1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የዶቼቬለ የአማርኛዉ ክፍል የቀድሞ ባልደረቦች ሲታወሱ

Azeb Tadesse Hahn
እሑድ፣ መጋቢት 28 2017

ዶቼቬለ የሬድዮ ጣብያ በሚታወቅበት እና ደወል መሰለ ሙዚቃ የሚጀምረዉ የአማርኛዉ ስርጭት የሬድዮ ጣብያ እነሆ 60ኛ ዓመቱን ያዘ። ስለቀድሞ የአማርኛዉ ክፍል ባልደረቦች በጥቂቱ እናስታዉስ።

ዶቼቬለ DW የብዙሃን መገናኛ ጣብያ
ዶቼቬለ DW የብዙሃን መገናኛ ጣብያ ምስል፦ DW

የዶቼቬለ የአማርኛዉ ክፍል የቀድሞ ባልደረቦች ሲታወሱ

This browser does not support the audio element.

የዶቼ ቬለ የአማርኛዉ ክፍል የቀድሞ ባልደረቦች በጥቂቱ

ዶቼ ቬለ የሬድዮ ጣብያ በሚታወቅበት እና ደወል መሰለ ሙዚቃ የሚጀምረዉ የአማርኛዉ ስርጭት የሬድዮ ጣብያ፤ የስርጭቱ መግብያና መሰናበቻን ይናገር የነበረዉ አቶ አማኑኤል በረከት ነዉ። አቶ አማኑኤል በረከት  ለረጅም ዓመታት የአማርኛዉ ክፍል ዋና ተጠሪ ብሎም የስፖርት ፤ የባህል እንዲሁም የተለያዩ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀቱም ይታወቃል። አብዛኞች የዶቼቬለ ባልደረቦች የሚጠሩት ጋሽ አማኑኤል ሲሉም ነበር። አቶ አማኑኤል በረከት በተለይ ከአንጋፋዉ የዶቼቬለ ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ ጋር ቅርበት ነበረዉ። አቶ አማኑኤል በረከት በጡረታ ከተገለለ በኋላ፤ ባደረበት ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ዓመታት ተቆጠሩ።

ሌላዉ በጡረታ የተገለለዉ የዶቼቬለ ጋዜጠኛ ጌታቸዉ ደስታ፤ ጡረታ እንደወጣ ኢትዮጵያ መኖር ከጀመረ በኋላ በየዓመቱ ወደ ጀርመን እየመጣ የቀድሞ መስርያ ቤት ባልደረቦቹን ይጠይቅ ነበር። ጋዜጠኛ ጌታቸዉ፤ ቀልጣፋ፤ ፈጣን ተግባቢ፤ እንዲሁም ቁም-ነገርን በቀልድ እያዋዛ በመናገሩ ይታወቃል። ሌላዉ በዶቼቬለ አድማጮች ዘንድ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈዉ፤ የጥንት የጠዋቱ ጋዜጠኛ ዘዉዱ ታደሰ ነዉ። ዘዉዱ ታደሰ፤ በሚጽፋቸዉ የተለያዩ ርዕሶች በቃላት አጠቃቀሙ እና ጥልቅ ጥናት እና መሰናዶ አድርጎ በማድረጉ ዝግጅቶቹ የተዋጣላቸዉ በሚል አድማጮች ያወድሱት ነበር።  

እዉቁ እና ተወዳጅ የነበረዉ የዶቼቬለ ጋዜጠኛ ተክሌ የኋላ ደግሞ፤ ባልደረቦቹ መዝገበ -ቃላት ነዉ ሲሉ ያደንቁታል። ተክሌ የኋላ በአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ እና ሥነ-ግጥሞቹም ይታወቃል። በመጨረሻዎቹ ዓመታት፤ ተክሌ የኋላ በአድማጮቹ ዘንድ በሳይንስ ዝግጅቶቹ ቢታወቅም ፤ በተለይ ባህል ነክ የሆኑ ነገሮችን በማቅረቡ ለዓመታት ሰርቷል።  ጋዜጠኛ ተክሌ የኋላ በጡረታ ከተገለለ በኋላ በጀርመን ኮለኝ ከተማ ሲኖር፤ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በቅርቡ በሞት የተለየ የዶቼቬለ ባልደረባ ነበር። ጋዜጠኛ ማንተጋፍቶት ስለሺ ተክሌ የኋላ እምቅ የአማርኛ ቋንቋ ችሎታ የነበረዉ፤ ትዕግስት የተላበሰ ሲል ተክሌ የኋላን ያስታዉሳል።  

ሌላዋ በጡረታ የተገለችዉ የዶቼቬለ አንጋፋ ጋዜጠኛ አርያም ተክሌ ናት። አርያም ተክሌ በአብዛኛዉ በየሳምንቱ የተለያዩ አፍሪቃ ሃገራት ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮችን በመዘገቧ ትታወቃለች። አርያም ተክሌ ለብዙ ዓመታት የዶቼቬለ አማርኛዉ ቋንቋ ክፍል ምክትል አስዳዳሪ ሆናም አገልግላለች።     

የዶቼቬለ የሀዋሳ ወኪል የነበረዉ ጋዜጠኛ ፀጋዬ እንደሻዉ፤ እንዲሁም የዶቼቬለ የአዲስ አበባ ወኪል ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳዉ በሞያቸዉ የተደነቁ ጋዜጠኞች ነበሩ። በመኪና አደጋ በድንገት የተለየን የአዲስ አበባዉ ወኪላችን በድንገተኛ ሞቱ ፤ የአማርኛዉን ክፍል ብቻ ሳይሆን የዶቼ ቬለ ከ33 በላይ ቋንቋ ክፍል አዘጋጆችን፤ እጅግ አስደንግጦ አሳዝኖአልም። ህጻናት ልጆቹን ባለቤቱን ቤተሰቡን በትኖ መቅረቱ የመላዉን ጣብያ ሰራተኞች አሳዝኗል። የጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳዉ ስም እና ስራዉ በቋሚነት ተቀርጾ፤ ጀርመን ቦን ከተማ በሚገኘዉ ዋናዉ የዶቼቬለ የራድዮ ማሰራጫ ጣብያ መግብያ ላይ በማስታወሻነት ተለጥፎ ይታያል።

ዶቼቬለ አማርኛ ምስል፦ Tsvangirayi Mukwazhi/AP Photo/picture alliance

አንጋፋዉ ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳዉ ፈጣን ታታሪ እንዲሁም በጣም ተባባሪ ሰራተኛ ነበር ሲል ገልጾታል።  በጥሩታ የተገለለዉ የዶቼቬለ ጋዜጠኛ መስፍን መኮንን ፤ አብዛኞቹ ባልደረቦቹ ጨዋ ቁጥብ ታታሪ ሲሉ ይገልፁታል። መስፈን መኮንን በጀርመንኛ ቋንቋ ይጠበባል። በዚህም ምክንያንያ በዶቼቬለ ራድዮ የጀርመንኛ ቋንቋ ትምህርት አዘጋጅ ሆኖ ለረጅም ዓመታት አገልግሏል። መስፍን ከስፖርት ሌላ የኤኮኖሚ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ ሆኖ ለረጅም ዓመታት አገልግሏል። ን በማዘጋጀቱም ይታወቃል።

ከቅርብ ዓመታት በፊት በሞት የተለየን የአዲስ አበባ የዶቼ ቬለ ወኪል ጋዜጠኛ ጌታቸዉ ተድላ፤ በተለይ በአፍሪቃ ህብረት ስብሰባዎች ላይ እየተገኘ ይዘግብ የነበረ ጋዜጠኛ ነዉ ። ባልደረቦች ሁሉ ጋዜ ሲሉ ይጠሩት የነበረዉ ጌታቸዉ ተድላ፤ ከጋዜጠኝነቱ ባሻገር የዶቼ ቬለ ጋዜጠኞች ጀርመኖችን ጨምሮ የሌሎች ሃገር ጋዜጠኞች ወደ አዲስ አበባ ሲያቀኑ  መኪናዉን ይዞ ቦሌ ዓለምአቀፍ አዉሮፕላን ጣብያ ከእቅፍ አበባ ጋር ይቀበል የነበረ የዶቼቬለ ባልደረባ ነዉ።

በጀርመን ኮለን ከተማ ነዋሪ የሆነችዉ እና በጡረታ ላይ የምትገኘዉ ሌላዋ የቀድሞ የዶቼቬለ ጋዜጠኛ ንጋት ከተማ ናት። ጋዜጠኛ ንጋት፤ ከባልደረቦችዋ የበለጠ በምታዘጋጃቸዉ ፕሮግራሞችዋ ከዶቼቬለ አድማጮች ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራት ጋዜጠኛ ነበረች። ጋዜጠኛ ንጋት ከተማ ከዶቼ ቬሌ ራድዮ ቀደም ብላ በብስራተ ወንጌል ራድዮ ያገለገለች በዘርፉ በርካታ ልምድን ያካበተች ጋዜጠኛ ናት።

ዶቼቬለ አማርኛ ምስል፦ He Yiping/Xinhua/picture alliance

ከአስመራ ዘገባወችን ይልክልን የነበረዉ ሌላዉ የዶቼ ቬለ አንጋፋ ጋዜጠኛ ጎይቶም ቢሆን አድማጮች በተለይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ የድምበር ዉዝግብ ጦርነት ያስታዉሱታል። ጋዜጠኛ ጎይቶም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከመገንጠሏ በፊት አዲስ አበባ ላይ በብስራተ ወንጌል በጋዜጠኝነት ያገለገም ነበር። በኤርትራ ከተገነጠለች ወዲህ አስመራ ላይ ሆኖ ለዓመታት የዶቼ ቬለ ወኪል ሆኖ ያገለገለዉ ጎይቶም ቢሆን በጋዜጠኝነት ሞያዉ ኤርትራ ዉስጥ መቀመጥ ባለመቻሉ ወደ ጀርመን መጥቶ ፍራንክፈርት ከተማ አቅራብያ ሲኖር ሲኖር ባደረበት ህመም ከጥቂት ዓመታት በፊት በሞት ተለይቶናል።

ሌላዉ በተለይ በአነባበቡ በሚያወጣዉ ድምፅ እና ቅላፄ በሚጠቀማቸዉ ቃላቶች የማይረሳዉ የዶቼቬለዉ ጋዜጠኛ የበርሊን ወኪል ይልማ ኃይለሚካኤል በጡረታ ቢገለልም ከበርሊን በቀጭኑ ሽቦ ቦን ከሚገኙት ከቀድሞ ባልደረቦቹ ጋር ግንኙነቱን አላቋረጠም። መዲና በርሊን ለጉዳዩ ጎራ ያለ ይልማ ኃይለሚካኤልን ሳያገኝ የሚመለስ የለም።

ዶቼቬለ አማርኛ ምስል፦ Tsvangirayi Mukwazhi/AP Photo/picture alliance

በዶቼቬለ የአማርኛዉ አልያም በኢንጊሊዘኛዉ ክፍል አገልግለዉ ወደ ሌላ ስራ አልያም ወደ ትምህርት የተመለሱ በርካታ ኢትዮጵያዉያን ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል ሃሌሉያ ሉሌ፤ ዶ/ር መርጋ ዮናስ ቡላ፤ እንዲሁም ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ ተጠቃሽ ናቸዉ።

ሙሉዉን ጥንቅር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

 

Azeb Tadesse Hahn Azeb Tadesse
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW