1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዶናልድ ትራምፕ አዲሱ የፍትህ ሚኒስቴር ዕጩ ራሳቸውን አገለሉ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 14 2017

በዶናልድ ትራምፕ ካቢኔ ውስጥ በጠቅላይ አቃቢ ህግነት እንዲመሩ የተመረጡት የቀድሞው የምክር ቤት አባል ማት ጌትዝ ከህገወጥ የወሲብና የአደንዛዥ እጽ ክስና ምርመራ ጋ በተያያዘ ራሳቸውን ከእጩነት አግልለዋል። በምትካቸውም ዶናልድ ትራምፕ የፍሎሪዳዋን የቀድሞ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ፓም ዶንዲን መርጠዋል።

USA Representative Matt Gaetz Republikaner
ምስል Mandel Ngan/AFP

የዶናልድ ትራምፕ የፍትህ ሚንስትር ዕጩ ራሳቸውን አግልለዋል

This browser does not support the audio element.

በዶናልድ ትራምፕ ካቢኔ ውስጥ በጠቅላይ አቃቢ ህግነት እንዲመሩ የተመረጡት የቀድሞው የምክር ቤት አባል ማት ጌትዝ ከህገወጥ የወሲብና የአደንዛዥ እጽ ክስና ምርመራ ጋ በተያያዘ ራሳቸውን ከእጩነት አግልለዋል። በምትካቸውም ዶናልድ ትራምፕ የፍሎሪዳዋን የቀድሞ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ፓም ዶንዲን መርጠዋል። የመከላለያ ሚኒስትር እጩው ፒት ሄግሴት፣ የትምህርት ሚኒስትር እጩዋ ሊንዳ ማክማሆን፣ የጤናና የሰብዓዊ አገልግሎት ሚኒስትር እጩው ሮበርት ኬኔዲም በተመሳሳይ ከወሲብ ጥቃትና ትንኮሳ ጋ የተያያዘ የተለያዩ ውንጀላወች እየቀረቡባቸው ነው። በነዚሁ የካቢኔ እጩወች ላይ የበረቱት የስነምግባርና የግብረገብ ጉድለቶች ደግሞ፣ ዶናልድ ትራምፕ ትኩረታቸው ሚመርጧቸው ሰወች ስበዕና ላይ ሳይሆን ታማኝነት ላይ እንደሆነ ማሳያ ነው ተብሏል።

የተወካዮች ም/ቤት አባል የነበሩት ማት ጌትዝ በፕሬዝዳንት ተመራጩ ዶናልድ ትራምፕ ለጠቅላይ አቃቢ ህግነት መታጨታቸው ገና ከጅምሩ ብዙ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። ከሁሉም የካቢኔ ሹመቶች ውስጥ ለዶናልድ ትራምፕ ዋናው እንደሆነ የሚነገርለትን የጠቅላይ አቃቢ ህግ ቦታ ለመያዝ፤ ጠላቶቻቸውን የሚከሱላቸው፣ የሚሉትን የሚሰሙ፣ ህጉን እንደፈለጉ ለፖለቲካ አላማ የሚጠቀሙላቸው፣ የሚያዟቸውን የሚፈጽሙ ታማኝ ሰው ማት ጌትዝ ናቸው ብለው ነበር። ያም ሆኖ ልክ እንደራሳቸው ማት ጌትዝም በተለያዩ የስነምግባር ጥሰቶች በተወካዮች ም/ቤትም፣ በፍትህ ሚኒስቴርም ዘንድ ምርመራ እየተደረገባቸው ነበር።

የትራምፕ አስተዳደር ሕገ ወጥ ባላቸው ስደተኞች ላይ የያዘው ዕቅድ

በተለይ በተወካዮች ም/ቤት የስነምግባር ኮሚቴ በኩል እድሜያቸው ካልደረሱ ሴቶች ጋር በተያያዘ ህገወጥ ወሲብና እነዚሁኑ ሴቶች ለወሲብ በማዘዋወር የተደረገባቸው ምርመራ ዋናው ነበር። ይሄው ምርመራ ወደ ማጠቃለያው መድረሱና ተጨማሪ የወሲብ ጥቃት የተፈጸመባቸው ምስክሮች መምጣታቸው ማት ጌትዝን ከእጩነት ራሳቸውን እንዲያገሉ አስገድዷቸዋል።

በትራምፕ ማሸነፍ የአፍሪካ መሪዎች ተስፋ

የማት ጌት ዝን ከእጩነት መውጣት ዲሞክራትና ሪፐብሊካኖች በተለያየ መንገድ ነው የተመለከቱት ። ሪፐብሊካኑ እንደራሴ ሊንሲ  ግራም እንዲህ ያሉ ክሶች ሪፐብሊካን ላይ ሲሆን ይገናሉ ባይ ናቸው። ዲሞክራቱ ክሪስ ኩንስ በበኩላቸው እንዲህ አይነቱን በከባድ ክሶች የተከበበ ሰው የሃገሪቷ ዋና አቃቢ ህግ አድርጎ መሾሙ አግባብ አልነበረም ብለዋል።

ዳግም ምርጫ ካሸነፉ ወዲህ የመጀመሪያ የሆነውን ሽንፈት ከማት ጌትዝ የተቀበሉት ዶናልድ ትራምፕ በማት ጌትዝ ምትክ የቀድሞዋን የፍሎሪዳ ግዛት ጠቅላይ አቃቢ ህግ ፓም ቦንዲን መርጠዋል። ፓም ዶንዲም ቀንደኛ የትራምፕ ደጋፊ፣ የፍትህ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ለመፈጸም ጥቅም ላይ ውሏል ብለው የሚያምኑ፣ የትራምፕን አጀንዳ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለማስፈጸም የተዘጋጁ ናቸው።

ግም ምርጫ ካሸነፉ ወዲህ የመጀመሪያ የሆነውን ሽንፈት ከማት ጌትዝ የተቀበሉት ዶናልድ ትራምፕ በማት ጌትዝ ምትክ የቀድሞዋን የፍሎሪዳ ግዛት ጠቅላይ አቃቢ ህግ ፓም ቦንዲን መርጠዋል።ምስል Andrew Caballero-Reynolds/AFP

ፕሬዝዳንት ባይደንና ተመራጩ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ነጩ ቤተ-መንግሥት ዉስጥ ተገናኙ

የዶናልድ ትራምፕ የካቢኔ እጩወች ግርግር በዚህ አያበቃም። የመከላከያ ሚኒስትር እጩው፣ የቀድሞው የፎክስ ቴሊቭዥን አቅራቢ ፒት ሄግሴት እንዲሁ ከዚህ ቀደም የወሲብ ጥቃት የፈጸሙ እንደሆነ እየተነገረ ነው። ጉዳዩ ከፍ/ቤት ውጪ በካሳ ክፍያ የተፈታ እንደሆነ ጠበቆቻቸው ቢናገሩም፣ ፒት ሄግሰት ያጠፋሁት ነገር የለም ባይ ናቸው።

በተመሳሳይ ሁኔታ የትምህርት ሚኒስትር እንዲሁኑ የተመረጡት ሊንዳ ማክማሆን በነጻ ትግል መዝናኛ ሃላፊነታቸው ዘመን ህጻናት ለወሲብ ጥቃት እንዲጋለጡ አድርገዋል የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል። የጤናና የሰብዓዊ አገልግሎት ሚኒስትርን እንዲመሩ የተመረጡት ሮበርት ኬኔዲም ቤታቸው ውስጥ ትሰራ የነበረች የህጻናት ጠባቂ ላይ የወሲብ ትንኮሳ ፈጽመዋል በሚል ስማቸው ተነስቷል።

የኋይት ሃውስ እጩወች ስብዕናና ማንነት የፕሬዝዳንቱ ማንነት መገለጫ ናቸው ይባላልምስል Matt Rourke/AP/picture alliance

እንዲህ ላለው ከፍተኛ ስልጣን የሚታጩ ግለሰቦች ተገቢው የኤፍቢአይ ምርመራ ሪፖርትን ጨምሮ ሰፊ የጀርባ ታሪክ ጥናት የሚደረግባቸው መሆኑ የተለመደ ነው። ያም ሆኖ ዶናልድ ትራምፕ ከመደበኛው የማንነትና የስብዕና ጥያቄ ይልቅ ታማኝነትና ታዛዥነት ላይ ያተኮሩ ይመስላሉ።

የዶናልድ ትራምፕ የባለሥልጣናት ምርጫ ስለመጪው አስተዳደራቸው ምን ይጠቁማል?

የኋይት ሃውስ እጩወች ስብዕናና ማንነት የፕሬዝዳንቱ ማንነት መገለጫ ናቸው ይባላል። እናም ብዙወቹ የትራምፕ እጩ የካቢኔ አባላት በወሲብ ጥቃት፣ በስነምግባር፣ በግብረገብ አልያም በህግ ጥሰት ክስና እሰጣ ገባ ውስጥ ያሉ መሆናቸው የዚህ እውነት ነጸብራቅ ነው። ዶናልድ ትራምፕ ካቢኔያቸውን በራሳቸው አምሳዮች እየቀረጹት ይመስላል። እስካሁን አንዱን አጥተዋል። ከመረጧቸው እጩወች ምን ያህሉ በሴኔት ይሁንታን አግኝተው ይቀጥላሉ የሚለው የሚታይ ይሆናል።

አበበ ፈለቀ

ታምራት ዲንሳ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW