የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ 44 ኢትዮጵያውያን አዘዋዋሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም ከተባሉ ግለሰቦች ታደገ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 23 2017
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በጁሐንበርግ ከተማ ያለ ፈቃዳቸው የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም በተባሉ ግለሰቦች ተይዘው ነበር ያላቸውን 44 ኢትዮጵያውያን መታደጉን አስታወቀ። ከኢትዮጵያውያኑ መካከል 17 ታዳጊዎች ይገኙበታል።
ሳንድተን ተብሎ በሚጠራው የጁሐንስበርግ ሰሜናዊ ክፍል ፖሊሶች ለቁጥጥር በሚዘዋወሩበት ወቅት ከአንድ ቤት ውስጥ በሰሙት ጩኸት ኢትዮጵያውኑ መገኘታቸውን ሉቴናንት ኮሎኔል ማቬላ ማሶንዶ የተባሉ የፖሊስ መኮንን ተናግረዋል።
“በክፍሎች ውስጥ ተዘግቶባቸው የነበሩ 44 ሕገ ወጥ ስደተኞች አግኝተናል” ሲሉ ሉቴናንት ኮሎኔል ማቬላ ማሶንዶ ኒውስሩም አፍሪካ ለተባለ የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል። የፖሊስ መኮንኑ እንዳሉት በክፍሎች ውስጥ ተቆልፎባቸው ከተገኙ ኢትዮጵያውያን መካከል 17 ታዳጊዎች ናቸው።
“ከእነሱ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሚረዳን አስተርጓሚ እየጠበቅን ነው” በማለት የፖሊስ መኮንኑ አክለዋል። የተሻለ ኑሮ እና ገቢ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን በተለይ ወጣቶች ለስደት ከሚመርጧቸው ሀገራት አንዷ ደቡብ አፍሪካ ናት።
ኢትዮጵያኑ በተለይ መደበኛ ባልሆነ የስደት መስመር ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲያቀኑ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ማላዊ እና ሞዛምቢክን የመሳሰሉ ሀገራት በማቋረጥ ነው። በጉዞው በርካታ ወጣቶች ለሞት እና ለእንግልት ይዳረጋሉ። ደቡብ አፍሪካ ከደረሱ በኋላ ሕጋዊ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ ማግኘት ይፈትናቸዋል።
ባለፈው መጋቢት ያለ ፈቃዳቸው ተይዘው ነበር የተባሉ በርካታ ወጣት እና ሕጻናት ኢትዮጵያውያን ከጁሐንስበርግ ከተማ ወጣ ባለ አካባቢ ከሚገኝ መኖሪያ ቤት አምልጠው ነበር። የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ካመለጡት መካከል 32 ኢትዮጵያውያን ማግኘቱን አስታውቋል።
በጥር ወር በዚያው በጁሐንስበርግ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም በተባሉ ግለሰቦች ተይዘው የነበሩ 26 የመኖሪያ ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ራቁታቸውን በፖሊስ እንደተገኙ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ከ80 በላይ ኢትዮጵያውያን ኢ ሰብአዊ በሆነ አኳኋን በጁሐንስበርግ ዳርቻ በሚገኝ ሌላ መኖሪያ ቤት በነሐሴ 2016 ተቆልፎባቸው ተገኝተዋል።
አርታኢ ፀሀይ ጫኔ