ሩሲያ ናት።   

ምስል፦ Julian Stratenschulte/dpa/picture alliance

የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞም የነዳጅ ዋጋ ከፍ ብሏል። ምክንያት፤ በኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ምክንያት የተዳከመው ኤኮኖሚ እንዲያገግም በሚደረግ እንቅስቃሴ በጨመረው የነዳጅ ፍላጎት። በዚያም ላይ ነዳጅ አቅራቢ ሃገራት እናሳድጋለን ያሉትን የነዳጅ አቅርቦት መጠን እንደቃላቸው አላሳደጉም። ከእነዚህ ሃገራት መካከልም አንጎላ እና ናይጀሪያ ይገኙበታል። ከአፍሪቃ ታላቋ ነዳጅ አቅራቢ የሆነችው የናይጀሪያ አራት የነዳጅ ማጣሪያ ተቋማት በአግባቡ ስለማይሠሩ እንኳን ለሌሎቹ የአፍሪቃ ሃገራት ልትተርፍ እራሷም ከውጭ ነዳጅ የምታስገባ ሀገር ሆናለች። የነዳጅ ማጣሪያዎቿ በየቀኑ 445 ሺህ በርሜል ነዳጅ የማውጣት አቅም አላቸው። ሆኖም ብልሹ አስተዳደር እና ሙስና የሀገሪቱ የነዳጅ ምርት ከባድ ተጽዕኖ አሳድረዋል። የዋና መናሩም በኃይል ምንጭ ላይ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ለዚህም ከሰሃራ በስተደቡብ ያሉ ጥሬ ሃብት ያላቸው ሃገራት ያላቸውን ጥቅም ላይ ለማዋል በሚያስችል መልኩ ባለመዘጋጀታቸው ለግሽበት መዳረጋቸው እንደማይቀር በናይጀሪያ ዛሪያ ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚ ምሁር የሆኑት አብዱል ጋንዩ ጋርባ ያመለክታሉ።

ምስል፦ DW/ Jochum

«አብዛኞቹ በጥሬ ሃብት የበለጸጉ ከሰሃራ በስተደቡብ ያሉ የአፍሪቃ ሃገራት በመሠረቱ ያላቸውን ሃብት፤ በእሴቱ ሰንሰለት ውስጥ ራሳቸውን ለመቻል በሚያበቃ መልኩ በአግባቡ አልያዙትም።»

በመሠረቱ ናይጀሪያ ውስጥ የነዳጅ ዋጋ በአህጉሩ ካሉ ሃገራት ጋር ሲነጻጸር በጣም ርካሽ የሚባል ነው። ለአንድ ሊትር፤ አራት የአሜሪካ ሳንቲም ። አንጎላ ደግሞ ከዚህም ዝቅ ይላል ሦስት አሜሪካ ሳንቲም። ይኸው ነዳጅ ቻድ ላይ ዘጠኝ የአሜሪካን ሳንቲም ነው። አሁን ግን የናይጀሪያ መንግሥት ይኽን ዋጋ ጠብቆ መዝለቅ አይችልም። በሌሎች የአፍሪቃ ሃገራትም ዋጋው ከፍ ብሏል። ደቡብ አፍሪቃ ከሦስት ወር በፊት 40,5 በመቶ ጭማሪ ተደርጓል፤ ቡርኪናፋሶም እንዲሁ ስምንት በመቶ ዋጋውን ከፍ አድርጋለች። ቡሩንዲም በጥር ወር መጨረሻ በነዳጅ ዋጋ ላይ 13 በመቶ ነው የጨመረችው። የቡሩንዲ የተቃዋሚ ፓርቲ ሊቀመንበር አሎይስ ባሪካኮ ይኽ አይነቱ ጭማሪ በታሪክ የመጀመሪያ ነው ይላሉ።

«በአንድ ሊትር ላይ 300 ፍራንክ ጨምረናል። ይኽ በቡሩንዲ ታሪክ በነዳጅ ዘይት ላይ 300 ፍራንክ ድንገተኛ ጭማሪ ሲደረግ የመጀመሪያ ነው።»

ምስል፦ Marijan Murat/dpa/picture alliance

አፍሪቃ ውስጥ ቡሩንዲ ብቻ ሳይሆን በማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፑብሊክ፣ዚምባቡዌ እና ሴኔጋልም የነዳጅ ዋጋ ቀድሞም ውድ ነው። በአብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገራትም መኪና ለማሽከርከር የነዳጅ ዋጋው ኪስ የሚገለብጥ ሆኗል። ከዚሁ ጎን ለጎንም የምግብ ዋጋ  እንደ ቶጎ እና ቡርኪናፋሶ ባሉ ሃገራት በእጥፍ ንሯል። የኬንያ መንግሥትም በዓለም የገንዘብ ድርጅት በቀረበለት ገቢውን የማሳደግ ጥያቄ ምክንያት በምግብ፣ በነዳጅ እና ማብሰያ ጋዝ ላይ የ14 በመቶ ጭማሪ አድርጓል። እርምጃውን የተቃወሙ ኬንያውያን በማኅበራዊ መገናኛው የምግብ ዋጋ ይቀንስ የሚል ዘመቻ ጀምረዋል።  

ሸዋዬ ለገሠ/ ዚሊያ ፍርሆሊሽ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW