1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሕግ እና ፍትሕ

የአማራ ክልል ዳኞችና የጉባኤ ተሿሚዎች የደመወዝ ጭማሬ እና ጥቅማጥቅም መዘግየት

ኢሳያስ ገላው
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 23 2017

የአማራ ክልል ዳኞችና የጉባኤ ተሾሚዎች ቃል የተገባልን የደመወዝ ማሻሻያና ልዮልዮ ጥቅማጥቅም ገቢራዊ አለመደረግ ለከፍተኛ የኑሮ ጫና ዳርጎናል ይላሉ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ያነጋገርናቸዉ ዳኞች ።

Symbolbild Justiz Gericht Richterhammer
ምስል፦ picture alliance/imageBROKER

በአማራ ክልል የደመወዝ ጭማሬ እና ጥቅማጥቅም መዘግየት

This browser does not support the audio element.

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅርቡ የፍርድ ቤቶችን የማጠናከሪያ አዋጅ በማፅደቅ በክልሉ የመጀመሪያ የሆነውን የዳኞችን ያለመከሰስ መብት ህጋዊ እዉቅናና ከለላ መስጠቱ ይታወሳል። ይሁን እንጂ የክልሉ ዳኞች የጉባኤ ተሿሚዎች ከሚሰሩት ስራ አንፃር የሚከፈላቸዉ ደመወዝና ጥቅማጥቅም ሊሻሻል ይገባል ተብሎ  ዳኞች የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግልን ቢወሰንም  እስካሁን ተፈፃሚ ባለመሆኑ «ለከፍተኛ ኑሮ ዉድነት ተዳርገናል» ይላሉ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ያነጋገርናቸዉ ዳኞች ።

የኑሮ ዉድነትና ጫናዉ

"የኑሮ ዉድነቱ ጫና በጣም ከባድ ነዉ እንኳን አሁን ባለዉ ደመወዝ ጭማሪዉ እንኳን ቢሰጠን ኑሮን መቋቋም በጣም ይከብዳል እንግዲህ ይከፈለናል ብለን ነበር ስንጠብቅ የነበረዉ አሁን የሚያዚያ ደርሷል በዚህ ወርም ሊተገበር አልቻለም አልተገለጸም ምክንያቱ ሁሉም በአዲሱ ይከፈለናል ብሎ ጠብቆ ነበር ።ሁሉም አዝኗል ደስተኛ አይደለም" ይላሉ ዶይቸ ቬለ ካነጋገራቸው ዳኞች አንዱ።

ከ5አመት በፊት በተሰራ የደመወዝ መዋቅር እያገለገልን ነዉ የምንገኘዉ የሚሉት ዳኞች በዚህ አምስት አመት ግን የኑሮ ዉድነቱ በከፍተኛ መጠን ማደጉ ለስራችን እንቅፋት ፈጥሮብናል ይላሉ። "ከአምስት አመት በፊት ነዉ የተጨመረዉ ጭማሬ እስካሁን ድረስ በዚህ አምስት አመት ዉስጥ የኑሮ ዉድነቱ በጣም ከመቶ  ፐርሰንት በላይ ነዉ የጨመረዉ ሁለት መቶ ፐርሰንት፤ የስራ ተነሳሽነታችንን እንዲቀንስ አድርጓል በቂ ነዉ የሚባል አይደለም ከእጅ ወደአፍ ነዉ ስራዉና ክፍያዉ ተመጣጣኝ አይደለም"

የዳኞች ፍልሰት

በአማራ ክልል በርካታ ዳኞች ከዚህ ቀደም ለቀዋል የሚሉት አስተያየት ሰጭም  አሁን ከደመወዝ ማሻሻያው ገቢራዊ አለመሆን ጋር ተያይዞ እና በክልሉ ያለዉ የፀጥታ ሁኔታ ለለስራ ምቹ ባለመሆኑ ለመልቀቅ በር ላይ የቆሙ መኖራቸዉ ተነግሯል። "የአማራ ክልል በራሱ በጀት ዳኛና አቃቤ ህግ አሰልጥኖ ለፌደራል መንግስቱ የሚሰጥ ብቸኛ ተቋም ሆኗል በጣም የዳኞች ፍልሰት አለ የኑሮ ዉድነቱ ጫናዉ ስላለ የምታየዉ ነገር ጥቅማጥቅም ሲያንስ የተሻለ ነገር ያምርሀል እንደሰዉ በዚያ ምክንያት ፍልሰቱ እንደጨመረ ነዉ አሁንም ቢሆን ወጣቱ በተለይ ለመልቀቅ ነዉ አኮብኩቦ ያለዉ ያለዉ ሁኔታ ስራ ስለማያሰራም ይህነገር ገቢራዊ ካልተደረገ ጭማሬዉ ፍልሰቱ ይቀጥላል"

በማሻሻያዉ ተፈፃሚነት ላይ ተስፋ  መቁረጥ

ባህር ዳር ከተማምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

በክልሉ በሁሉም ደረጃ ያሉ ዳኞችን መብት የሚያስከብረዉ የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ከዚህ ቀደም የደመወዝ ማሻሻያው እንዲፀድቅ በርካታ ስራ መስራቱን በማህበራዊ የትስስር ገፁ የጠቀሰ ቢሆንም ዳኞች ግን የደመወዝ ማሻሻያው ገቢራዊነት ላይ ጥርጣሬ አላቸዉ
 "መጀመሪያ ላይ እንደማንኛዉም መንግስት ሰራተኛ ዳኞችም ከሰራ ጫና አንፃር እየተከፈለን የነበረዉ ደመወዝ በቂ አይደለም።  እረዥም ሰአት ተቀምጦ ነው የሚውለው።  በሰዉ ህይወትና ንብረት ላይ የሚወስን ነዉ ዳኛ ለማንኛዉም መንግስት ሰራተኛ ደመወዝ ማስተካክያ ሲደረግ ዳኞችም ይጠብቁ ስለነበር ከየካቲት ወር ጀምሮ ያለፈ ክፍያ ደመወዝ ከጥቅምት ጀምሮ እንደሚከፈል አይተን ነበረ ።አሁን ተስፋ ወደ ማስቆረጥ ደረጃ ደርሷል" ይላሉ።

በአማራ ክልል በዳኞች ላይ እስር እና ማዋከብ እየተፈጸመ ነው ፤ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን

የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ተወካይ ሰብሳቢ አቶ ብርሀኑ አሳሳ በዚህ የዳኞች ጥያቄ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጡን ብንጠይቃቸዉም ማህበሩ በፌስቡክ ማህበራዊ የትስስር ገፁ ላይ አሁናዊ ሁኔታዉን መግለፁን አዉስተዉ መረጃ በድምፅ ለመስጠት ተከልክለዋል። ማህበሩ ግን ከሦስት ቀናት በፊት  ባወጣዉ መረጃ የሚያስፈልገውን በጀት የሚመድበው የክልሉ መንግስት በመሆኑ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የበጀት መጠኑን ጠቅሶ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለክልሉ ምክርቤትና ገንዘብ ቢሮ አሳዉቆ እስኪለቀቅለት እየጠበቀ መሆኑን አባላቴ ይወቁልኝ ብሏል። ይሁን እንጂ በዚህ የዳኞች ቅሬታ ዙሪያ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምን ምላሽ ይሰጥበታል ስንል የጠየቅናቸዉ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች አብይ ጉባኤ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደራዉ ወርቁ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW