የዶይቼ ቬለ አማርኛ የአልማዝ ኢዮቤልዩ በማስመልከት ሉድገር ሻዶምስኪ ያስተላለፉት መልዕክት
እሑድ፣ መጋቢት 28 2017
ዶይቼ ቬለ በመላዉ ዓለም ዘገባዎች ከሚያሠራጭባቸዉ 31 ቋንቋዎች አንዱ አማርኛ ነው። የአማርኛው አገልግሎት ለኢትዮጵያ እና ለአካባቢዉ ሐገራት ማሰራጨት የጀመረዉ መጋቢት 6 ቀን 1957 ነበር።
የክፍሉ ኃላፊ ሉድገር ሻዶምስኪ 60ኛውን ዓመት በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት “በመጀመሪያ ለባልደረቦቻችን እና ኢትዮጵያ፣ ብራስልስ፣ ለንደን እና ዩኤስ አሜሪካን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ ዘጋቢዎቻችን ለዶይቼ ቬለ አማርኛ ላላቸው ፅኑዕ ቁርጠኝነት በዚህ አጋጣሚ ከልብ ላመሰግናቸው እወዳለሁ” ብለዋል።
ሉድገር ሻዶምስኪ ከታኅሳስ 1999 ጀምሮ የዶይቼ ቬለ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ክፍል ኃላፊ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ለኢትዮጵያ በራዲዮ ሞገድ፣ በሳተላይት እና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘገባዎች የሚያቀርበውን ክፍል ለረዥም ዓመታት በመምራታቸው “ትልቅ ክብር” እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።
ዶይቼ ቬለ አማርኛ 60ኛ ዓመቱን ሲያከብር ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ “በአስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ” እንደሚገኙ ሻዶምስኪ በመልዕክታቸው አስታውሰዋል። “እርግጥ ነው በዚያ ያለዉ ሁኔታ ተስፋ ሰጪ ብሩሕ አይደለም። ይህ በግልጽ ሊነገር የሚገባው የሚገባዉ ይመስለኛል።መታየት ያለበትም በዚህ አውድ ነዉ ብዬ አምናለሁ” ያሉት ሉድገር ሻዶምስኪ በተለይ “የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ትሥሥር” እንደሚያሳስባቸው ጠቅሰዋል።
በዶይቼ ቬለ የአማርኛ ቋንቋ ዝግጅት ክፍል ኃላፊነታቸው ብቻ ሳይሆን “በኢትዮጵያ ከነበረኝ ልምድ፤ ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቡ ባለኝ ቅርበት ላይ በመመርኮዝ” አስተያየታቸውን የገለጹት ሻዶምስኪ “የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ትሥሥር በነበረበት አይደለም” ብለዋል።
“በብሔር ፖለቲካ አንዳንዴም በሐይማኖታዊ አውድ በጣም የተወጠረ፤ በከፊል የተበጣጠሰ እና የተጎዳ ሆኗል። በእርግጥ ይህ በታዘብነው አውዳሚ ጦርነት ጭምር የተከሰተ ነው” ሲሉ ኃላፊው አክለዋል። “በስብሰባዎቻችንም ላይ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ተወያይተናል” ያሉት ሉድገር ሻዶምስኪ “ይህ እኛን በጣም ያሳስበናል። ዘገባ በምንሠራበት ወቅትም ትልቅ ተግዳሮት ይፈጥራል” ሲሉ ተጽዕኖውን አስረድተዋል።
በ2018 በኢትዮጵያ ይካሔዳል ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ ሌላው ትልቅ ጉዳይ መሆኑን አስታውሰው “ይህ ምርጫ ገና ካሁኑ ጥላውን እያጠላ ነው።ኢትዮጵያ ዉስጥ ትልቅ አሻራ እንዳሳረፈ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ምርጫውን መዘገብ ይኖርብናል” ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ጸጥታ እና ፖለቲካ ረገድ መሠረታዊ ለውጥ እየተከሰተ እንደሚገኝ ሻዶምስኪ በመልዕክታቸው አስታውሰዋል። ሻዶምስኪ እንዳሉት አሜሪካን አጋሮቿ በ ሚሰጡትን የልማት ርዳታ ረገድ የታየው ለውጥ የከፋ ያሉትን የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ ሊያባብስ እንደሚችል ሥጋታቸውን አጋርተዋል።
የአጎዋ እጣ-ፈንታ እና ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ሀገሮች ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የጣሉት ትሪፍ እና ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዶይቼ ቬለ ተከታትሎ ዘገባ ከሚያቀርብባቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚሆኑ ጠቅሰዋል። የዶይቼ ቬለ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ወደፊት ዘገባዎቹን ባለፉት 60 ዓመታት እንዳደረገው ሁሉ በገለልተኛነት እንደሚያጠናቅር ቃል ገብተዋል።
“ገለልተኛ እንሆናለን። በተለይ በሐሰተኛ መረጃ በተጥለቀለቅንበት ባሁኑ ጊዜ ሐቅ ላይ ብቻ በመመርኮዝ እንዘግባለን። በፖለቲካ፣ በጎሳም ይሁን በሐይማኖት ንቅናቄዎች እና ዝንባሌዎች ወደየትኛውም አንወግንም” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሉድገር ሻዶምስኪ “በዘመናት ውስጥ የተፈተነ የዶይቼ ቬለ አማርኛ ጋዜጠኝነትን በተጠናከረ መልኩ ለመቀጠል፣ ከሁሉም በላይ የበለጠ አድማጭ ጋር ለመድረስ እንሰራለን” ብለዋል።
በራዲዮ በአጭር ሞገድ ብቻ ይተላለፍ የነበረው እና በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 11:00 ሰዓት የሚጀምረው የዶይቼ ቬለ ሥርጭት “የጀርመን ድምጽ” እንዲሁም “የኮሎኝ ድምጽ” ተብሎ ይታወቅ እንደነበር በመልዕክታቸው አስታውሰዋል።ዕለታዊው ሥርጭት አሁንም በአጭር ሞገድ የሚተላለፍ መሆኑን የጠቀሱት የዶይቼ ቬለ የአማርኛ ቋንቋ ክፍል ኃላፊ “ዛሬ ዘገባዎቻችንን የምናቀርብባቸውን ስልቶች በከፍተኛ ሁኔታ አስፋፍተናል” ብለዋል።
“የበለጠ ከፍተኛ እና የተለያዩ አድማጭ-ተከታታዮች ጋር ለመድረስ በኢንተርኔት ከሁሉም በላይ ደግሞ አጭር ዕድሜ ያለው ቲክ ቶክን ጨምሮ ጠቃሚ በሆኑ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እንጠቀማለን” ያሉት ሉድገር ሻዶምስኪ “ባለፉት 60 ዓመታት እንደነበረን ልማድ ሁሉ ከዚህ መንገድ አናፈነግጥም” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።