1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹት የዳሰነች ተፈናቃዮች

ሰኞ፣ ኅዳር 17 2016

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በኦሞ ወንዝ ሙላት የተፈናቀሉ ከ79 ሺህ በላይ ነዋሪዎች “ የዕለት ደራሽ የምግብ ድጋፍ ባለማግኘታችን ተቸገርን “ አሉ ፡፡ ነዋሪዎቹ በጎርፍ ሙላት ከተፈናቀሉ ከአንድ ወር በላይ ቢያስቆጥሩም አስከአሁን የምግብ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ለረሀብ መዳረጋቸውን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹት የዳሰነች ተፈናቃዮች- የኦሞ ወንዝ ሙላት አደጋ
አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹት የዳሰነች ተፈናቃዮች- የኦሞ ወንዝ ሙላት አደጋ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ከ79 ሺህ በላይ ነዋሪዎች “ የዕለት ደራሽ የምግብ ድጋፍ ባለማግኘታችን ተቸገርን “ አሉ

This browser does not support the audio element.

አርብቶ አደር ሀራ ሜሪ እና ተስፋዬ ዶቻ በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የለበት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው  ፡፡ ሀራ እና ተስፋዬ እንደሚሉት  የኦሞ ወንዝ ለወትሮው ቀበሌያቸውን በዝምታ አቋርጦ ያልፍ ነበር ፡፡ ከባለፈው የጥቅምት ወር አጋማሽ ወዲህ ግን ወንዙ ግራ እና ቀኝ ሞልቶ መፍሰስ ጀመረ ይላሉ ፡፡ አሁን ላይም  ወደ መንደራቸው መሰስ ብሎ በመግባት የመኖሪያ ቤቶችንና የመሠረተ ልማቶችን ውጦ እንደሚገኝ ነው ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ፡፡ መንደራቸው በኦሞ ወንዝ መጥለቅለቁን ተከትሎ ወደ ደረቃማ ቀበሌያት በመሸሽ በዚያው ሠፍረው እንደሚገኙ የለበት ቀበሌ ተፈናቃዮቹ ይናገራሉ ፡፡

የተጋረጠው የረሀብ አደጋ

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አሁን ላይ በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በኦሞ ወንዝ ሙላት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ቁጥር ከ79 ሺህ በላይ ነው ፡፡ የወንዙ ሙላት ካጥለቀለቃቸው 39 ቀበሌያት መካከል የለበት ቀበሌ ነዋሪዎቹ አርብቶ አደር  ሀራ ሜሪ እና ተስፋዬ ዶቻ ይገኙበታል ፡፡  ሀራ እና ተስፋዬ ከመንደራቸው ተፈናቅለው ከወጡ ጀምሮ ምንም አይነት የምግብ ድጋፍ ባለማግኘታቸው አሁን ላይ  በረሀብ እየተጎዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ “ የነበረን እህል በሙሉ በወንዝ ሙላቱ ተውስዶብናል “ የሚሉት አርብቶአደሮቹ “ አሁን ላይ ቤተሰቦቻችንን የምናበላው ነገር በእጃችን የለም ፡፡ ይቀርብላችኋል የተባለው ድጋፍም እኛ ጋር አልደረሰም ፡፡ በዚህም የተነሳ በተለይ ህጻናትና ሐረጋዊያን በምግብ እጦቱ እየተራቡ ሰውነታቸውም እየተጎሳቆለ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

እጅ ያጠረው የምግብ ድጋፍ አቅርቦት 

ከኦሞ ወንዝ በተነሳዉ ጎርፍ ከ15 ሺህ በላይ ሰዉ ተፈናቀለ

ዶቼ ቬለ  የተፈናቃዮቹን አቤቱታ አስመልክቶ  ያነጋገራቸው  የደቡብ ኦሞ ዞን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር መምሪያ ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ ናንጎዲዮ የተፈናቃዮቹን ቅሬታ ተገቢ  ብለውታል ፡፡ ለተፈናቃቹ የዕለት ደራሽ ድጋፎችን የማቅረብ ጥረት መኖሩን የጠቀሱት አቶ  ኤርሚያስ  “ አሁን ላይ 79 ሺህ ተፈናቃዮች በእጃችን ይገኛሉ ፡፡ አስከአሁን 1 ሺህ 137 ኩንታል የቦቆሎ ዱቄት ፤ የሸራ ድንኳኖችን ጨምሮ የተለያዩ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች አቅርበናል ፡፡ ነገር ግን ይህ በቂ ነው ማለት አይደለም ፡፡ ባለው የአቅርቦት እጥረት የተነሳ ከጠቅላላ ድጋፍ ፈላጊው መድረስ የተቻለው ግማሽ ያህሉን ብቻ ነው “ ብለዋል ፡፡

አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹት የዳሰነች ተፈናቃዮች- የኦሞ ወንዝ ሙላት አደጋ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የድጋፍ ጥሪ ለለጋሾች 

በደቡብ ከ62 ሺህ በላይ ሰዎች በወንዝ ሙላት ተፈናቀሉ 

ዶቼ ቬለ  አጋጥሟል በተባለው አስቸኳይ ምግብ ድጋፍ አቅርቦት እጥረት ዙሪያ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ቢሮ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ሃላፊዎቹን ማግኘት ባለመቻሉ ሊሳካ አልቻለም ፡፡ የደቡብ ኦሞ ዞን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር መምሪያ ሃላፊው ኤርሚያስ ናንጎዲዮ ግን የምግብ ድጋፍ እጥረቱን ለመቅረፍ ዞኑ ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ ነው የጠቀሱት ፡፡ እስከአሁን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ፣ ዎርልድ ቪዥን ፣ ፕላን ኢንተርናሽናል እና አይሪሽ ኤይድ በወረዳው ገብተው ድጋፍ ማድረግ ጀምረዋል ፡፡ ድርጅቶቹ የምግብ አቅርቦት ፣ የውሃ ተሸከርካሪ ቦቴዎችን  እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ እያገዙ ይገኛሉ ፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት በለገሠው 30 ሚሊዬን ብር የምግብ እህል ግዢ እየተደረገ ይገኛል ፡፡ ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶችም እጃቸውን እንዲዘረጉ እየጠየቅን እንገኛለን “ ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW