1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“የዳኞች እስራት አሳስቦኛል” የአማራ ዳኞች ማህበር

ዓለምነው መኮንን
ሐሙስ፣ ጥቅምት 14 2017

በአማራ ክልል በመንግስት ኃይሎች የሚደረግው ተከታታይ የዳኞች እስራት እንዳሳሰበው የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ገለጸ። ከመስከረም 26 ጀምሮ 13 ዳኞች መታሰራቸውን የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ብርሐኑ አሳሳ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ስለ ጉዳዩ ከመንግሥት በኩል ምላሽ ለማኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

የፍትኅ ምልክት
ከመስከረም 26 ጀምሮ 13 ዳኞች መታሰራቸውን የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ብርሐኑ አሳሳ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።ምስል alexlmx/Zoonar/picture alliance

“የዳኞች እስራት አሳስቦኛል” የአማራ ዳኞች ማህበር

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመንግሥት ኃይሎች እየተደረገ ያለው ተከታታይ የዳኞች እስራት በእጀጉ እንዳሳሰበው የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር አስታውቋል። ማህበሩ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ “ዳኞችን ያላግባብ ማሰርና ማዋከብ የተለመደ ተግባር ሆኗል” ብሏል። “ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል” ያለው የማህበሩ መግለጫ፣ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ በክልሉ ሁሉም ዞኖች 35 ዳኞች ታስረው መፈታታቸውን አመልክቷል።

ከመስከረም 26/2017 ዓም ጀምሮ ደግሞ እንደአዲስ የዳኞች እስራት መቀጠሉንና 13 ዳኞች መታሰራቸውን የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ብርሐኑ አሳሳ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

የእስሩ ሂደት “ህገወጥ ነው” የሚሉት አቶ ብርሐኑ፣ የታሰሩት ዳኞች የተጠረጠሩበት ወንጀል አይታወቅም ብለዋል፣ አንዳንዶችም የታሰሩባቸው ቦታዎች መደበኛ እንዳልሆኑ ገልጠዋል።

የዳኝነትን ነፃነት ባላማከለ ሁኔታ ዳኞቹ ከስራ ቦታቸው ከችሎት ላይ በፖሊስ መያዛቸውን የሚገልጹት አቶ ብርሐኑ፣ የታሰሩት ዳኞች እስካሁንም ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና አንዳንዶቹ ከመስከረም 26/2024 ጀምሮ “በማዕከል እስር ቤቶች ይገኛሉ ነው ያሉት።

በአማራ ክልል አሳሳቢው የነባር ዳኞች ስራ መልቀቅ

የእስሩ ሁኔታ አጠቃላይ የፍትህ ሥርዓቱን ነፃነት የሚጋፋና በሌሎች ዳኞች ሥራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትል እንደሚሆን ሥጋታቸውንአስቀምጠዋል።

በባሕር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ በባሕር ዳር ወረዳ ፍርድ ቤትና ፍትህ ጽ/ቤቶች የሚሰሩ ዳኞችና ጠበቆች መታሰራቸውን እንደሚያውቁ በአማራ ክልልና በፌደራል ደረጃ የግል ጠበቃና የህግ አማካሪ አቶ ገበያው ይታየው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Matyas/Pond5 Images/IMAGO

የዳኞች እስራት የፍትህ ሥርዓቱንችግር ውስጥ የሚጥል ነው

አቶ ብርሐኑ፣ “… እንደ ሥርዓት የእስር ሂደቱ  ‘የዳኝነት ሥርዓት የምንለውንችግር ውስጥ የሚጥል ነው። ችሎት ላይ እያሉ ‘ፖሊስ ትፈለጋላችሁ’ እያለ ወሰዳቸው በዚያው ታስረው ቀሩ፣ ይህ አብረው የሚሰሩ ዳኞችን ጨምሮ በፍርድ ቤቱ ተቋማዊ ነፃነት ላይ ሊፈጥረው የሚችለው ተፅዕኖ ይታወቃል፣ በክልሉ ያለ ዳኛ “በእኔ ላይ ምን ሊፈጠር ይችላል” በሚል ሥጋት ላይ ወድቋል።” ብለዋል።

በአማራ ክልልና በፌደራል ደረጃ የግ ልጠበቃና የህግ አማካሪ አቶ ገበያው ይታየው በበኩላቸው፣ ማነኛውም ሰው በወንጀል ከተጠረጠረ በመንግስት ሊታሰር እንደሚችል አመልክተው፣ ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ በአማራ ክልል በዳኞች ላይ እየተደረገ ያለውን የዳኞችን እስር ሂደት ግን ኮንነዋል።

«ከእርዳታ አውጡን» የአማራ ክልል ተፈናቃዮች

ከአንድ ዓመት ጀምሮ በዳኞች ላይ እስራትና ወከባዎች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ገበያው፣ በሰሜን ወሎ ዞን የነበረን እስር ለአብነት አንስተዋል። በባሕር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ በባሕር ዳር ወረዳ ፍርድ ቤትና ፍትህ ጽ/ቤቶች የሚሰሩ ዳኞችና ጠበቆች መታሰራቸውን እንደሚያውቁ ተናግረዋል።

ዶይቼ ቬለ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንገሻ ፋንታውን ጨምሮ ከተለያዩ ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ምስል Alemnew Mekonnen/DW

አንድ ሰው ወንጀል ከፈፀመ ሊጠየቅ እንደሚቻል ጠቅሰው አሁን እየተደረገ ያለው የዳኞች የእስር ሂደት ግን የዳኞችን ስብዕናና የዳኞችን ክብር ባልጠበቀ ሁኔታ ነው ብለዋል። በዳኞች ላይ እየተደረገ ያለው የዘፈቀደ የእስር ሂደት ቀሪ ዳኞች “ነገ በእኔ ላይ ምን ይመጣ ይሆን?” በሚል ከፍተኛ የሰነልቦና ጫና ውስጥ ሊከትታቸው እንደሚችል ሥጋታቸውን አስቀምጠዋል።

በሥራ ላይ ያሉ ዳኞችን ስነ ልቦና ይጎዳል

በሥራ ላይ ያሉ ዳኞች በጓደኞቻቸው ላይ የተፈፀመውን ድርጊት ሲመለከቱ በእነርሱ ላይ በቀጣይ ምን ሊመጣ እንደሚችል በመስጋት ሥራቸውን በአግባቡ አያስችላቸውም ነው ያሉት።ትልቅ ሥጋት ውስጥ ሊጥላቸው እንደሚችልም አቶ ገበያው ሥጋት እንዳላቸው ገልጠዋል።

በአማራ ክልል ከ600 ሺ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸው ተገለጸ

የዳኞችን እስራት በተመለክት ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ለአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንገሻ ፋንታው በድምፅና በአጭር የፅሁፍ መልዕክት በተደጋጋሚ ብንጠይቅም “ስብሰባ ላይ ነኝ” በሚል በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልሰዋል። ለክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ያደረግሁት የድምፅና የአጭር የፅሁፍ መልዕክትም ምላሽ አላገኘም። በአካል ወደ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ብንሄድም “ቢሮው በአድሳት ላይ ነው” በመባሉ ዘልቀን መግባት አልቻልንም።

ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW