የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎች ጉዳይ
ረቡዕ፣ ጥር 29 2016የአማራ እና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጠያቄ የሚያነሱባቸው ቦታዎችን በተመለከተ መንግሥት ካቀረበው የችግሩ መፍቻ አማራጭ ውጪ የሁለቱ ክልሎች ምኁራን የተሻለ አማራጭ ማቅረብ ከቻሉ የፌዴራሉ መንግሥት ተባባሪ እንደሚሆን ተገለፀ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት ለሕዝብ ተወተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ሲሰጡ "ከጦርነት በመለስ በሰላማዊ መንገድ ሁለቱን ሕዝቦች ሳያጋጭ የሚፈታበት ካለ የፌዴራሉ መንግሥት ተባባሪ ይሆናል" ሲሉ የሚቀርብን የመፍትሔ አማራጭ ለመቀበል መንግሥታቸው ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ አስቀድሞ በዚሁ ጉዳይ ላይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተለያየ ሀሳብ በመግለጫ ያወጡ ሲሆን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያወጣውን መግለጫ እንደማይቀበለው አስታውቋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መግለጫዎች
በአማራ በኩል ወልቃት ጠገዴ ሠቲት ሁመራ ፣ በትግራይ በኩል ምዕራብ ትግራይ የሚባለው እና ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገር ሱዳን የሚያዋስነው መሠረታዊ የግብርና ምርቶች - ሰሊጥ፣ ጥጥ እና ማሽላ በስፋት የሚመረቱበት አካባቢ ያለው የይገባኛል ጥያቄ "ዘላቂ ሰላምን በሚያረጋግጥ መልኩ ይፈታ" የሚል የፌዴራል መንግሥት አቋም መኖሩን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህንን ሥራ ለማከናወን ግጭት ችግር መፍጠሩን አንስተዋል። ያም ቢሆን ግን ጉዳዩ በሕዝበ ውሳኔ እስኪፈታ ድረስ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች እንዲከናወኑ ጥረት ሲደረግ እንደነበር ገልፀዋል።
መቐለ በሺህዎች የሚቆጠሩ የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ
"ያለው መፍትሔ በሰከነ መንገድ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምኁራን ተሳትፈውበት ፣ በምክክር በውይይት ሰላምን በሚያረጋግጥ መንገድ እንፍታው" የሚል መሆኑን ጠቅሰዋል። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጥር 23 ቀን 2016 "የፕሪቶርያው ስምምነት ከምንም በላይ ተግባራዊ ምላሽ ይፈልጋል" በሚል በጽሑፍ ባወጣው መግለጫ "የአከራካሪ ቦታዎችን ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ጉዳዩ በዋናነት ከሚመለከታቸው ከአማራ እና ከትግራይ ክልሎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር" ሲል የክልሉ አስተዳደር ስምምነቱ ይከበር በሚል ላወጣው መግለጫ ምላሽ ሰጥቷል።
ለዚህ መግለጫ ቀጥተኛ ምላሽ የሰጠው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር "ጉዳዩን በሪፈረንደም ለመፍታት መረዳዳት ላይ ተደርሶ ነበር በሚል የቀረበው መግለጫ ፍፁም የተሳሳተ እና ተቀባይነት የሌለው" መሆኑን ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰጡት ማብራርያ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከሁለቱም ክልሎች የተሻለ የመፍትሔ አማራጭ መቅረብ ከቻለ መንግሥት የሚቀበል መሆኑን አረጋግጠዋል።
"ከጦርነት በመለስ በሰላማዊ መንገድ ሁለቱን ሕዝቦች ሳያጋጭ የሚፈታበት ካለ የፌዴራሉ መንግሥት ተባባሪ ይሆናል"
ተፈናቃዮችን የመመለስ ጉዳይ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት "በአንዳንድ አካባቢዎች ትክክለኛ ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ መደረጉን" በመግለጫው የጠቀሰ ሲሆን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይህ "እጅግ አደገኛ እና በጉልበት የሀገሪቱን ካርታ ለመቀየር የተደረገውን አውዳሚ እንቅስቃሴ ሕጋዊ ሽፋን የሚሰጥ" አድርጎ ገልጾ እንደማይቀበለው አስታውቋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፌዴራሉ መንግሥት ከመፍትሔው ይልቅ የችግሩ አካል ለመሆን የወሰነ ያስመስለዋል ሲልም ወቅሷል።
ተጠያቂነትን በተመልከተ
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግሥት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከጦርነቱ ጋር በተገናኘ ተጠያቂነትን በሚመለከት ያቀረበውን ሀሳብም ውድቅ አድርጎታል። ኮሙኒኬሽን አገልግሎት "ከሰሜኑ ጦርነት ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥቱ ተገቢውን ርምጃ በእሱ በኩል ወስዷል። ተጠያቂ መሆን ያለባቸውንም ተጠያቂ አድርጓል" ያለ ሲሆን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይህ "ምን ይህል እውነት አለው የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ ፍትሕ የማረጋገጥ ተግባር የዘመቻ ጉዳይ እንዳልሆነ ታውቆ" ሁሉም ሊሠራበት ይገባል ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና የህወሓት መወቃቀስ
የፌዴራሉ መንግሥት ከፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት በኋላ 37 ቢሊዮን ብር ለትግራይ ክልል ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በክልሉ የፌዴራል ምንግሥቱ እና ጊዜያዊ አስተዳደሩ "ትልልቅ ድሎችን አስመዝግበዋል" ሲሉ ትናንት ተደምጠዋል።
ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ