1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመኑ ቻንስለር ለዩክሬን ያላቸዉ ግልፅ አቋም

ሰኞ፣ ግንቦት 1 2014

የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችዉን ጦርነት አታሸንፍም የሚል ጠንካራ እምነት እንዳላቸው ተናገሩ። "በሩሲያ አምባገነናዊ አገዛዝ ሥር ምንም ሰላም የለም"ያሉት ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ በሩሲያ የጠብ አጫሪ ጦርነት ዉስጥ ዩክሬንን በመደገፍ ረገድ ጀርመን ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባት አጉልተዉ ተናግረዋል።

Bundeskanzler Scholz TV-Ansprache
ምስል Britta Pedersen/AFP

የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችዉን ጦርነት  አታሸንፍም የሚል ጠንካራ እምነት እንዳላቸው ተናገሩ። ቻንስለሩ ይህን የተናገሩት ትናንት በጀርመን ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ያበቃበትን 77ኛ ዓመት በማስመልከት ለህዝባቸዉ ቤቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር ነዉ። "በሩሲያ አምባገነናዊ አገዛዝ ሥር ምንም ሰላም የለም"ያሉት ቻንስለር  ኦላፍ ሾልዝ  በሩሲያ የጠብ አጫሪ ጦርነት ዉስጥ  ዩክሬንን በመደገፍ ረገድ ጀርመን ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባት አጉልተዉ ተናግረዋል። 
«የሩስያ ፕሬዚደንት ፑቲን ዩክሬንን ለመጣል፤ ባህሏን እና ማንነቷን ለማጥፋት ይፈልጋሉ። ይህን አረመኔያዊ ጥቃት ከብሔራዊ ሶሻሊዝም ጋር ከሚደረግ ጦርነት እኩል  እንደሚዋጉ አድርገው ይቆጥራሉ። ይህ  በደንብ የሚታወቅ ታሪክን ማዛባት ነው። አሳፋሪ የሆነ የተዛባ አመለካከት ነው። እኛ ይህን በግልጽ የመናገር ግዴታ አለብን።»
እንደ ቻንስለር ሾልዝ ገለፃ ከሆነ ጀርመን ከጎርጎረሳዉያኑ 1933 እስከ 1945 ዓ.ም ባሉት ዘመናት ከነበረው አደገኛ ታሪክ፤ ወሳኝ ትምህርት ወስዳለች ብለዋል። መራሔ መንግሥት ሾልዝ ጀርመን ከታሪክ ያገኘችዉ ትምህርት "ዳግመኛ ጦርነት አይነሳም፤ ዳግመኛ የዘር ማጥፋት ዘመቻ አይነሳም፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጨቋኝነት የለም" የሚል ነዉ ሲሉ አክለዋል።  ይህ ማለት ብለዋል የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ይ ማለት፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከ77 ዓመታት በኋላ ዛሬ በሚታየዉ ሁኔታ፣ ዩክሬን ላይ የተቃጣዉን  ጥቃት ለመመከት ጀርመን ከጎንዋ ትሰለፋለች ማለት ነዉ ሲሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም ሾልዝ፣ ሩሲያውያንና ዩክሬናውያን በአንድ ወቅት በአንድነት እንዴት ተባብረው እንደተዋጉና የጀርመንን "ነፍሰ ገዳይ ብሔራዊ ሶሻሊስት አገዛዝ" ያሉትን ለማሸነፍ ከፍተኛ መስዋዕትነት እንደከፈሉ አስታውሰዋል።

 

አዜብ ታደሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW