የደቡብ ሱዳን ቶፖሳ ጎሳ አባላት ድንበር ተሻግረው ኢትዮጵያ መግባታቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 11 2012
ማስታወቂያ
የቶፖሳ የሚባለው የደቡብ ሱዳን ጎሳ አባላት የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው በደቡብ ክልል መስፈራቸውን በደቡብ ክልል የምዕራብ ኦሞ ዞን መስተዳድር አስታወቀ።
የጎሳ አባላቱ ከቅርብ ወራቶች ወዲህ ቀስ በቀስ የኢትዮጵያ የድንበር ወሰን በማለፍና ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ውስጥ በመግባት በአሁኑ ወቅት ማርዳ በተባለ ቦታ ሰፈረው እንደሚገኙ አንድ የምዕራብ ኦሞ ዞን መስተዳድር ከፍተኛ ባለስልጣን ገልጸዋል።
ከአጎራባች የደቡብ ሱዳን ግዛት የተነሱት የእነኝሁ ጎሳ አባላት ቁጥር አስከ አስር ሺህ ይገመታል ያሉት በለስልጣኑ አብዛኞቹ የጦር መሳሪያዎችን የታጠቁ በመሆናቸው በአካባቢው የጸጥታ ስጋት ማሳደሩን አስረድተዋል።
የደቡብ ሱዳን የቶፖሳ ጎሳ አባላት ወደ ኢትዮጲያ ግዛት ዘልቀዋል የተባለው ትክክለኛ ሲል ያረጋገጠው የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር እየሰራሁበት እገኛለሁ ብሏል።
ሸዋንግዛው ወጋየሁ