የደቡብ አፍሪካ እና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ ያየለበት የቡድን 20 ጉባኤ
ሰኞ፣ ኅዳር 15 2018
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ የቡድን 20 ጉባኤ ትላንት እሁድ ሲጠናቀቅ ስኬታማ እንደነበር ተሰምቷቸዋል። ጉባኤው በበርካታ ምክንያቶች ከቀደሙት የተለየ ነበር። በጎርጎሮሳዊው 1999 የተጀመረው የቡድን 20 ጉባኤ በአፍሪካ ሲካሔድ የመጀመሪያው ነው። ለዓለም ቀውሶች መፍትሔ ለማፈላለግ በተጀመረው ዓለም አቀፍ ጉባኤ አሜሪካ ሳትሳተፍ ስትቀር ለመጀመሪያ ጊዜ ሆኗል።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ግን “አንዳንዶች በሀገራት መካከል ክፍፍል እና ልዩነት ለመፍጠር ቢጥሩም” በጉባኤው “የጋራ ሰብአዊነታችንን አጠናክረናል” ሲሉ የአሜሪካ እና መሪዋ ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ ያጎደለው እንደሌለ ለመግለጽ ሞክረዋል። ዛሬ ሰኞ ባወጡት መግለጫ በጉባኤው “ትብብር እና በጎ ፈቃድን አሳድገናል” ያሉት ራማፎሳ ለደቡብ አፍሪካ ሕዝብ “ከሁሉም በላይ የጋራ ግቦች ከልዩነቶቻችን እንደሚበልጡ አረጋግጠናል” ሲሉ ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል።
ራማፎሳ እና ሀገራቸው “የአፍሪካን ዕድገት እና ልማት የቡድን 20 አጀንዳዎች ማዕከል” የማድረግ ፍላጎት ነበራቸው። ጉባኤው ሲጠናቀቅ “የ21ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ የብልጽግና ዕድል በአፍሪካ ይገኛል” ያሉት ራማፎሳ “ይህን ዕድል መጠቀም በአፍሪካ እና በቡድን 20 እንዲሁም በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም መካከል ጠንካራ አጋርነት ይፈልጋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
በጁሐንስበርግ ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሔደው የቡድን 20 ጉባኤ “ለተበላላጭነት” መፍትሔ በማፈላለግ እና ዘላቂ ዕድገትን በማበረታታት ፍትኃዊ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ማበጀት የሚቻልበት ስልት ላይ ያተኮረ ነበር። በጉባኤው ከከባቢ አየር ለውጥ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የተወሰኑ አለመግባባቶች ቢፈጠሩም ደቡብ አፍሪካ ለባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እና በሕግጋት ላይ የተመሠረተ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ባላት ቁርጠኝነት ከፍተኛ ድጋፍ ማሰባሰብ ችላለች። ይህ በቡድን 20 ጉባኤ የመሪዎች መግለጫ ላይ በግልጽ ተንጸባርቋል።
መግለጫው ከወትሮው አካሔድ በተለየ በፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ግፊት በሙሉ ድጋፍ የጸደቀው በጉባኤው መክፈቻ ዕለት ባለፈው ቅዳሜ ነበር። በአጠቃላይ 122 ነጥቦች የያዘው የመሪዎች መግለጫ ለባለ ብዙ ወገን ትብብር አጽንዖት የሰጠ ሲሆን ሁሉን አቀፍ ዕድገት እና ዘላቂ ልማትን ለማፋጠን ለአዳጊ ሀገራት የተጠናከረ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
መግለጫው በፍጥነት ተቀባይነት ማግኘቱ ከዩናይትድ ስቴትስ አቋም ጋር በእጅጉ የሚቃረን ሆኗል። ከጉባኤው በፊት በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ያለ ዩናይትድ ስቴትስ ይሁንታ በሥምምነት የሚጸድቅ ማንኛውንም ውሳኔ እንደሚቃወም ለሲሪል ራማፎሳ መንግሥት ገልጾ ነበር። አሜሪካ ጉባኤው አንዳች መልዕክት ቢያወጣ እንኳ “የሊቀ-መንበሩ መግለጫ” ሊባል እንደሚገባ አሳውቃ ነበር። ደቡብ አፍሪካ ግን አሜሪካ በጉባኤው ባለመሳተፍ በሒደቱ ሊኖራት የሚችለውን ድምጽ በማጣቷ አካሔዱን ማዘዝ እንደማትችል መልስ ሰጥታለች።
የቡድን 20 የመሪዎች መግለጫ ምን ይላል?
የቡድን 20 መሪዎች በሱዳን፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በእስራኤል በጉልበት በተያዙት የፍልስጤም ግዛቶች እና በዩክሬን “ፍትኃዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላዊቂ ሰላም” እንዲወርድ፤ ሌሎች በዓለም ዙሪያ የሚካሔዱ ግጭቶች እና ጦርነቶችን ለማብቃት “እንሰራን” ሲሉ ቃል ገብተዋል።
“በዚህ ዓመት በርካታ በማደግ ላይ የሚገኙ ኢኮኖሚዎች ባለቤት የሆኑ ሀገራት ላይ የበረታው የዕዳ ጫና የተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ዋንኛ እንቅፋት እንደሆነ ዕውቅና ሰጥተናል” ያሉት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት “መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት የዕዳ ተጋላጭነታቸውን ሲጋፈጡ ቡድን 20 ለመደገፍ ቃል ገብቷል” ሲሉ ራማፎሳ የመግለጫውን ይዘት አብራርተዋል።
መሪዎቹ የዕዳ ጫናን በመቀነስ እና የመንግሥታትን ኢንቨስትመንት በማሳደግ ፈጣን እና አካታች ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መፍጠር እንደሚያስፈልግ በአጽንዖት አሳስበዋል። በከባቢ አየር ለውጥ ምክንያት ከተፈጠሩ ቀውሶች በኋላ የመልሶ ግንባታ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ ቀርቧል።
“የከባቢ አየር ለውጥ ሁሉንም ሀገር ይነካል፤ ተጽዕኖው ፍትኃዊ ባልሆነ መንገድ በሁሉም ላይ ያርፋል” ያሉት ራማፎሳ “በማደግ ላይ ለሚገኙ ኢኮኖሚዎች የሚሰጠውን ድጋፍ በጥራት እና በብዛት ለማሳደግ፤ ባለ ብዙ ወገን የልማት ባንኮችን ለማጠናከር፤ ፍትኃዊ የኃይል ሽግግር እንዲፈጠር የሚደረጉ የሀገራት ጥረቶችን ለመደገፍ እና ከግሉ ዘርፍ ገንዘብ ለማሰባሰብ ወስነናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ራማፎሳ በተሳታፊዎቹ ዘንድ የጋራ መግለጫውን በተመለከተ ከፍተኛ መግባባት መኖሩን ቀደም ብለው አስታውቀዋል። ይሁንና የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አጋር የሆኑት የአርጀንቲናው ፕሬዝደንት ሐቪየር ሚሌይ ረቂቁ ከመጽደቁ በፊት ስብሰባውን ረግጠው እንደወጡ የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣን ለሬውተርስ ተናግረዋል። የአርጀንቲና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ፓብሎ ኩይርኖ መግለጫው “ለረዥም ጊዜ የቆየውን የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት የገለጸበት መንገድ ውስብስብነቱን” ከግምት ውስጥ ያስገባ እንዳልሆነ ለሬውተርስ ተናግረዋል።
መግለጫው የከባቢ አየር ለውጥን አሳሳቢነት ለመግለጽ የተጠቀመበት ቋንቋ፣ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ለማጠናከር የቀረበው ጥሪ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የሚወደድ አይደለም። ፕሬዝደንቱ የሰው ልጆች እንቅስቃሴ የምድር ሙቀት በአሳሳቢ ፍጥነት እንዲጨምር አድርጓል በሚለው ሳይንሳዊ ትንታኔ አይስማሙም። ባለሥልጣኖቻቸው አስቀድመው እንዲህ አይነት አገላለጽ በመግለጫው እንዳይካተት ግፊት እንደሚያደርጉ አስታውቀው እንደነበር ሬውተርስ ዘግቧል።
በጁሐንስበርግ እነማን ነበሩ?
የመሪዎች መግለጫውን ያለ አሜሪካ ተሳትፎ ከዚህ በፊት እንደሚደረገው ከመዝጊያው ይልቅ በመክፈቻው በጸደቀበት ጉባኤ የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርስ እና የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮን ጨምሮ በርካታ መሪዎች ታድመዋል። የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ የብሪታኒያው አቻቸው ኪር ስትራመር፣ የብራዚል ፕሬዝደንት ሉላ ዳ ሲልቫ እና የቱርክ ፕሬዝደንት ራቺብ ጠይብ ኤርዶጋንን የመሳሰሉ መሪዎች ተገኝተዋል። የቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ዢን ፒንግ እና የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን በጉባኤው አልተገኙም።
ውዝግብ የፈጠረው ግን በሚጥቀለው ዓመት የጉባኤው ፕሬዝደንት የምትሆነው አሜሪካ አለመገኘቷ ብቻ ሳይሆን ከአዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ ጋር የገጠመችው እሰጥ አገባ ጭምር ነበር። ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በጉባኤው የማይገኙት በነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ላይ ይፈጸማል ባሉት የዘር መድሎ ምክንያት እንደሆነ አስታውቀው ነበር።
በነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ላይ የትራምፕ አስተዳደር ይፈጸማል ለሚለው “የዘር ማጥፋት” እስካሁን ተጨባጭ ማስረጃ ባያቀርብም የራማፎሳ መንግሥት ውንጀላውን አስተባብሏል። ትራምፕ ከዚህ በተጨማሪ ንግድ እና የአካባቢ ጥበቃን ጨምሮ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ከአሜሪካ ፖሊሲ ጋር ይጋጫል የሚል ሰበብ አቅርበው ነበር።
ትራምፕ ሐሳባቸውን ቀይረው ምክትል ፕሬዝደንት ጄድ ቫንስን ወደ ጁሐንስበርግ ይልካሉ ቢባልም የኋላ ኋላ ቢሯቸው ዋይት ሐውስ “ሐሰት” ሲል አስተባብሏል። ዩናይትድ ስቴትስ በጉባኤው እንደማትሳተፍ የተናገሩት የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት አሜሪካ የኤምባሲዋን ተወካይ የምትልከው አዘጋጅነቱን ለመረከብ ብቻ እንደሆነ ገልጸው ነበር።
“አምባሳደሩ ወይም በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው ኤምባሲ ተወካይ በስብሰባው የሚገኙት ዩናይትድ ስቴትስ [በሚቀጥለው ዓመት] የቡድን 20 አስተናጋጅ እንደምትሆን ለማረጋገጥ ብቻ ነው” ያሉት ካሮላይን ሌቪት “በስብሰባው መጨረሻ ላይ አስተናጋጅነቱን በይፋ ይረከባሉ” ብለው ነበር።
አሜሪካ ከታኅሳስ 28 ቀን 2018 ጀምሮ ተዘዋዋሪውን የቡድን 20 ፕሬዝደንትነት ትረከባለች። ጉባኤው በጎርጎሮሳዊው 2026 በፍሎሪዳ በሚገኝ የዶናልድ ትራምፕ የጎልፍ መጫወቻ ሥፍራ ይካሔዳል ተብሎ ይጠበቃል። ይሁንና በጁሐንስበርግ በተካሔደው ጉባኤ የፕሬዝደንትነት ርክክቡ ሳይፈጸም ቀርቷል። የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ቪንሰንት ማግዌኛ ሀገራቸው ኃላፊነቱን ለተራ የኤምባሲ ባለሥልጣን ለማስረከብ ፈቃደኛ እንዳልሆነች ተናግረዋል።
ሲሪል ራማፎሳ “የቡድን 20 ፕሬዝደንትነትን ለተራ የኤምባሲ ባለሥልጣን አያስረክቡም። በዚህ ሁኔታ ተቀባይነት የማያገኝ እና የማይፈቀድ የፕሮቶኮል ጥሰት ነው” ሲሉ በአጽንዖት ገልጸዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ከቡድን 20 ቀዳሚ ሐሳብ አመንጪዎች አንዷ መሆኗን ያስታወሱት ቪንሰንት ማግዌኛ “በቡድን 20 ያላትን ታሪካዊ አስተዋጽዖ እና የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ በመሆኗ ያለባትን ኃላፊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት አሜሪካ የተከተለችውን አቋም መምረጧ እና በጉባኤው ሳትሳተፍ መቅረቷ እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው” ሲሉ ነቅፈዋል።
የቡድን 20 ሀገራት መሪዎች የጋራ መግለጫ በሕግ ፊት አስገዳጅ አይደለም። የፕሬዝደንትነት ርክክቡም ቢሆን ተምሳሌታዊ ነው። ከፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባዮች አንዷ የሆኑት አና ኬሊ ግን ራማፎሳ “የቡድን 20 ፕሬዝደንትነት ሽግግር ሰላማዊ እንዳይሆን” አድርገዋል ሲሉ ከሰዋል።
ደቡብ አፍሪካ በርክክቡ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባይገኙ እንኳ በሚኒስትር ደረጃ አሊያም በሚወክሏቸው ከፍተኛ ባለሥልጣን በኩል ሊደረግ ይገባል የሚል አቋም ነበራት። ይሁንና በዚህ ሣምንት የሁለቱ ሀገራት ዝቅተኛ ባለሥልጣናት ተገናኝተው ርክክቡ ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል።
አሜሪካ ጉባኤውን ለማቃለል ተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳን ጨምሮ የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት ስኬታማ እንደነበር እርግጠኞች ናቸው። የአሜሪካ አካሔድ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የገባችበት እሰጥ አገባ ውጤት ብቻ ሳይሆን የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በሕግ ላይ የተመሠረተ በሚባለው ዓለም አቀፍ ሥርዓት ረገድ የሚከተለውን አቋም በድጋሚ ያንጸባረቀበት ጭምር ነበር።
በጉባኤው የታደሙ መሪዎች በቡድን 20 መሪነት ለተጫወተችው ሚና ደቡብ አፍሪካን አመስግነዋል። ራማፎሳን አቅፈው ምሥጋናቸውን የገለጹት የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ ጉባኤው ባለብዙ ወገን የዓለም ሥርዓት አሁንም ውጤታማ መሆኑ የታየበት እንደሆነ ቢያምኑም ልዩነቶች መኖራቸውን አልሸሸጉም።
የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርስ ዓለም “በአሁኑ ወቅት የአሰላለፍ ለውጥ እያደረገች፤ እዚህ አዳዲስ ግንኙነቶች እየተፈጠሩ እና ዩናይትድ ስቴትስ የምትጫወተው ሚና ትንሽ እንደሆነ” በጁሐንስበርግ ታዝበዋል። “የአሜሪካ መንግሥት ከዚህ ለመቅረት ያሳለፈው ውሳኔ ጥሩ ነው ብዬ አላስብም” ያሉት መራኄ መንግሥት ሜርስ “በዚህ መገኘታችን ግን ለእኛ ጥሩ ነበር” ሲሉ አስገንዝበዋል።
አሜሪካ ብትቀርም በጉባኤው የተሳተፉ ሀገራት በሕዝብ ቁጥር፣ በኢኮኖሚ እና በንግድ ከፍ ያለ ድርሻ ያላቸው መሆኑን የገለጹት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኔይ “የዓለም ኢኮኖሚ የስበት ማዕከል እየተለወጠ መሆኑን የሚያስታውስ” እንደሆነ ተናግረዋል።
የዓመቱ የተባበሩት የከባቢ አየር ስብሰባ አስተናጋጅ የነበረችው የብራዚል ፕሬዝደንት ሉላ ዳ ሲልቫ በበኩላቸው ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸውን ከተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት እና ከዓለም የንግድ ድርጅት ማስወጣታቸውን አስታውሰው “ባለብዙ ወገን የዓለም ሥርዓት (multilateralism) በተግባር ማብቃቱን እየሰበኩ የአንድ ወገን የበላይነትን ለማጠናከር እየሞከሩ ነው” ሲሉ ተችተዋል።
ሉላ “እኔ ግን ባለብዙ ወገን የዓለም ሥርዓት እንደሚያሸንፍ አምናለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ደቡብ አፍሪካ በአዘጋጅነቷ ከጋበዘቻቸው መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለደሐ ሀገሮች የሚሰጥን የዕዳ እፎይታ ወደ ጠቃሚ ኢንቨስትመንት መለወጥ አስፈላጊ እንደሆነ በአጽንዖት ተናግረዋል። የናሚቢያው ፕሬዝደንት ኔቱምቦ ናንዲ ንዳይትዋህ በበኩላቸው በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ሲበደሩ የሚከፍሉት ወለድ ፍትሐዊ ሊሆን እንደሚገባ ወትውተዋል።
ደሀዎቹ ሀገራት በጉባኤው ለከባቢ አየር ለውጥ ዳፋዎች እና በዕዳ ጉዳይ መፍትሔ የመጠየቃቸውን ያክል በማዕድን እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች አጋር ለመሆን አለን ያሉትን አቅም ለታዳሚዎቹ ነግረዋል። የዕዳ ጫና በሉዋንዳ በተከፈተው የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት ጉባኤ መነጋገሪያ ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል።
በቡድን 20 የጁሐንስበርግ ጉባኤ የታደሙት የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርሱላ ፎን ዴር ላየን እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ማሕሙድ አሊ ይሱፍ በሰባተኛው የሁለቱ አኅጉራዊ ተቋማት ስብሰባ ተገኝተዋል። ለሁለት ቀናት በሚካሔደው ስብሰባ በሰላም፣ ጸጥታ፣ አስተዳደር እና ባለ ብዙ ወገን የዓለም ሥርዓት ረገድ ትብብራቸውን በሚያጠናክሩበት ስልት ላይ ይነጋገራሉ። ለአውሮፓ ዋንኛ ጉዳይ የሆነው ፍልሰት ሌላው የሉዋንዳ ጉባኤ አጀንዳ ነው።
የአፍሪካ መንግሥታት ዕዳ፣ የከባቢ አየር ለውጥ እና ዓለም አቀፍ አስተዳደርን በመሳሰሉ ዘርፎች ለሚሿቸው ለውጦች የአውሮፓ ኅብረት ቁልፍ የዲፕሎማሲ አጋራቸው ሆኖ ቆይቷል። ኅብረቱ ለአፍሪካ ሸቀጦች ዋንኛ ገበያ ከመሆን በተጨማሪ ኢንቨስትመንት፣ የልማት ርዳታ እና ቴክኖሎጂ የሚያገኙበትም ነው። አውሮፓውያኑ በፊናቸው በዓለም ተፈላጊ የሆኑ ማዕድናትን ከእጃቸው ለማስገባት ዐይናቸውን እንደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ጥለዋል።
አርታዒ ነጋሽ መሐመድ