1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ ለማሳደግ ምክክር ተደረገ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 21 2011

ደቡብ ኮሪያ እና እስራኤልን ጨምሮ በመላው አውሮፓ ከ 16 ሚስዮኖች የተውጣጡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደሮች እና የዲያስፖራ ተሳትፎ ኃላፊዎች በፍራንክፈርት ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ባለፈው ሳምንት ውይይት አካሂደዋል። ውይይቱ በዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲው አተገባበር ላይ ያተኮረ ነበር። 

Mulu Solomon - Botschafter der Demokratischen Republik Äthiopien in Deutschland
ምስል DW/E. Fekade

የዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ ለማሳደግ ምክክር ተደረገ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እና ሌሎችም የኤጀንሲው ሃላፊዎች ከአዲስ አበባ በክብር እንግድነት በተካፈሉበት በዚሁ የውይይት መድረክ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በሀገራቸው ጉዳይ ያለምንም ልዩነት በንቃት ለማሳተፍና ተጠቃሚ ለማድረግ ብሎም መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር በሚቻልበት የአተገባበር ስልት ዙሪያ መክረዋል። 

በሁለት ቀናቱ ጉባኤ በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አምባሳደሮች በየሶስት ወሩ እየተገናኙ የዲያስፖራውን አገራዊ ተሳትፎ ለማጎልበት እና የኤጀንሲው የስራ አፈጻጸም ሂደት በጋራ ለመገምገም እንዲረዳቸው አራት የተለያዩ የመገናኛ ማዕከላት መቋቋማቸውንም በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ጄኔራል አቶ ፈቃደ በየነ ዶይቼ ቬሌ (DW) ገልጸዋል። 

እነዚህ የመገናኛ ማዕከላት ለሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ ዱባይ እንደዚሁም ለአፍሪቃ አህጉር ደቡብ አፍሪቃ ናቸው። ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ያካሄዱትን ሕዝባዊ ጉባኤ ያስተናገደችው የፍራንክፈርት ከተማ ደግሞ በመላው አውሮጳ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደሮች የመገናኛ ማዕከል ሆና መመረጧ ይፋ ተደርጓል።

በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ወይዘሮ ሙሉ ሰለሞን እና የዲያስፖራ ተሳትፎ ሃላፊዎች በፍራንክፈርት እና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና የተለያዩ አደረጃጀቶች ተወካዮች ጋር በፍራንክፈርት ቆንጵላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ቀጣይ ውይይት አካሂደዋል። በውይይት መድረኩ ላይም በኢትዮጵያ ስላለው ለውጥ እና ተግዳሮቶቹ እንዲሁም የዲያስፖራ ኤጀንሲ ስለተቋቋመበት ዓላማ እና የትኩረት መስኮች ሰፊ ገለጻ እና ውይይት ተካሄዷል። 

አምባሳደር ሙሉ ዲያስፖራው በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገር ልማት እና ግንባታ የበኩሉን ሚና እንዲያበረክት  ጥሪ አስተላልፈዋል። " ከአሁን ቀደም በተፈጠሩ ቅሬታዎች ምክንያት ከመቆዘምና ከመራቅ ይልቅ አሁን ከለውጡ ጋር በአዲስ መንፈስ የነበሩ ቅሬታዎችን በማረም ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲያዊ አሰራሮች በኤምባሲዎቻችን ተግባራዊ በመሆናቸው ዲያስፖራው በአሰራር የሚገጥሙት ቅሬታዎችን በማናቸውም ጊዜ በግልጽ እንዲጠይቅ እና በባለቤትነት መንፈስ የጋራ ተሳትፎም እንዲያደርግ ነው በዚህ አጋጣሚ መልዕክት ማስተላለፍ የምንፈልገው " ብለዋል አምባሳደሯ።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የዕውቀት፣ የሙያ እና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለኢትዮጵያ እንዲያበረክቱ እንዲሁም አገር ውስጥ ገብተው መስራት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸትን ጨምሮ ልዩ ልዩ አሳታፊ ተግባራትን ኤጀንሲው እንደሚያከናውንም ነው በቅዳሜው የፍራንክፈርቱ የውይይት መድረክ ላይ የተወሳው። የዲያስፖራ ተሳትፎ ሃላፊዎችም በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የዲያስፖራው ሚና የማይናቅ መሆኑን በማስታወስ መብት እና ጥቅሙ እንዲከበር ከመታገል ጎን ለጎን ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።  

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት "ዲያስፖራው በአገር ኢኮኖሚ ግንባታ በሰው ኃይል በስራ ዕድል ፈጠራ በልማት እና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ለውጥ ለማስመዝገብ ትልቅ አቅም እንዳለው ይታወቃል። ይሁንና ከአሁን ቀደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲያስፖራውን በተመለከተ ይከተላቸው የነበሩ የአሰራር ሥልቶች የጉዳዩን ባለቤት በተገቢው መልኩ የሚያሳትፉ አልነበሩም። አሁን ግን ኤጀንሲው ከተቋቋመ በኋላ በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻችን፣ ያለ ልዩነት፣ በማንኛውም አገራዊ እንቅስቃሴ በባለቤትነት መንፈስ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበትን ገለልተኛ የሆነ አደረጃጀት ለመገንባት ጠንክሮ የሚሰራ ይሆናል። በውጭ ካሉ ማህበራት እና የዲያስፖራ አደረጃጀቶችም ጋር የሚኖረንን ትሥሥር የምናጠናክረው ይሆናል"  ሲሉ በፌደራል መንግሥቱ ስር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ከሚያከናውናቸው ፈርጀ ብዙ ተግባራት መካከል የተወሰነውን ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን አገራዊ ተሳትፎ ይበልጥ ለማጠናከር ተጠሪነቱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሆነ የዲያስፖራ ኤጀንሲ ያቋቋመ ሲሆን መተዳደሪያ ደንቡም በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክርቤት መጽደቁ ይታወሳል። ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ አሃዝ በሚሊዮኖች የሚገመት መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ በቅድሚያ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ይህንኑ ቁጥር በውል ማረጋገጥን ጨምሮ አጠቃላይ የዲያስፖራውን መረጃ ማሰባሰብ እንደሚሆን ታውቋል። በዓለም ዙሪያ ከ 3 ሚልዮን የሚልቁ ኢትዮጵያውያን በውጭ አገራት እንደሚኖሩ ሲገመት ዓለማቀፉ የጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት በአንድ ጥናቱ እንዳመለከተው ዛሬ በመላው ጀርመን ኑሮዋቸውን የመሰረቱ ከ 19ሺህ የሚልቁ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ። 

ዶይቼ ቬሌ (DW) ያነጋገራቸው አንዳንድ የውይይቱ ተሳታፊዎች ከአሁን ቀደም በኢትዮጵያ መንግሥት ይፈጽማቸው የነበሩ የተለያዩ የሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶች በመቃወማቸው ምክንያት ከባድ ተጽዕኖ በኤምባሲዎች አካባቢ ሲፈጸምባቸው መቆየቱን ገልጸዋል። ከእነዚህም መካከል በፍራንክፈርት እና አካባቢው የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ማህበር ዋና ጸሃፊ አቶ ማሞ ይሁኔ ይገኙበታል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው ዜጎችን የማፈናቅል እና የብሄር ግጭት በተመለከተ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መፍትሄ ሊያበጅለት ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። 

እንዳልካቸው ፈቃደ

ተስፋለም ወልደየስ 

እሸቴ በቀለ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW