1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 28 2008

በትናንትናው ዕለት በድሬ ዳዋ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ሶስት ሰዎች ተገደሉ። በድሬዳዋ እና አጎራባች ደጋማ አካባቢዎች በሚጥለው ዝናብ ምክንያት በተከታታይ በተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ሰባት ደርሷል።

12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

[No title]

This browser does not support the audio element.

በድሬዳዋ እና በአጎራባች ደጋማ አካባቢዎች ሰሞኑን በጣለው ከባድ ዝናብ በተፈጠረ የጎርፍ አደጋ በትናንትናው ዕለት ሶስት ሰዎች ተገደሉ። ቁልቢ እና ደንገጎን ከመሳሰሉ ከፍተኛ አካባቢዎች እየተንደረደረ ከተማዋን ሰንጥቆ የሚያልፈው ጎርፍ የመልካ ጀብዱን ድልድይ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ አድርጎታል። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ በየነ በተከታታይ በደረሱ የጎርፍ አደጋዎች የሞቱት ሰዎች ቁጥር ሰባት መድረሱን ተናግረዋል። በአካባቢው የሚጥለው ዝናብ እና የሚከሰተው የጎርፍ አደጋ በድሬዳዋ በድልድዮች እና የጎርፍ መከላከያ ግድቦች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆን የጠቆሙት አቶ ፍቃዱ በየነ አሸዋማ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በድሬዳዋም ይሁን በደጋማው የሐረርጌ አካባቢዎች የሚጥለው ዝናብ ቀጣይነት እንደሚኖረው የተናገሩት አቶ ፍቃዱ ካሁን በኋላም ጥንቃቄ ካልተደረገ የከፋ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ስጋታቸውን ተናግረዋል። በጎርፍ ጉዳት የደረሰባቸውን መከላከያዎች ለመጠገን ቢታሰብም እየጣለ ያለው ዝናብ ፋታ እስኪሰጥ እየተጠበቀ ነው።
ከዚህ ቀደም በተከሰተ ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ ጉዳት የደረሰበት እና ትናንት ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ የሆነው የመልካ ጀብዱ ድልድይ ድሬዳዋን ከመልካ ጀብዱ እና ወጣ ብሎ ከሚገኘው የኢንዱስትሪ መንደር የሚያገናኝ ነበር። በድልድዩ ላይ የደረሰው ጉዳት በድሬዳዋ በኩል የሚያልፈውን የኢትዮ-ጅቡቲ የአውራ ጎዳናም እንዲቋረጥ አድርጓል። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ድልድዩን መልሶ ለመገንባት ማቀዱን አቶ ፍቃዱ በየነ ተናግረዋል።
የድሬዳዋ ከተማ ከአስር አመታት በፊት በደረሰባት የጎርፍ አደጋ በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ከአስከፊ ድርቅ በኋላ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እየጣለ ነው። የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ድርጅት ድረ-ገጽ እንደ ሚጠቁመው ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ እና ድሬዳዋ ባለፈው ወር መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ጥሏል።


እሸቴ በቀለ


አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW