1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ትኩረት በአፍሪቃ፤ የትራምፕ መመረጥና አፍሪቃ፣ የኮጎ ግጭት

ቅዳሜ፣ ጥር 17 2017

የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ኤሰይ ሲካንኩ የትራምፕን ሁለተኛ የሥራ ዘመን አስመልክቶ ጠንካራ ትችት ሰጥተዋል ። «ዶናልድ ትራምፕ የተከፈተ መጽሐፍ ነው» ያሉት ሲንካኩ ትራምፕ «አሜሪካ ትቅደም» በሚል መርሃቸው የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም እንደሚያስቀድሙ አሳውቀዋል በማለት ያብራራሉ።

USA Washington 2025 | Donald Trump in der Washington National Cathedral
ምስል፦ Kevin Lamarque/REUTERS

ትኩረት በአፍሪቃ፤ የትራምፕ መመረጥና አፍሪቃ፣ የኮጎ ግጭት

This browser does not support the audio element.

 የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣት ለአፍሪካውያን ያለው ትርጉም


የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ቢመረጡ እተገብራቸዋለሁ ብለው የቀሰቀሱዋቸው የተለያዩ አጀንዳዎች ገና የሥልጣን እርካቡን እንደተቆናጠጡ ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል። እንደቅስቀሳቸው ሁሉ  ለአሜሪካ ቅድሚያ እሰጣለሁ ያሏቸውን የፖሊሲ ዕቅዶቻቸውን ይፋ እያደረጉ ነው። ትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣታቸው ለአፍሪቃውያን ምን ትርጉም አለው? በማለት የዶይቼ ቨለው የአፍሪቃ እንግሊዘኛ ክፍል ማይክል ኦቲ ያሰናዳውን እንደሚከተለው እናቀርበዋለን።

ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በነበሩበት የመጀመሪያ ጊዜበአፍሪካ ከሚገኙ መንግሥታት ጋርለመገናኘት እምብዛም ፍላጎት አልነበራቸውም ። በአሁኑ ሁለተኛ የሥልጣን ጊዜያቸውም ቢሆን ሕገወጥ ያሏቸውን ስደተኞችን ወደ አገራቸው እመልሳቸዋለሁ የሚለው  እንዲመረጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከነበረው የምርጫ ቅስቀሳቸው በዘለለ በበአለ ሲመታቸው ባደረጉት ንግግርም ከአፍሪካ ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት ያሉት ነገር እምብዛም ነው።
ያም ሆኖ ዶይቸቨለ ያነጋገራቸው በርካታ ጋናውያን የትራምፕን ከሁለተኛ የሥራ ዘመናቸው ስለአፍሪካ ግኑኝነት ከፍ ያለ ነገር ይጠብቃሉ። ጄኒፈር ናርቴይ በአሜሪካ-አፍሪካ አጋርነት ላይ አዎንታዊ አመለካከት እንዳላት ተናግራለች ። «ከአፍሪካ አገሮች ጋር የበለጠ አጋርነት ለመገንባት ትኩረት እንደሚሰጡ እጠብቃለሁ ፤ ከነዚህ የአፍሪካ ሐገሮች  ውስጥም  ጋና አንዷ ናት» በማለት ዶናልድ ትራምፕ ከጋና ጋር ጠንካራ ግኑኝነት ሊኖራት እንደሚችል ያላትን ተስፋ ገልጻለች።
ጄኒፈር በተጨማሪም በተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ  መብቶች ዙሪያ ያላትን ስጋቶች አንስታለች። ትራምፕ በአፍሪካ አገራት ፖሊሲዎች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ ብላ ጠብቃ ነበር ። በሷ እምነት አዲሱ ተመራጭ ዶናልድ ትራምፕ የዚህ መብት አቀንቃኝ እንደሚሆኑ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ይህ መብት በአፍሪቃ ሐገራት ተግባራዊ እንዲሆን ጫና እንደሚያደርጉም ከፍተኛ ጉጉት ነበራት። ይሁንና ዶናልድ ትራምፕ ገና በመጀመሪያዎቹ የስልጣናቸው ቀናት በእሳቸው የስልጣን ዘመን ሕጋዊ ዕውቅና የሚሰጧቸው ጾታዎች ወንድና ሴት ብቻ መሆናቸውን ይፋ ማድረጋቸውን አላስደሰታትም።
የጋና ዋና ከተማ አክራ ነዋሪ የሆነው ፍሬድ አዉኒ የተሰማው ስሜት ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው። እንደ አፍሪካዊነቱ እንደወግ ባህሉ ዶነልድ ትራፕ ለተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ዕውቅና መንፈጋቸው አበጁ፣ ደግ አደረጉ ሲል ድጋፉን ገልጿል።

«አፍሪካዊ እንደመሆኔ ኤል ጂ ቢ ቲ ኪው (ማለትም የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን ጨምሮ የሰውነት አካልን በቀዶ ጥገና በመቀየር ጾታን የመቀየር) ተግባር ከባህላችን አንጻር ከፍተኛ ግምት የምሰጠው ጉዳይ ነው። ዶናልድ ትራፕ ይህን መብት መሰረዛቸው በጣም አደንቃቸዋለሁ።»
ባለፈው የጎርጎሮሳውያን ዓመት የጋና የእንደራሴዎች ምክርቤት  ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚደረገውን የጾታ ግንኙነት ወንጀል መሆኑን ለመደንገግ የወጣውን ረቂቅ ሕግ አጽድቋል። የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች «አዋጁን የአናሳ ሰዎች መብት የሚጋፋ ነው» በሚል የሚተቹት ቢሆንም ሕጉ ጸድቆ ተግባራዊ የሚሆንበት መመሪያና ደንብ የሚወጣበት ደረጃ ላይ ይገኛል።

«ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በነበሩበት የመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ከሚገኙ መንግሥታት ጋር ለመገናኘት እምብዛም ፍላጎት አልነበራቸውም»ምስል፦ Evan Vucci/AP/dpa/picture alliance

በትራምፕ ሁለተኛው የስልጣን ዘመን ላይ አፍሪካውያን የነበራቸው አወንታዊ ተስፋና ተቃርኖው

አንድ የማሊ ዋና ከተማ ባማኮ ነዋሪ የትራምፕ መመረጥ አሜሪካ ከሐገራቸው ማሊ ጋር ወደፊት ሊኖራት ስለሚችለው ግኑኝነት ከጠበቁት በተቃራኒው እንደሚሆን ከዶይቼቨለ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። ቢያንስ የእሳቸው ወደ ሥልጣን መምጣት ግኑኝነቱ ፈቀቅ ሊል እንደማይችል ነው ያስረዱት።

«የፕሬዚዳንት ትራምፕ መመረጥበማሊ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን ግንኙነት ትርጉም ባለው መልኩ የሚቀይር አይመስለኝም።»
ዶይቼቬለ ያነጋገራቸው የተለያዩ አፍሪካ ሐገራት ነዋሪዎችም አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ይኖራታል ብለው የጠበቁትና እየሆነ ያለው ብዙም እንዳላስደሰታቸው ነው የሚገልጹት። የማሊ ጎረቤት በሆነችው  ናይጄሪያ ነዋሪ ለዶይቼቨለ በሰጡት አስተያየትም ትራምፕ ከአፍሪካ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ብዙም ፍላጎት አላሳዩም በማለት ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝሯል።

 «ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን የመጡት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው  ከአፍሪካውያን ለመተባበርና አብሮ ለመስራት ምንም ፍላጎት አላሳዩም ነበር። አሁን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ሲመጡም ከእሳቸው ትርጉም ያለው ለውጥ ይመጣል ብዬ አልጠብቅም።»
የዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን መምጣትን በተመለከተ የካሜሩን ነዋሪዎች አስተያየት ጥንቃቄ የተሞላበት ይመስላል። ምክንያቱም ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ከካሜሩን ጋር አጋርነት ስላላት። በመሆኑም ካሜሩን የምትከተለው ዲፕሎማሲ ከአዲሱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተቃኘ መሁን እንዳለበት ነዋሪዎች ይገልጻሉ። የያውንዴ ከተማ ነዋሪው አስተያየት ይህን የሚያጠናክር ይመስላል።

« በአሁኑ ወቅት ያለ አፍሪቃ የሚደረጉ ነገሮች የሚኖሩ አይመስለኝም፤ አፍሪካን ማግለል የሚቻል አይመስለኝም። ምክንያቱም ለዓለም ሰላምና መረጋጋት የአፍሪካ ሚና ወሳኝ ስለሆነ።»

የትራምፕ ሐገራቸው ከዓለም የጤና ድርጅት (WHO) የማግለል ውሳኔ  በመላው አፍሪካ ድንጋጤን የፈጠረ ሁኗልምስል፦ Fatih Aktas/Anadolu/picture alliance


                     የጤና እንክብካቤና ስደት

የትራምፕ ሐገራቸው ከዓለም የጤና ድርጅት (WHO) የማግለል ውሳኔ  በመላው አፍሪካ ድንጋጤን የፈጠረ ሁኗል። የዓለም ጤና ድርጅት በተለያዩ የአፍሪካ ሐገሮች የእናቶችና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚያስችሉ የጤና ሥርአቶች እንዴኖሩ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሊባል የሚችል አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህ በተጨማሪም እንደ ኤች አይ ቪ ኤይድስ ሥርጭት በመግታት፣ እንደ ኤም ፖክስ፣ ኢቦላ ያሉ ቫይረሶች ሥርጭት እንዳይስፋፋ የሚደረጉ ጥረቶችና ሌሎች ጤና ነክ ፕሮጀክቶችን በማገዝ የተሻለ የጤና ስርአት እንዲኖር የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነም ይታወቃል። እነዚህ በርካታ የዓለም ጤና ድርጅት ፕሮጀክቶች በድሃዎቹ የአፍሪካ ሐገራት አቅም ለመተግበር እጅግ ከባድ እንደሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ። የዶናልድ ትራምፕ ከአለም ጤና ድርጅት አገራቸውን የማግለል ፖሊሲ አፍሪካውያን ቢያስደነግጥ የማይገርመውም ለዚሁ ይመስላል። 
 በዚምባብዌ የሚኖረው ኩድዛይ ዚቪቫሼ ለዶይቼቬለ  እንደገለጹት የዶናልድ ትራፕ ውሳኔ «ትልቅ ዱብ ዕዳ» ነው።  አፍሪካ በከፍተኛ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ችግር የምትገኝ ሐገር እንደመሆኗ ውሳኔው እጅግ አስጊ እንደሆነም አክሏል። የዓለም ጤና ድርጅት በተለይም እንደ ኢቦላ ፣ ኮቪድ እና ኤም ፖክስ  ያሉ በሽታዎች  በመከላከልና በማከም ያለውን ክፍተት በመቅረፍ ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ያለው ኩድዛይ ይህ ሁሉ ጥረት በዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ በነበር የሚያስቀር እንደሆነ ስጋቱን አልሸሸገም። 
የፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የስደተኞች አያያዝ በተመለከተም ወደ አሜሪካ በመሄድ የተሻለ የኑሮ አማራጭን ለሚሹ ወጣት አፍሪካውያን የወደፊት ተስፋ ቀዝቃዛ ውሃ የቸለሰ እንደሆነ ወጣት አፍሪካውያን ይገልጻሉ። በአሜሪካ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመላክታሉ። ከነዚህም ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው አፍሪካውያን ይገኙበታል። ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ሕገወጥ ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዳይገቡ ከሜክሲኮ የሚያዋስናቸውን ድንበር በአጥር ከመዝጋት በተጨማሪም በርካታ ሰነድ አልባ ስደተኞች ወደየመጡበት እንዲመለሱ ማድረጋቸውን ይታወሳል።
አሁን ወደ ሥልጣን ለመምጣት ካደረጓቸው የምረጡኝ ዘመቻዎች አንዱና ምናልባትም ዋነኛው ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአሜሪካ እንደሚያባርሩ መግለጻቸው ነው። ትራምፕ ወደ ሥልጣን ድጋሚ ሲመጡ ይህን ስደተኞችን ወደየመጡበት የማባረር ፖሊያቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት አረጋግጠዋል። ይህ በጉስቁልና ለሚኖሩና ነገ ወደ አሜሪካ በመሰደድ የተሻለ የኑሮ አማራጭ አገኝ ይሆን ይሆናል ብለው ተስፋ ላደረጉ አፍሪካውያን ወጣቶች ተስፋን የሚያስቆርጥ እንደሆነባቸው ለዶይቼቨለ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል። 
ትራምፕ በኢሚግሬሽን ፖሊሲዎች በጣም ሥር ነቀል በሆነ መንገድ መምጣታቸው በአሜሪካ ሄዶ ሰርቶ የመለወጥ ህልሙን እንዳጨለመበት የሚገልጸው ኒያቲ ወደፊት ሊያገኟቸው የሚችሉ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ተስፋ ማድረጉን ግን አልሸሸገም። እንዴት አድርጎ ሕልሙን ዕውን እንደሚያደርግ ውሉ ቢጠፈበትም ተስፋ ከመቁረጥ፤ ተስፋ ማድረግን የመረጠ ይመስላል።

ሁን ወደ ሥልጣን ለመምጣት ካደረጓቸው የምረጡኝ ዘመቻዎች አንዱና ምናልባትም ዋነኛው ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአሜሪካ እንደሚያባርሩ መግለጻቸው ነው።ምስል፦ Brian Snyder/REUTERS

                የአፍሪካ የንግድ ልውውጥ 

የፖለቲካ ሳይንስ  ፕሮፌሰር የሆኑት ኤሰይ ሲካንኩ የትራምፕን ሁለተኛ የሥራ ዘመን አስመልክቶ ጠንካራ ትችት ሰጥተዋል ። «ዶናልድ ትራምፕ የተከፈተ መጽሐፍ ነው» ያሉት ሲንካኩ  ትራምፕ «አሜሪካ ትቅደም» በሚል መርሃቸው የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም እንደሚያስቀድሙ አሳውቀዋል በማለት ያብራራሉ። 

« አፍሪካ እራሷን እንዴት ከዚህ ሁኔታ ማስማማት እንዳለባት በጣም ግልጽ ነው። ዶናልድ ትራምፕ የተገለጡ መጽሐፍ ናቸው። የሚከተሉት ፖሊሲ «አሜሪካ ትቅደም» የሚል መሆኑን በግልጽ አስቀምጠዋል። ለአሜሪካ ህዝብ ተጨማሪ ጥቅም የማያስገኝ ከሆነ ከማንኛውም የዓለማችን ክፍል እንደማይተባበሩ ግልጽ አድርጓል።
አፍሪካን በተመለከተም የሚኖራቸው ግኑኝነት በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሚገታይ ነው። ከዚህ በፊት ዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ሸቀጦች ከቀረጥ ነጻ የሚገቡበት ዕድል አግዋን ለማስቀጠል ፍላጎት እንደሌላቸው ግልጽ አድርገዋል።»

ፕሮፌሰሩ በትራምፕ የንግድ ፖሊሲ ምንም ተስፋ እንደሌላቸው ገልጸዋል ። ምንም እንኳን አንዳንድ ታዛቢዎች የትራምፕ ሁለተኛ የሥራ ዘመን የዩ.ኤስ-አፍሪካ ግንኙነት እንደ ዕድል ቢቆጥሩትም ፣ ሌሎች ግን ያለፈውን ፖሊሲያቸውንና ንግግራቸውን ይጠራጠራሉ።  ከጤና ጥበቃ እስከ ስደተኛ ድረስ የሚከተሉትን መርሆችን እግምት ውስጥ በማስገባት የአፍሪካ መሪዎች ከፕረዚደንት ትራምፕ ፖሊሲዎች የሚጣጣሙ  የግኑኝነት መርሆችን ሊቀይሱ ይገባል በማለት ምክራቸውን ይለግሳሉ።
 

                  የስቪሎችን አበሳ ያናረው የኮንጎ ጦርነት
በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የማዕከላዊ መንግስቱን በሃይል ለመገልበጥ ነፍጥ አንግበው መዋጋት ከጀመሩ ከ10 ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል፤ የኤም 23ደፈጣ ተዋጊዎች። እንደዘንድሮ ግን ድል የቀናቸው ጊዜ ያለ አይመስልም። 
በያዝነው የጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከአለፈው አመት ወዲህ የጥቃት ኢላማዎቻቸውን በማስፋት በመንግስት ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ያሉት ጉዳት ከማድረሳቸውም በላይ በአሁኑ የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት ከ400,000 ሕዝብ በላይ እንዲፈናቀል ማድረጋቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሞሽን ያወጣው ሪፖርት ያመላክታል። 
እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2013 በኮንጎ የመከላከያ ሰራዊት ከባድ ሽንፈት ተከናንበው ወደ ጎረቤት ሃገራት ኡጋንዳና ሩዋንዳ ተሻግረው የነበሩ የኤም 23 ታጣቂዎች በአሁኑ ወቅት በተለይም በምስራቃዊ የሃገሪቱ ክፍል ከፍተኛ ያሉትን ጥቃት በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ። በዚህ ጥቃት ምክንያት ወደ ቁልፍ ከተማ የሆነችው ጎማ ከተማ የሚወስዱ መንገዶች ሙሉ በሙሉ ዝግ በመሆናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ዕለት ደራሽ ዕርዳታና የሕክምና ግብአቶችን ለማድረስ ከባድ እንደሆነባቸው የረድኤት ሰራተኞች ይገልጻሉ። 
በምስራቃዊ ኮንጎ የምትገነውና በአማጺዎቹ ከበባ ሥር በምትገኘው የፕሪንስ ከተማ በርካታ በጦርነቱ የተጎዱ ስቪል ዜጎች ይገኛሉ። በከተማዋ የሚገኙ ሃኪሞች ባላቸው የሕክምና ግብአቶች በጦርነቱ ምክንያት የቆሰሉትን ለማከም ሙያዊ ግዴታቸውን በመጣት ላይ ቢገኙም ካለው የተጎጂ ቁጥር አንጻር ተገቢው ሕክምና መስጠት እንዳልቻሉ ይገልጻሉ። 

« እዚህ ህክምና ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ ሐኪሞቹ የቻሉትን ያህል ሕክምና እያደረጉልኝ ቢሆንም በቂ የሕክምና መሳሪያና የመድሃኒት አቅርቦት የለም።»ምስል፦ Arlette Bashizi/REUTERS


ናምያ ማቶንዶ በተባራሪ ጥይት እጇን ቆስላ ወደህክምና ከገባች ቀናትን አስቆጥራለች።

« እዚህ ህክምና ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ ሐኪሞቹ የቻሉትን ያህል ሕክምና እያደረጉልኝ ቢሆንም በቂ የሕክምና መሳሪያና የመድሃኒት አቅርቦት የለም።»
በአለፈው ሳምንት ብቻ ኤም አይ 23 በጎማ ከተማ አቅራቢያ በፈጸመው ጥቃት ምክንያት ከ178,000 በላይ ዜጎች አካባቢያቸውን ጥለው መሰደዳቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዴቪድ ሻማቩ አስተማሪ ሲሆን ስለተማሪዎቹ ደህንነት አብዝቶ የተጨነቀ ይመስላል።

« የሕዝቡ ደህንነት መጠበቅ አለበት። ይህ ካልሆነ ተማሪዎችን ማስተማር አልችልም። በሺዎች የሚቆቸሩ ተማሪዎች አሉን። እነሱም በየትምህርትቤቱ ተጠልለው ይገኛሉ። ይሁንና ይህ ቦታም ቢሆን ለደህንነታቸው አስጊ ነው።»
የደፈጣ ተዋጊዎቹ አሁን እየፈጸሙት ላለው ጥቃት ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሩዋንዳ ድጋፍ እየሰጠች ነው በማለት ሁለቱም ሐገሮች እሰጥ አገባ እንዲገቡ ምክንያት ሁኗል። 
በቀጠናው የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ሃይል ቢኖርም ሰላም ማምጣት ይቅርና ከአለፈው የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት በፊት የነበረውን አንጻራዊ ሰላም አስጠብቆ መሄድ ባለመቻሉ በነዋሪዎች ዘንድ ብርቱ ትችትና ውግዘት እያስተናገደ ይገኛል። 
በኮንጎ ያገረሸው የእርስ በእርስ ጦርነት ለማስቆም የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤  የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባል አገሮች መሪዎች፣ በኮንጎ በቅርቡ ያገረሸውን ጦርነት ማስቆም በሚቻልበት ላይ በኬንያ  የመከሩ ቢሆንም ጠብ ያለ መፍትሔ አልተገኘም። በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው ሞት፣ መቁሰል፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ግን አሁንም በከፋ መልኩ እንደቀጠለ ነው። 


ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW