የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል
ረቡዕ፣ ጥቅምት 24 2014
ማስታወቂያ
የደቡብ ክልል ምክር ቤት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የፌዴራሉ 11ኛ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ የሚያስችለውን የሥልጣን ርክክብ አካሄደ ።
ምክር ቤቱ የሥልጣን ርክክቡን ያደረገው ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ባካሄደው 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት አስቸኳይ ጉባኤ ነው ።
ምክር ቤቱ ርክክቡን ያደረገው በህዝበ ውሳኔው አፈጻጸም ዙሪያ በቀረበለት ሪፖርት ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ነው ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ የካፋ ፣ የሸካ ፣ የዳውሮ ፣ የቤንች ሸኮ ፣ የምዕራብ ኦሞ እና የኮንታ ልዩ ወረዳ ራሳቸውን ችለው በክልልነት ለመደራጀት የሚያስችላቸውን የሕዝበ ውሳኔ ድምፅ የሰጡት ባለፈው መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ነበር።
በህዝበ ውሳኔው ድምፅ ከሰጡት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን መራጮች መካከል ከ98 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከደቡብ ክልል በመነጠል የጋራ ክልል መመሥረትን ደግፈው ድምፅ መስጠታቸውን የኢትዮጲያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል ።
በሕዝበ ውሳኔው ድምፅ ውጤት መሰረት አምስቱ ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ በቀጣዩ ሳምንት የጋራ ያሉትን ክልል ያዋቅራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ