1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ወሎ «ቱርክ» መጠለያ ጣቢያ ያሉ ተፈናቃዮች አቤቱታ

ሰኞ፣ ግንቦት 5 2016

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ በተለምዶ «ቱርክ» እየተባለ በሚጠራው የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ባለፈው ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ ም በከፍተኛ ዝናብ መኖሪያ ድንኳናቸው የፈረሰባቸው ተፈናቃዮች እስካሁን የተደረገላቸው ድጋፍ እንደሌለ ተናገሩ።

ተፈናቃዮች በአማራ ክልል ፣ ፎቶ ከማኅደር
ተፈናቃዮች በአማራ ክልል ፤ ፎቶ ከማኅደርምስል Alemnew Mekonen/DW

የደቡብ ወሎ «ቱርክ» መጠለያ ጣቢያ ያሉ ተፈናቃዮች አቤቱታ

This browser does not support the audio element.

 የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የመጠለያ ድንኳን ድጋፍ ለማድረግ ተሞክሮ በፀጥታ ምክንያት ወደቦታው መድረስ አልተቻለም ብሏል። የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መርሐ ግብሮች ማስተባበሪያ ኮሚሽን በበኩሉ የእርዳታ እህል ከማዕከል እየተላከ እንደሆነ አመልክቷል።

ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ ም ምሽት በደቡብ ወሎ ዞን  በተለምዶ «ቱርክ» እየተባለ በሚጠራው የተፈናቃዮች መጠለያ አካባቢ የጣለው ከባድ ዝናብ የብዙዎቹን መጠለያ ድንኳን በማፈራረሱ ተፈናቃዮች ለችግር መዳረጋቸውን ይናገራሉ። በወቅቱ የዞኑ አደጋ መከላከል የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት የተጎዳውን አካባቢ ጎብኝተው የሄዱ ቢሆንም እስካሁን ድጋፍ አላገኘንም ይላሉ። «የተቀዳደደውን ልብሳችንን ወጣጥረን በየታዛው ተቀምጠናል፣ ሚያዝያ 23 ቀን በከባድ ዝናብ መኖሪያችን ጉዳት እንደደረሰበት በነጋታው የአደጋ መከላከል ሰዎች ጎብኝተውናል። ግን እስካሁን የመጣልን ነገር የለም፣ 12 ቀናት አልፎናል። የነበሩን የምግብ እህሎቻችንም በዝናቡ ተጎድቷ፣ የምግብ እርዳታ ካገኘንም ወር አልፎናል፣ ተቸጋግረን ነው የተቀመጥን።»

ከወለዱ 45 ቀናት የሆናቸው አንዲት እናት የድንኳናቸው መፍረስ ለእርሳቸውም ሆነ አዲስ ለተወለደው ሕጻን ከባድ እንደሆነባቸው አመልክተዋል።

«ቀን በሙቀት፣ ሌት በብርድ ሜዳ ላይ ወድቀን ነው ያለነው። ምግብም ወሩን ጠብቆ እየመጣልን አይደለም። የማይመቺ ቦታ ላይ ነው ያለነው፣ ... የተወለደው ሕጻን ፀሐይም ነፋስም የፀሐይ ብርሃንም አልቻለም፣ ቆዳው እየተላላጠ ነው። ሕጻኑም ያለቅሳል፣ እኔም እንደዚያው ነብሰ ጡሮችም ተቸግረዋል።» ነው ያሉት።

አስተያየት ሰጪዎቹ ወደከተሞች ወጥቶ የቀን ሥራ ለመሥራት ቢታሰብም የመጠለያ ጣቢያው ከከተሞች በእጅጉ በመራቁ ያንን ማድረግ እንዳልቻሉ ነው የሚገልጡት።

የደቡብ ወሎ ዞን የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሊ ሰኢድ በከባድ ዝናብ ጉዳት የደረሰበትን የተፈናቃዮች መጠለያ አንድ የተዋቀረ ቡድን አጥንቶ መመለሱንና አንድ ግብረ ሠናይ ድርጅት ድጋፍ ለማድረግ ከተዘጋጀ በኋላ «የፀጥታ ስጋት አለብኝ» በማለቱ ለጊዜው ድጋፉ ባይደርስም፣ ጥረቱ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የመጠለያ ጣቢያው ከከተማ መራቁና ለማኅበራዊ አገልግሎት አመቺ አይደለም የሚለውን ቅሬታ በተመለከተ ደግሞ ተፈናቃዮች ወደየመጡበት መመለስ በመጀመራቸው በሂደት ሽግሽግ እንደሚደረግ አስረድተዋል። እስካሁንም 175 ተፈናቃዮች ወደነበሩበት የኦሮሚያ ክልል መመለሳቸውንም አስረድተዋል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መርሐ ግብሮች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል የእርዳታ እህል በእርግጥ መዘግየቱን አስታውሰው፣ አሁን ለሁሉም ተፈናቃዮች 1 ሚሊዮን 9 መቶ ሺህ ኩንታል አህል ከማዕከል እየተጓጓዘ መሆኑን አመልክተዋል።  ለደቡብ ወሎ ተፈናቃዮችም ወደ 146 ሺህ ኩንታል የምግብ እህል እንደተመደበላቸው ተናግረዋል። ሂደቱን የሚከታተል ባለሙያም ወደ አዲስ አበባ መላኩን ጠቁመው እርዳታ ወደሚከፋፈሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ በኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር የሚመራ ቡድን መሄዱን ገልጠዋል።

በዝናብ መኖሪያ ድንኳናቸው ለተጎዳባቸው ተፈናቃዮችም ከአካባቢው ማኅበረሰብና ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ይሠራላቸዋል ነው ያሉት ዲያቆን ተስፋሁን።

በተለያዩ አካባቢዎች በዋናነት በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተከስተው በነበሩ ግጭቶች 622 ሺህ ወገኖች ከቀያቸው ተፈናቅለው በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመጠለያና ከማኅበረሰቡ ጋር እንደሚኖሩ መዘገባችን ይታወሳል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW