«የዩጋንዳ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በጋዜጠኞች ላይ ያደረሱትን ጥቃት ይመርምር»
ሰኞ፣ ሚያዝያ 19 2012
የጋዜጠኞች ጥቃት በዩጋንዳ
የዩጋንዳ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች በጋዜጠኞች ላይ ያደረሱትን ጥቃት እንዲመረምር የጋዜጠኞች መብት ጥበቃ ኮሚቴ ገለፀ።ኮሚቴው ጋዜጠኞች የኮሮና ወረርሽኝን በተመለከተ ያለምንም ጣልቃገብነት እንዲዘግቡ ጠይቋል።
በዩጋንዳ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሀገሪቱ መንግስት የተለያዩ ገደቦችን ከጣለ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ቢሆንም ጋዜጠኞች ስራቸውን በነፃነትና በጥንቃቄ እንዲሰሩ እንዲሁም ስለበሽታው ለህዝቡ መረጃ እንዲያደርሱ ለማድረግ፤ እገዳው እነሱን እንደማይመለከት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሞሶቬኒ ገልፀው ነበር።
ያም ሆኖ ካለፈው መጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ በዩጋንዳ የፀጥታ ኃይሎች የCVIDID-19 ስርጭትን ለመግታት የተጣለውን እገዳ ለማስፈፀም በሚደረግ ቁጥጥር ቢያንስ ስድስት ጋዜጠኞች ጥቃት ድርሶባቸዋል ሲል የዩጋንዳ የጋዜጠኞች መብት ጥበቃ ኮሚቴ ገልጿል።የኮሚቴዉ ከስሃራ በታች ያሉ ሀገራት ተወካይ ሞቶኪ ሙሞ እንደሚሉት ጋዜቸኞች ያለምንም ጥፋት እስራትና ድብደባ እየደረሰባቸው ነው።
«በዩጋንዳ በቅርቡ እያየነው ያለው ጥቃት ቁጥር በጣም የሚያስደነግጥ ነው።የፖሊስ መኮንኖች፣ወታደራዊ አዛዦችና የአካባቢዉ ባለስልጣናት ጋዜጠኞችን ያንገላታሉ ጥቃት ያደርሳሉ ያስራሉ።ጋዜጠኞች የሚታሰሩት የኮቪድ-19ን ለመከላከል ተብለው የውጡ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ለማስፈፀም በሚል ነው። አንዳንድ ጊዜም ስራቸውን ስለሰሩ ብቻ ጋዜጠኞች እንዲወጡ ይደረጋሉ።»
ያለፈው መጋቢት ወር የዩጋንዳ ሬዲዮ ኔትወርክ የቢሮ ሃላፊ ጁሊየስ ኦኩንግን ፎቶ ያነሱ በነበረበት ወቅት የፖሊስ መኮንኖች ክብራቸውን በሚነካ መልኩ በጥፊ እንደመቷቸውና ከባድ ድብደባ እንደተፈፀሙባቸው የኮሚቴዉ ዘገባ ያሳያል።በሚያዚያ ወርም ዴይሊ ሞኒተር ለተባለው የግል ጋዜጣ በሪፖርተርነት የሚሰራ ፔሬዚ ሩምናዚ የተባለ ጋዜጠኛም በፀጥታ ሀይሎች ተመሳሳይ ድብደባ ደርሶበታል።በዚህ ሁኔታ ጥቃት ደርሶባቸው ሆስፒታል የገቡ መኖራቸዉቸዉንም ሃላፊዋ አስረድተዋል።
«በጣም ቅርብ በሆነው ዘገባችን ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ሚያዚያ መጨረሻ ባለው ጊዜ ውስጥ ስድስት በፀጥታ ሀይሎች ድብደባና ማስፈራሪያ የደረሰባቸውን ጋዜጠኞችን አነጋግረናል።ከነዚህ ውስጥ አራቱ ከፍተና ጉዳት ደርሶባቸዉ ሆስፒታል ገብተዉ ነበር።ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ ለበርካታ ቀናት ሆስፒታል ቆይተዋል።»
ኮሚቴው በጋዜቸኞቹ ላይ የደረሰውን ጥቃት በየደረጃው ላሉ የመንግስት ባለስልጣናት ቢያሳዉቅም እስካሁን «እናጣራለን» ከማለት ውጭ የተወሰደ ርምጃ አለመኖሩንም አመልክቷል።
«የሀገሪቱ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑንና ትኩረት እንደተሰጠው ነግረውናል።ነገር ግን ጋዜጠኞች ለአካባቢው ባለስልጣናት ማመልከት አለባቸዉ።ችግሩ የደረሰባቸዉን ለአካባቢዉ ባለስልጣናት ለመናገርና ፍትህ ለመፈለግ ሲሞክሩ ሁኔታው ያስፈራቸዋል።»
ስለሆነም የሀገሪቱ መንግስት በጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በአስቸኳይ እንዲመረምርና ጥቃት ያደረሱ የፀጥታ ሀይሎችንም ለህግ እንዲያቀርብ ኮሚቴው ጠይቋል ።የመገናኛ ብዙሃንም COVID-19ን በሚመለከት ያለ ምንም ጣልቃገብነት የመዘገብ መብታቸው እንዲከበር ሲፒጄ አሳስቧል።
ጸሐይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ