የድንበር ይገባኛል ንትርክ የበረታበት ፌዴራላዊው ሥርዓት
ዓርብ፣ ጳጉሜን 3 2009የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው የጠገዴ እና ፀገዴ ወረዳዎች ድንበር ሊካለሉ ሥምምነት ፈርመዋል። ሥምምነቱን በጠገዴ ወረዳ ቀራቅር ከተማ የፈረሙት የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ-መሥተዳድሮች አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና አቶ አባይ ወልዱ ናቸው።
በሥምምነቱ መሰረት "ለረዥም አመታት ሲያወዛግቡ ነበር" የተባሉት የግጨው በረኻዎቹ የሟይእምቧ እና የሰላንዴ የእርሻ አካባቢዎች እንዲሁም አየር ማረፊያ ወደ ጠገዴ ወረዳ እንደሚካለሉ፤ በግጨው እና በጎቤ የሚኖሩ የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ደግሞ በትግራይ ክልል ወደ ፀገዴ ወረዳ ሊከለሉ መወሰኑን የአማራ መገናኛ ብዙኃን
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ-መሥተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የድንበር ውዝግቡ ሳይፈታ የከረመው "በመካከላችን መደማመጥ ባለመኖሩ" ምክንያት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
"በመካከላችን አለመግባባት አለመደማመጥ በመኖሩ ምክንያት ለረዥም ጊዜ ያጓተትንውን ችግር አሁን መደማመጥ በመኖሩ ተስማምተን በቀላሉ ፈተነዋል። ካሁን በኋላ ዘመኑ የአብሮነት የአንድነት እና የልማት ነው።"
የትግራይ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ በበኩላቸው ይኸው ችግር ሥራ ለመስራት እክል ሆኖብን ቆይቷል ሲሉ ተደምጠዋል።"ልማቱ መልካም አስተዳደሩ የምናጠናክርበት ሁኔታ እንዳንፈጥር ሲያሰናክለን የነበረው ችግር የእናንተ የሕዝብ ሽማግሌዎች ሐሳብ መሰረት በማድረግ ብአዴን፤ሕውሐት ይኸ ችግር በዛሬው ዕለት የሚፈታበት ሁኔታ፤ሕዝብ ለሕዝብ የሚቀራረብበት ሁኔታ ሁለቱም ድርጅቶች በጋራ የህዝቡን ጥቅም የሚያረጋግጡበት ሁኔታ፤ጠላቶቻችን አገኘን ያሉትን ክፍተት የሚዘጋበት ሁኔታ፤ለወደፊቱ በልማት ትኩረት ሰጥተን የምንሰራበት ሁኔታ የፈጠረ ታሪካዊ ቀን በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ።"ኢትዮጵያ በመስተዳድሮች መካከል የድንበር ችግር የገጠማት ግን በትግራይ እና አማራ ክልሎች መካከል ብቻ አይደለም። የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎችን በሚያዋስነው ምሥራቅ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ኩነቶች እየታዩ ነው። ከምዔይሶ ተሻግሮ ወደ ባሌ እና ወደ ቦረና ግዛቶች በተስፋፋው የወሰን ግጭት የድንበር አካባቢ ነዋሪዎች ነፍጥ ተማዘው ተታኩሰዋል፤ ትክክለኛ ቁጥሩ ባይታወቅም የሰው ሕይወትም ጠፍቷል። የኢትዮጵያን አዲስ አመት ለማክበር ሽር ጉድ የሚለው የሀገሪቱ መንግሥት ግን እስካሁን በግጭቶቹ ላይ በይፋ ያለው ነገር የለም።
የግጭት ትንተና እና አፈታት ባለሙያው አቶ አለማየሁ ፈንታው በትግራይ እና በአማራ እንዲሁም በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች መካከል የተቀሰቀሱት የወሰን ጥያቄዎች እንደየ አካባቢዎቹ ነዋሪዎች የአኗኗር ጠባይ ሁለት መፍትሔ ያሻቸዋል ብለው ያምናሉ።
የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት በክልሎች መካከል ለሚነሱ ግጭቶችና አለመግባባቶች መፍትሄ እንዲፈልግ ኃላፊነት የጣለበት የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ድምጹ አይሰማም። የግጭት ትንተና እና አፈታት ባለሙያው አቶ ዓለማየሁ ፈንታው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በፖለቲካ ተቋምነቱ ችግሮቹን መፍታት ስለመቻሉ ጥያቄ አላቸው።
"ሕገ-መንግሥቱ በንድፈ-ሐሳብ ያስቀመጠው አሰራር አለ። ከንደፈ ሐሳቡ አንጻር ችግር የለውም። ነገር ግን የፓርቲው አወቃቀር ኢሕአዴግ እንደሚታወቀው ግንባር እንደመሆኑ መጠን የፓርቲዎቹ የርስ በርስ ግንኙነት የፌዴሬሽኑን አካሔድ ይወስነዋል። ከዚህ አንፃር አሁን እየተነሳ ያለው ጥያቄ በእርግጥ ሕገ-መንግሥት በንድፈ-ሐሳብ ያስቀመጠው፤ አሁንም በተግባር የምንከተለው የግጭት አፈታት አሰራር እንደዚህ አይነት ነገሮችን የሚወስነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደግሞ ፖለቲካዊ ተቋም ነው። በእርግጥ ፖለቲካዊ ተቋም እንደዚህ አይነት ችግሮችን የመፍታት ብቃት አለወይ? ይኼስ አካሔድ ለወደፊቱ ሰላምን ሊያረጋግጥልን ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ ነው። "
የድንበር ውዝግቦቹ ገዢውን ፓርቲ ከአመት በላይ የፈተነውን ሕዝባዊ ቁጣ እና የጸጥታ መደፍረስ መከተላቸው በፌድራላዊው ሥርዓት ላይ የሚነሱትን ጥያቄዎች ከረር ያደርጉታል። የኢትዮጵያ መንግሥት ሹማምንት ለሌሎች አገሮች አርዓያ ይሆናል የሚሉለት ፌዴራላዊ አወቃቀር ከቶውንም አልበጀንም የሚሉ የተቃውሞ ድምጾች በርክተዋል። የኢትዮጵያ የመንግሥታዊ አወቃቀር ሥልት (ሞዴል) ከሽፎ ይሆን የሚሉ ታዛቢዎችም በርካቶች ናቸው። አቶ አለማየሁ ፈንታው ገዢው ግንባር ሀገሪቱ ለሚገጥሟት ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ እሳት በማጥፋቱ ላይ አተኩሯል ይላሉ።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ