1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ጉዞ ተግዳሮቶች እና መፍትሄዎች

ረቡዕ፣ የካቲት 27 2016

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እቅድ ከ5 ዓመታት በፊት ይፋ የተደረገ ዕቅድ ሲሆን፤ የበይነመረብ አገልግሎትን እንደ መሳሪያ በመጠቀም የዜጎችን የዲጅታል ቴክኖሎጂ አቅም የማጎልበት እና በ2025 አካታች የሆነ ዲጅታል ኢኮኖሚን የመገንባት ዓላማ ያለው መሆኑን የዚህ ዕቅድ ሰነድ ያሳያል።

የኢትዮጵያ የዲጅታል ቴክኖሎጅ ዕቅዷን ለማሳካት በርካታ ተግዳሮቶች አሉባት
የኢትዮጵያ የዲጅታል ቴክኖሎጅ ዕቅዷን ለማሳካት በርካታ ተግዳሮቶች አሉባት ምስል Steinach/IMAGO

የበይነመረብ መዘጋት እና የኤለክትሪክ መቆራረጥ ከተግዳሮቶቹ መካከል ናቸው

This browser does not support the audio element.


በኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት ባለፈው ሳምንት በተለያዩ መርሀግብሮች የዶጂታል ሳምንት ተከሂዷል። ይህ መርሀ ግብር  በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጄ ነው። ይህንን መነሻ በማድረግ የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት  ከ5 ዓመታት በፊት ይፋ በሆነው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ተግዳሮቶች እና መፍትሄዎች ላይ ፍተሻ አድርጓል።
በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ያተኮረ  የዲጂታል  ሳምንት ከየካቲት 18  እስከ  የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ/ም በተለያዩ መርሀ ግብሮች ተካሂዷል። በኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት የተካሄደው እና ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጄው ይህ የዲጂታል  ሳምንት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብሮች እንደነበሩት የመርሀ ግብሩ አስተባባሪ አቶ ቲዎድሮስ ታዘዘ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጅ ሚንስትር የአንድ ሳምንት የዱጅታል ግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ አዘጋጅቷል።

አስተባባሪው እንደገለፁት መርሀ ግብሩ የተካሄደው የዲጅታል ግንዛቤ አስፈላጊነትን ታሳቢ በማድረግ ነው። አንድ ሳምንት በዘለቀው በዚህ መርሀ ግብር የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ጉዞ  ለውይይት ከቀረቡ ጉዳዮች መካከል ነው።
የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግንዛቤን ማሳደግ ኢትዮጵያ ከ5 ዓመታት በፊት ይፋ ካደረገችው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጅን ለማሳካት ከሚረዱ መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ ነው። ይህ ስልት የበይነመረብ አገልግሎትን እንደ መሳሪያ በመጠቀም የዜጎችን የዲጅታል ቴክኖሎጂ አቅም የማጎልበት እና በ2025 አካታች የሆነ ዲጅታል ኢኮኖሚን የመገንባት ዓላማ እንዳለው የዚህ ዕቅድ ሰነድ ያሳያል። በአማራ ክልል የኢንተርኔት መቋረጥ በባንክ አገልግሎት፣ በግብረ ሰናይ እና የምርምር ሥራዎች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ
ያም ሆኖ የኢንተርኔት አገልግሎት ውስንነት እና የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ፣ የሀይል አቅርቦት እጥረት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀት ማነስ እና ቴክኖሎጂን ገዝቶ ለመጠቀም የኢኮኖሚ አቅም አነስተኛ መሆን አሁንም በሀገሪቱ ውስጥ ያልተፈቱ ችግሮች ናቸው።
በግላቸው በሶፍትዌር ልማት ላይ የተሰማሩት እና የሶፍትዌር መሀንዲስ የሆኑት አቶ ይግረማቸው እሸቴ ይህ ዕቅድ ከ5 ዓመት በፊት ይፋ ሲሆን አራት መሰረታዊ ምሰሶዎች እንደነበሩት ያስታውሳሉ።የመጀመሪያው የቴሌኮም ግንኙነትን እና የሀይል አቅርቦትን የሚያጠቃልለው የመሰረተ ልማት ግንባታ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

አቶ ይግረማቸው እሸቴ ፤የሶፍትዌር መሀንዲስምስል Privat

በይነመረብ አገልግሎትን በተመለከተ ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ተደራሽነቱ 30 በመቶ መድረሱ አወንታዊ ቢሆንም በግጭቶች ሳቢያ በየጊዜው የሚደረገው የበይነመረብ መዘጋት እንዲሁም  የጥራት ጉድለት አሁንም ፈተናዎች ናቸው። 
ለዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ሁለተኛው መሰረታዊ ጉዳይ የዲጂታል አስቻይ ሁኔታ መኖር ነው:: ይህንን ለመፍጠርም  የዲጂታል መታወቂያ ፣የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት እና ዲጅታል  ደኀንነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ነገሮች ናቸው። ከዚህ አንፃር  ጅምሮች እንዳሉ የገለጹት ባለሙያው ነገር ግን ውስኑነቶች አሏቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚዘጋው፣ የሚገደበው ኢንተርኔት እና ያስከተለው ኪሳራ
ከሳይበር ደህንነት አንጻርም ምንም እንኳ በግለሰብ ደረጃ ችግሮች ቢኖሩም በተቋም ደረጃ ያን ያህል ስጋት አለመታየቱን አብራርተዋል።
ሌላው በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ዲጂታል መስተጋብር  /ዲጂታል ኢንተራክሽን/ ሲሆን፤ እንደ ባለሙያው ገለፃ ለዘርፉ መሰረት የሆኑት የዲጂታል ገበያ  እና የክፍያ ሥርዓቶች እንዲመቻቹና በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ፈጣን እንዲሆን ዲጅታል መስተጋብር ላይ ሊሰሩ የሚገባቸው በርካታ ሥራዎች አሉ።አሳሳቢው የኦንላይን ባንክ ዘረፋ

አራተኛው እና የመጨረሻው የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025  ዕቅድ መሰረታዊ ነገር  የዲጂታል ሥነ-ምህዳር /የዲጂታል ኢኮሲስተምን/ ማልማት ነው። ለዚህም ሰዎች በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ አገልግሎቱን ለማግኘትም  ሆነ ለመስጠት የዲጂታል ክህሎት ሊኖራቸው ይገባል።የሶፍትዌር መሀንዲሱ አቶ ይግረማቸው እንደሚሉት አሁን ያለው የዲጂታል ሥነ-ምህዳር የተበታተነ ፣አባካኝ እና የተወሳሰበ ነው ይሉታል።ለዚህም የገንዘብ ተቋማትን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። ክላውድ፤መረጃን ከመጥፋት የሚታደገው ቴክኖሎጂ

የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ፤የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ዕቅድ አንዱ ምሰሶ ነውምስል Monika Skolimowska/dpa/picture alliance

ከዚህ በተጨማሪ የዲጂታል ሥነ-ምህዳርን ለማዳበር  የውጭ የጥቃት ተጋላጭነትን የሚቀንስ የሀገር ውስጥ የባንክ አሰራር ስልትን መዘርጋት፣ የሰው ሀይልን ማብቃት እና ተጨማሪ ፖሊሲና መመሪያዎችን ማውጣትም  የዲጂታል ሥነ-ምህዳርን ለማልማት አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዲጅታል 2025 ዕቅድ የምታደርገው  ዲጂታል ጉዞ የተወሰኑ ለውጦች የታዩበት ቢሆንም፤ ከላይ ከተጠቀሱት ተግዳሮቶች 
በተጨማሪ በተቋማት  የመሰረተ ልማት ዝርጋታ አነስተኛ መሆን፣በየተቋማቱ ያሉ ሰራተኞችም የዲጅታል ቴክኖሎጂ ግንዛቤ ደካማ መሆን ብዙ ሥራ የሚፈልግ ነው። በመሆኑም የሰው ሀይልን ለማብቃት ስልጠናዎችን መስጠት፣ተማሪዎች ከታች ጀምሮ  የቴክኖሎጅ እውቀት እንዲኖራቸው በመስራት የዲጅታል እውቀትን ማስፋፋት ፣ የሀገር ውስጥ ፈጠራዎችን ማበረታታት እና በገንዘብ መደገፍ እንዲሁም  የዲጅታል ቴክኖሎጅ መሳሪያዎችን  በአነስተኛ ዋጋ ማቅረብ ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ ከሚያግዙ ነገሮች  መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸውን ባለሙያው አስረድተዋል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW