1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደሞዝ ይከፈለን አድማ በሃድያ ዞን

ሰኞ፣ ሐምሌ 15 2016

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን የሾኔ የመጀመሪ ደረጃ ሆስፒታል ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ መቱ፡፡ የሁለት ወራት ደሞዛችን ይከፈለን የሚለው ጥያቄ የአድማው መነሾ ምክንያት ነው ተብሏል ፡ ሠራተኞቹ ሥራ መቆማቸውን ለዶቼ ቬለ ያረጋገጡት የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር የሠራተኞቹን ጥያቄ ለዞንና ለክልል መስተዳድሮች ማሳወቃቸውን ተናግረዋል ፡፡

ቁጥራቸው ከሦስት መቶ በላይ የሚሆኑት የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ
ቁጥራቸው ከሦስት መቶ በላይ የሚሆኑት የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማምስል Privat

የደሞዝ ይከፈለን አድማ በሃድያ ዞን

This browser does not support the audio element.

የደሞዝ ይከፈለን አድማ በሃድያ ዞን

በሀድያ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ክፍያ መስተጓጎል ዛሬም መፍትሄ ማግኘት የተነሳው ይመስላል ፡፡ በተለይም በዞኑ ምሥራቅ ባድዎቾ ወረዳ ሠራተኛው ከደሞዝ ክፍያ ጋር ተያይዞ ዓመቱን ቅሬታ ሲያሰማ ፤  አድማ ሲመታ ነው የከረመው ፡፡ በአድማው ሰበብ አንድ ጊዜ ሲዘጉ ሌላ ጊዜ ሲከፈቱ የሰነበቱ ትምህርት ቤቶችና የህክምና ተቋማት ተገልጋዩን ለእንገልት ሠራተኛውን ለኑሮ  ችግር መዳረጋቸው አልቀረም ፡፡

አሁን ላይ በዞኑ የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሠራተኞች በዚህ ዓመት ብቻ ለሦስተኛ ጊዜ የሥራ ማቆም አድማ መምታታቸው እየተነገረ ይገኛል ፡፡ የሁለት ወራት ደሞዛችን ይከፈለን የሚለው ጥያቄ የአድማው መነሾ ምክንያት መሆኑን ነው  የአድማው ተሳታፊ ሠራተኞች ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ፡፡

ግማሽ ክፍያ

ቁጥራቸው ከሦስት መቶ በላይ የሚሆኑት የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ እያደረጉ የሚገኙት ከባለፈው ዓርብ ጀምሮ መሆኑን ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸውና ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሁለት የሆስፒታሉ ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡ በወረዳው በተደጋጋሚ የደሞዝ ክፍያ ባለመፈጸሙ ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር መቸገራቸውን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ “ ያልተፈጸመው ክፍያ የግንቦት እና የሰኔ ወር ነው ፡፡ ነገር ግን የግንቦትን ዘለው የሰኔ ወር እንደሚከፈል ነግረውናል ፡፡ በዚህም አብዛኛው ሠራተኛ በግማሽ ክፍያው አልተስማማም ፡፡ የሆስፒታሉ አስተዳደር ጥያቄያችንን ሊመልስ ባለመቻሉ ሥራ አቁመን እንገኛለን “ ብለዋል ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ሠራተኞቹ ከባለፈው ዓርብ ጀምሮ ሥራ ማቆማቸውን የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል  ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ አህመድ ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል ፡፡ ሠራተኞቹ ጥያቄያቸው ካልተመለሰ ሥራ እንደማይገቡ ተፈራርመው ማስገባታቸውን የጠቀሱት ሜዲካል ዳይሬክተሩ “ በዚህም የተነሳ አሁን ላይ ሆስፒታሉ በሠራተኞች አለመገኘት የተሟላ አገልግሎት መስጠት አልቻለም ፡፡  በእኛ በኩል የሠራተኞቹን ጥያቄ ለሃድያ ዞን እና ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስተዳድሮች አሳውቀናል ፡፡ ነገር ግን  ካሽ / ጥሬ ገንዘብ / የለም ፡፡እየተፈለገ ነው ጠብቁ የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል  “ ብለዋል ፡፡

የእንገባለን አትገቡም እሰጥ አገባ

በደሞዝ ይከፈለን አድማ ውስጥ የሚገኙት የሆስፒታሉ ሀኪሞች ጥያቄያችን በሆስፒታሉ አስተዳደር ደረጃ ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም ይላሉ ፡፡ በመሆኑም ክፍያው እንዲፈጸምላቸውለሃድያ ዞን መስተዳድር ለማመልከት ባለፈው ዓርብ በሁለት አውቶብሶች ወደ ሆሳዕና ከተማ ማቅናታቸውን ገልጸዋል  ፡፡ ነገር ግን የሆሳዕና የፖሊስ አባላት በከተማ መግቢያ ላይ በመጠበቅ ወደ ከተማው እንዳይገቡ እንደከለከሏቸው  የጠቀሱት ሠራተኞቹ “እኛ አቤቱታችንን ለሚመለከተው አካል በሰላማዊ መንገድ ለማሰማት ነው የምንፈልገው ፡፡ ከዚህ ውጭ ሌላ ዓላማ የለንም ብለን ብንናገረም የፖሊስ አባላቱ ሊሰሙን አልፈለጉም ፡፡ በእኛና በአባላቱ መካከል ወደ ከተማው እንገባለን አትገቡም በሚል በተነሳ ጭቅጭቅ መግባባት አልቻልንም ፡፡ በመጨረሻ ወደመጣችሁበት ካልተመለሳችሁ ትታሰራላቹ በሚል ማስፈራራት ሲጀምሩ ቅሬታችንን ሳናቀርብ ወደ ሾኔ ከተማ ልንመለስ ችለናል “ ብለዋል ፡፡

ሃድያ፤ ሆሳዕና ከተማ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የሆስፒታሉ አስተዳደር ተማፅኖ

ዶቼ ቬለ የሃድያ ዞንና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጤናና የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ቢሞክርም ሃላፊዎቹ የሥልክ ጥሪ ባለመመለሳቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻለም ፡፡ የሾኔ ሆስፒታል ሜዲካል  ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ ግን  የሆስፒታሉ አስተዳደር በአድማው ምክንያት ተገልጋዩ ማህበረሰብ እንዳይጉላላ ለማድረግ  ሠራተኞች እየሠሩ መብታቸውን እንዲጠይቁ በማድረግ ለማግባባት እየተሞከረ ይገኛል ብለዋል ፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን በማዳበሪያ ብድር ዕዳና በጥሬ ገንዘብ እጥረትየተነሳ ሠራተኞች ደሞዝ በወቅቱ እንደማያገኙ ይታወቃል ፡፡ በዚህም የተነሳ በተለይ መምህራንና ሀኪሞች  በተደጋጋሚ ቅሬታዎችንና ሲያሰሙና የሥራ ማቆም አድማ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW