1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የድጋፍ መቀዛቀዝ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በኤችአይቪ ኤድስ መከላከል ላይ ያስከተለው ሥጋት

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 5 2017

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲያቆም ያሳለፉት ውሳኔ በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ክልሎች የኤችአይቪ ሥርጭትን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶችን አደናቅፏል። ውሳኔው የኤችአይቪ መድሐኒት በነጻ የሚቀርብላቸው ሕሙማንን ጭምር ሥጋት ላይ የጣለ ነው።

ወይዘሮ አስቴር ያቆብ
የሐዋሳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አስቴር ያቆብ ኤችአይቪን በተመለከተ የአመለካከት ለውጥ እንዲፈጠር ለማድረግ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ያደረጉት ቀጥተኛ ድጋፍ የጎላ እንደነበር ይናገራሉ። ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

የድጋፍ መቀዛቀዝ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በኤችአይቪ ኤድስ መከላከል ላይ ያስከተለው ሥጋት

This browser does not support the audio element.

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አስቴር ያቆብ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው መኖሩን  ያወቁት ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት ነበር ፡፡ በወቅቱ ሲካሄድ የነበረው ዘመቻ ቫይረሱን ከተጠቂው ያለየ እንደነበር የሚያስታውሱት ወይዘሮ አስቴር ለዘመቻው ቅስቀሳ ይውሉ የነበሩ ምሰሎችም አስፈሪ ነበሩ ይላሉ ፡፡ ይህም ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች በማህበረሰቡ እንዲገለሉ እና እንዲፈሩ ማድረጉን ያስታውሳሉ ፡፡

ቆየት ብሎ ግን  “ መድሎ እና መገለል ይቁም “ የሚል የግንዛቤ መፍጠሪያ  ሥራዎች በመሠራታቸው  ፈጣን ሊባል የሚችል የአመለካከት ለውጥ መገኘቱን ጠቅሰዋል ፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ያደረጉት ቀጥተኛ ድጋፍ የጎላ ነበር ይላሉ ፡፡  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የእነኝህ ድርጅቶች ድጋፍ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን የሚናገሩት ወይዘሮ አስቴር ይህም በሽታው ዳግም እንዲያንሠራራ ዕድል ሊሰጥ ይችላል ይላሉ ፡፡

ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ሥጋት

ኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልን ጨምሮ የሳንባ ነቀርሳ እንዲሁም በእናቶች እና በህጻናት ዙሪያ የሚከናወኑ የጤና ሥራዎች በከፊል በልገሳ በሚገኝ በጀት የሚከናወኑ ናቸው ፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅርቡ የበጀት ድጋፉን በሙሉ እና በከፊል ያቋረጠው  የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት የተራድዖ ድርጅት (USAID)  ይጠቀሳል ፡፡ ድርጅቱ እንደአውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2024 ብቻ ለኢትዮጵያ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን መረጃዎች ያሳያሉ ፡፡

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ እመቤት መኮንን የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) በሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ በሲዳማ ክልል ብቻ 7 ተቋማት በቀጥታ 14 ደግሞ  በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እንደነበሩ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኤችአይቪ ሥርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ተባለ

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ድርጅቱ ድጋፉን እንዲያቆርጥ መደረጉ በተለይ በኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል ስራ ላይ  ተጽዕኖ አሳድሯል  ፡፡  ውሳኔው እንደነ አቶ  ተፈሪ ሚኖታ የመሳሰሉ  የፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ መድሃኒት አቅርቦትን በነጻ ሲያገኙ የቆየ ዜጎችን ሥጋት ላይ መጣሉ አልቀረም ፡፡ ግንዛቤ ማስጨበጥን ጨምሮ ሌሎች የኤች አይ ቪ መከላከል ሥራዎች ቢቋረጡም አሁን ላይ ግን የፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ መድሃኒት እያገኙ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተፈሪ “ ነገ ይህንንም አቋርጠናል  ቢሉ እንዴት እንሆናል ? “ ሲሉ ይጠይቃሉ ፡፡

“ የድጋፍ መቋረጥ እንደተጨማሪ ተግዳሮት “

መቶ አለቃ ይሳቅ ታንጋ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፣ የሲዳማ ፤ የደቡብ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎችን የሚሸፍነው የደቡባዊ ኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ ማህበራት ጥምረት ዳይሬክተር ናቸው ፡፡ በአራቱ ክልሎች ብቻ በየዓመቱ ከ2 ሺህ በላይ አዳዲስ ሰዎች በኤች አይ ቪ ኤድስ አማጭው ቫይረስ  እየተያዙ እንደሚገኙ የተናገሩት የጥምረቱ ዳይሬክተር  “ የቫይረሱ የሥርጭት መጠንም የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ ይገኛል “ ብለዋል  ፡፡

መቶ አለቃ ይሳቅ ታንጋ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) የበጀት ድጋፍ መቋረጥ በኤች አይቪ ኤድስ መከላከል ሥራው ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ገልጸዋል። ምስል፦ Shewangizaw Wegayoh/DW

የቫይረሱ ሥርጭት አስደንጋጭ ነው

አሁን ላይ በአራቱ ክልሎች ከቫይረሱ  ጋር እየኖሩ የሚገኙ 68 ሺህ 535 ሰዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ “ የድጋፍ በጀት መቋረጥ ተጨማሪ ተግዳሮት ሆኗል ይላሉ ፡፡ የክትትል እና የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን ጨምሮ አብዛኞቹ የዘርፉ ባለሙያዎች ከሥራ ውጭ ሆነው ነው የቆዩት ፡፡ በእርግጥ አሁን ላይ ባለሙያዎችን  በከፊል ወደ ሥራ  የመመለስ እንቅስቃሴ አለ ፡፡ ነገር ግን የበሽታ መከላከል ሥራው አሁንም ከውሳኔው በፊት ወደ ነበረበት ቦታው ተመልሷል ለማለት አያስደፍርም “ ብለዋል ፡፡

የትራምፕ ውሳኔ የማንቂያ ደውል

የትራምፕ ውሳኔ በዋናነት ሄዶ የነካው የኤች አይቪ ኤድስ ፕሮጀክቶችን መሆኑን የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ እና የዘርፈ ብዙ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ዘርፍ ሃላፊ  እመቤት መኮንን ይናገራሉ ፡፡ በበጀቱ በሲዳማ ብቻ 7 ተቋማት በቀጥታ 14 ደግሞ  በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እንደነበሩ የጠቀሱት እመቤት “ ውሳኔ በተቋማቱ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል ፡፡ ትልቁ ነገር ውሳኔው የማንቂያ ደውል ሆኖናል ፡፡ መዋቅሩን  መልሶ ማየትና የበሽታውን መከላከል ሥራዎችን በራስ አቅም  ማከናወን አስፈላጊ ነው ፡፡ ለዚህ ደግም መዋቅሩን መልሶ ማየትና ማደራጀት  አሥፈላጊ ሊሆን ይችላል “ ብለዋል ፡፡

የደቡባዊ ኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ ማህበራት ጥምረት ዳይሬክተር መቶ አለቃ ይሳቅ ታንጋ በዚህ ይስማማሉ ፡፡ የልማት የተራድዖ ድርጅቱ የበጀት ድጋፍ መቋረጥ በኤች አይቪ ኤድስ መከላከል ሥራው ላይ የጎላ ተፅኖ ቢባልም የትራንፕ ውሳኔ እንደመልካም አጋጣሚ እየታየ እንደሚገኝ የጠቀሱት መቶ አለቃ ይሳቅ “  የበጀት ድጋፉ መቋረጥ የግድ የውስጥ ሀብትን በማሰባሰብ በራስ አቅም የመጠቀም  አማራጭን ሊፈጥር ይችላል “ ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

እሸቴ በቀለ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW