1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የዩክሬን ፕሬዚዳንት ንግግር በጀርመን ምክር ቤት

ሐሙስ፣ መጋቢት 8 2014

የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጀርመን ምክር ቤት ቡንደስታኅ በኢንተርኔት የቪዲዮ መልእክት ዛሬ አስተላልፈዋል።ፕሬዚደንቱ በመልእክታቸው፦ «ጦርነቱን ለማስቆም ርዳታ የደረሰን ዘግይቶ ነው ሲሉም ቅሬታ አሰምተዋል።

Deutschland Bundestag | Rede Wolodymyr Selenskyj
ምስል Bernd von Jutrczenka/dpa/picture alliance

«በቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት መሀከል ነን»ም ብለዋል

This browser does not support the audio element.

የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጀርመን ምክር ቤት ቡንደስታኅ በኢንተርኔት የቪዲዮ መልእክት ዛሬ አስተላልፈዋል።ፕሬዚደንቱ በመልእክታቸው፦ «ጦርነቱን ለማስቆም ርዳታ የደረሰን ዘግይቶ ነው ሲሉም ቅሬታ አሰምተዋል። የጀርመን መንግሥት በእርግጥ በጦርነቱ በቀጥታ ባይሳተፍም ለዩክሬን ጦር መሣሪያ ለማቀበል ግን ውሳኔ ላይ መድረሱ ይታወቃል። እስካሁን ድረስ የጀርመን መንግሥት 1,000 ጸረ ታንክ ጦር መሣሪያዎችን፤ 500 ከምድር ተወንጫፊ ሚሳዪሎችን እንዲሁም 2,700 የሶቪዬት ዘመን ሚሳዪሎችን ወደ ምሥራቅ አውሮጳ ሃገራት ልኳል። የዩክሬን ፕሬዚደንት ዛሬ እንደተናገሩት ከሆነ፦ የጀርመን መንግስትም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ያሉት ርዳታን በጊዜ አላቀረቡላቸውም።

የዩክሬን ፕሬዚደንት በዛሬው ንግግራቸው የጀርመን መንግሥት ከሩስያ ጋር ያለውን የኤኮኖሚ ፍላጎትም በብርቱ ነቅፈዋል። ለጀርመን ዋነኛ የኃይል እና የጋዝ ምንጩዋ ደግሞ ሩስያ መሆንዋ ይታወቃል። እንደ ዩክሬን ፕሬዚደንት ፍላጎት ጀርመን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሩስያ ላይ ያላትን የኤኮኖሚ ፍላጎት ማቋረጥ ትችላለች?ለዩክሬን ጦር መሣሪያ እያቀበለችስ ከሩስያ ጋር በንግድ ትብብር መቀጠል ይቻላታል የሚለውም አጠያያቂ ነው።  ምናልባት በረዥም ጊዜ ካላሆነ በስተቀር ጀርመን ከሩስያ የኃይል ምንጭ በቀላሉ መላቀቅ አትችልም።

ምስል Tobias Schwarz/AFP

ዩናይትድ ስቴትስ በዋናነት የምትዘውረው የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) በዩክሬን ጦርነት በቀጥታ እንዳይሳተፍ ጀርመን አቋም ይዛለች። ኔቶም ቢሆን በቀጥታ ወደ ጦርነቱ መግባት የሚያስከትልበትን ጣጣ የተገነዘበ ይመስላል። ሩስያ ከበባ እየተፈጸመብን ነው ስጋት ገብቶኛል ስትል በተደጋጋሚ ትደመጣለች። ፕሬዚደንት ፑቲን የዛሬ 15 ዓመት ጀርመን ውስጥ በተኪያኼደው የሙኒክ የጸጥታ እና ደኅንነት ጉባኤ ላይ በተካፈሉበት ወቅት የኔቶ መስፋፋት ስጋት መሆኑን ተናግረው ነበር። የሀገራቸውን ደኅንነት ፈጽሞ ለአደጋ እንደማይያጋልጡም አስጠንቅቀው ነበር። በእርግጥ ኔቶ ባለፉት ሦስት ዐሥርተ ዓመታት እየተስፋፋ የምሥራቅ አውሮፓ ሃገራትን ጠቅልሎ ሩስያን እጅግ ተጠግቷል። የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ዛሬ ለጀርመን ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር፦ ጀርመን ከሩስያ ጋር ንግድ መቀጠሏን ተችተዋል። «በቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት መሀከል ነን»ም ብለዋል። ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ዳግም አገረሸ ማለት ነው፤ ግን ደግሞ አክትሞስ ነበር ማለት ይቻላል? የበርሊኑ ወኪላችን ለጥያቄዎቹ ማብራሪያ አለው።

ሙሉ ቃለ መጠይቁን ከድምፅ ማጫወቻው ማድመጥ ይቻላል። 

ይልማ ኃይለሚካኤል

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW