1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ ግጭት መባባስ ያስከተለው ስጋት

ቅዳሜ፣ ሰኔ 29 2016

«መንግሥት በኤም 23 የተያዙትን ግዛቶች ለማስመለስ ምንም ሲያደርግ አናይም።ለምሳሌ ቡናጋና በኤም 23 እጅ ከገባች ወደ ሁለት ዓመት ይሆናታል። ብዙዎች መንግሥት ኪሩምባን መልሶ መቆጣጠሩ ቀላል አይሆንለትም ይላሉ።እንደ አነስተኛ ቡድን የተነሳው የኤም 23 ቡድን ከአቅም በላይ እንደሆነ ነው የምናየው። በዚህ የተነሳም ህዝቡ ተጨንቋል።»የኪሩምባ ነዋሪ

DR Kongo | Armee auf Patrouille in Goma, Provinz Nord-Kivu
ምስል Wang Guansen/Xinhua/picture alliance

የዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ ግጭት መባባስ ያስከተለው ስጋት

This browser does not support the audio element.

የዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚካሄደው ግጭት መባባስ ያስከተለው ስጋት

ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚካሄደው ግጭት ሰሞኑን ተባብሶ ቀጥሏል። ይህም ያስከተለው መጠነ ሰፊ የህዝቦች መፈናቀል በእጅጉ አሳስቧል። በተለይ የሰሜን ኪቩ ክፍለ ሃገር ሰብዓዊ ይዞታው አስግቷል።   ኤም 23 የሚባለው የኮንጎው አማጺ ቡድን ዋና ዋና ከተሞችን መያዙም አስፈርቷል።ባለፈው አርብና ቅዳሜ አማጽያኑ ምሥራቅ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኙትን የካንያባዮንጋ እና ኪሩምባ ከተሞችን በቅደም ተከተል ይዟል። እንደ ትሶንጎ አውጉስቲን ያሉ የኪሩምባ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት በግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች መኖሪያ ከነበረው ከኪሩምባ በየጊዜው በርካታ ሰዎች ከአካባቢው ለመውጣት እየተገደዱ ነው። ከዚህ ቀደም ከሩትሹሩ ተፈናቅለው የመጡ ሰዎችን ተቀብላ የነበረችው የከተማይቱ ነዋሪ ቁጥር ተመናምኗል። 

የአካባቢው ስልታዊ ጠቀሜታ 

ትልቋ የሉቤሮ ግዛት ከተማ ኪሩምባ ከ120 ሺህ በላይ ህዝብ መኖሪያ ነበረች።  
ካንያባዮንጋ ደግሞ ከ60 ሺህ በላይ ህዝብ ይገኝባታል። አማጽያኑ ወደ ከተማይቱ ሲገሰግሱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሸሽተዋል። በኪሳንጋኒ ዩኒቨርስቲ መምህርና የትጥቅ እንቅስቃሴዎች ምሁር  ፕሮፌሰር አጌኖንጋ እንዳሉት ክልሉ አማጽያን ወደ ሀገሪቱ ትልቁ ሰሜናዊ ግዛት እንዳይዘልቁ የሚያግድ እንደ ጠንካራ ስልታዊ ይዞታ የሚቆጠር ነው።
የተባባሰው ሰብዓዊው ቀውስና ጭንቀት የካንያባዮንጋ እና ኪሩምባ መያዝ በነበረው ከባድ ሰብዓዊ ሁኔታ ላይ ተጨማሪ ሰዎችን በብዛት አፈናቅሏል። እናም ጥያቄው እነዚህ ሁሉ ቤተሰቦች ወዴት ይሄዳሉ ነው? እንደ ፕሮፌሰር አጌኖንጋ
እንደ ሜማ ኬኔዲ ያሉ የኪሩምባ ነዋሪዎች በመሪዎቻቸው ተስፋ ቆርጠዋል። 
«መንግሥት በኤም 23 የተያዙትን ግዛቶች ለማስመለስ ምንም ሲያደርግ አናይም።ለምሳሌ ቡናጋና በኤም 23 እጅ ከገባች ወደ ሁለት ዓመት ይሆናታል። ብዙዎች መንግሥት ኪሩምባን መልሶ መቆጣጠሩ ቀላል አይሆንለትም ብለው ይፈራሉ። እንደ አነስተኛ ቡድን የተነሳው የኤም 23 ቡድን ከአቅም በላይ እንደሆነ ነው የምናየው። በዚህ የተነሳም ህዝቡ ተጨንቋል።»
በቅርቡ በሰሜን ኪቩ ግዛት በአንድ ወታደራዊ አጀብ ላይ የተጣለው ጥቃት የአካባቢውንና ከዛም ርቆ የሚገኙትን  የጸጥታ ችግርና ሰብዓዊውን ቀውስ  አባብሶታል። በቅርብ ጊዜው ጥቃት ሁለት የደቡብ አፍሪቃ ወታደሮች ሲገደሉ ሁለት የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም።  
 

ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚካሄደው ግጭት መባባስ ያስከተለው ስጋትምስል ALEXIS HUGUET/AFP

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዝምታ

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና የአፍሪቃ ኅብረት በቅርብ ጊዜያቱ የተባባሰ ውጥረት ላይ ዝምታን የመረጡ ይመስላል ይባላል። ፕሮፌሰር አዶልፌ አገኖንጋ ቾበር የትጥቅ እንቅስቃሴዎች አዋቂ እና የኪሳንጋኒ ዩኒቨርስቲ መምህር እንደሚሉት ግን ጥረቱ አለ ችግሩ ግን ከኪንሻሳ መንግሥት በኩል ነው። 
«ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና የአፍሪቃ ኅብረት በግጭቱ በሚሳተፉ ወገኖች መካከል ውይይት እንዲካሄድ እያበረታቱ ነው። ይህ ግን በኪንሻሳ መንግሥት በኩል ተቀባይነት አላገኘም።» 
ሆኖም ይህ ሁኔታውን በመቀየር የኤም 23ን ግስጋሴ ማስቆም ያስቻለ አይመስልም። ስለዚህ ይሉ ሌላው ምሁር ኤሪክ ባቶን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና የዓለም መሪዎች በኅብረት ለግጭቱ መፍትሄ ለማግኘት ጥረት በማድረግ በሚሊዮኖች የሚቆጠጠሩ ሴቶችና ህጻናት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱና የወደፊቱ ሕይወታቸውም ዋስትና እንዲኖረው ማድረግ ይገባቸዋል። 

የዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚካሄደው ግጭት መባባስ ያስከተለው ስጋትምስል ALEXIS HUGUET/AFP

በኮንጎ ወታደሮች ላይ የሚቀርብ ወቀሳ 

በሌላ በኩል የኮንጎ ጦር ኃይል ብቃት ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ጥቃቱ ሲባባስ የወታደሮቹ ቸልተኝነት እና ውጤታማ ያልሆነው የእዝ መዋቅር እያነጋገረ ነው።  ምስራቅ ዴሞክራሲያዊት ኮንጎ የሚገኙት የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰር አውጉስቲን ሙሄሲ መፍትሄ የሚሉትን ተናግረዋል። 
«ይህ ከወታደሮቹ ሞራል ጋር የተገናኘ ነው።ብዙዎች ለረዥም ጊዜ ሲዋጉ ነበር።ወታደሮቹን በሌሎች መተካቱ ሊታሰብበት ይገባል ከሚሉት መካከል ነኝ ።»
በርሳቸው አስተሳሰብ ርስ በርሱ የሚደራረበው የእዝ መዋቅር በተለይ በሰሜን ኪቩ ተጨማሪ ችግር ሆኗል። ከኤም 23 ግስገሳ በኋላ የመከላከያ ምክር ቤት ጉባኤ ያካሄዱት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ችሴኬዲ የሀገሪቱን ሉዓላዊ አንድነት ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። ትናንት እንደተሰማው ደግሞ በምሥራቅ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ ለሁለት ሳምንታት የሚዘልቅ ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ላይ ተደርሷል። የተኩስ አቁሙ ከዛሬ አርብ እኩለ ለሊት አንስቶ እስከ እስከ ሐምሌ 12 ቀን 2016 ዓም የሚጸና ነው ተብሏል። ዋይት ዋይት ሀውስ የተኩስ አቁሙን ስታወድስ የዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥትና የኤም 23 አማጽያንን የሚያግዘው  የሩዋንዳ መንግስት ለተኩስ አቁሙ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። 
ኂሩት መለሰ 
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW