1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመኑ የረቂቅ ሙዚቃ መድረክና የኢትዮጵያዉያን አስተያየት  

ሐሙስ፣ ጥር 18 2009

በሰሜናዊ ጀርመን ወደሚገኘዉ የወደብ ከተማ ሃምቡርግ «ኤልቤ» ወንዝ ዳርቻ ላይ የተሠራዉ ግዙፍ የረቂቅ ሙዚቃ አዳራሽ የሃገሪቱ ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ሠዎች ፖለቲከኞች እንዲሁም የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ዩዘሂም ጋዉክና መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በተገኙበት ተመርቆአል።

Deutschland Hamburg Eröffnung der Elbphilharmonie
ምስል Reuters/C. Charisius

የጀርመኑ የረቂቅ ሙዚቃ መድረክና የኢትዮጵያዉያን አስተያየት  

This browser does not support the audio element.


ይህ እጅግ ግዙፍ ህንጻ በዓለም ከሚገኙ የረቂቅ ሙዚቃ መድረኮች እጅግ ዘመናዊ ፤ እንዲሁም ከመድረኩ የሚወጣዉ ድምፅ ጥራቱ ለታዳሚ ጆሮ በጥራት እንዲንቆረቆር በልዩ የሕንጻ መሳርያ እንደተሰራ ሁሉ ተነግሮለታል። በሰሜናዊ ጀርመን የወደብ ከተማ በሆነችዉ በሃምቡርግ ከአስር ዓመት ግንባት በኋላ የተጠናቀቀዉ የረቂቅ ሙዚቃ መድረክ « ኤልብ ፊላርሞኒ» የሚል ስያሜን ይዞአል። ከሁለት ሺህ በላይ ታዳሚዎችን ከሚይዘዉ የረቂቅ ሙዚቃ አዳራሽ ሌላ በሕንጻዉ፤ ግዙፍ ሆቴል፤ መኖርያ ቤት፤ ቡና ቤቶች እንዲሁም የመኪና ማቆምያ ጋራዥን ሁሉ ማካተቱ ሌላዉ የአድምጫን የተመልካችን ቀልብ የሳበ ሆንዋል።  መርከብ አልያም ማዕበል አይነት ቅርጽን የያዘዉ ሕንጻ በዓለማችን በቅርብ ጊዜ ከተሰሩ ግዙፍና ድንቅ ከሚባሉ ህንጻዎች ተርታ የተሰለፈና የፔኪንጉን የኦሎምፒክ ሜዳ እንዲሁም፤ የባቫርያዉን አሪና የተባለዉን ግዙፍ የኳስ ሜዳ የሰሩ አሜሪካዊና የኦስትርያዊ የሕንጻ ተቋራች ባለሞያዎች እንደገነቡት ተነግሮአል። በርሊን የሚገኘዉ ባልደረባዬ ይልማ ኃይለሚካኤል እንደሚለዉ ቀደም ሲል የሕንጻዉ የቆመበት ቦታ መሠረቱ የከመርከብ የሚራገፍ ጆንያ ማቆምያ ቦታ ነበር። 
ወደ ሰሜን ባህር የሚፈሰዉ ኤልበ ወንዝ ላይ የሚገኘዉ 37ሜትር ከፍታ ያለዉ ሕንጻ  ከጣርያዉ ላይ ሆኖ የወደብ ከተማይቱን ሃንቡርግን ዙርያ የሚያስቃኝ፤ ግዙፍ ሁለት የሙዚቃ አዳራሾችን ፤  250 ክፍሎች ያሉት ቅንጡ ሆቴልን እንዲሁም 45 ቅንጡ የመኖርያ ቤቶችን ያካተተም ነዉ። የሕንጻዉ ግንባታ ሲጀመር በ 77 ሚሊዮን ይጠናቀቃል ተብሎም ነበር፤ 

ምስል Mario Di Bari
ምስል Reuters/F. Bimmer

 30 ሺ ስኩየር ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባዉ ይህ ሕንፃ ረቂቅ ሙዚቃ የሚቀርብበት መድረክ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ዓለም ሃገርት የሚደመጡ ሙዚቃዎች ይቀርቡበታል። 
በወቅቱ በጀርመን ባለዉከፍተኛ ብርድና በረዶ ምክንያት ለሰላሳ ደቂቃ አርፍደዉ በምረቃዉ ሥነ-ስርዓት ላይ የተገኙት መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል፤ ሕንጻዉም በሦስት ዓመቱ ተገንብቶ ያልቃል ተብሎ በአስር ዓመቱ ተጠናቆአል ሲሉ ፈገግ አሰኝተዋል።  
ከጀርመናዉያን ሙዚቀኞች ጋር በርካታ ልምድን ያካበተዉ ብሎም « ጉዞ» በሚል ርዕስ ከጀርመናዉያን ጋር በጋራ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ጥናት ላይ የሚገኘዉ የፒያኖ ተጫዋቹ ከሳሙኤል ይርጋ እንደሚለዉ ጀርመናዉያን ለጥበብ የሚሰጡትን ቦታ አይቻለሁ፤ ሲል ገልፆልናል። ኢትዮ ጃዝ የተባለውን የሙዚቃ ስልት በመፍጠር የኢትዮጵያን የጃዝ ሙዚቃ ዕድገት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በማድረሱ የሚታወቀዉ አንጋፋዉ ሙዚቀኛ ሙላቱ አስታጥቄ፤ የጀርመናዉያንን የረቂቅ ሙዚቃ ጥልቀት ባይክድም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ለዓለም ሙዚቃ መሰረት መሆኑን ይናገራል። ኪነ-ጥበብ ለሃገር እድገት ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል ሕዝባችን ለሙዚቃ ያለዉ ፍቅር ከፍተኛ ቢሆንም ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሙዚቃ እድገት የሚሰጥ ምንም ድጋፍ እንደሌለ ተናግሮአል።በጀርመንዋ የወደብ ከተማ በሃምቡርግ የተገነባዉን ዘመናዊ የረቂቅ ሙዚቃ መድረክን እየቃኘን በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ በተለይ ደግሞ ሙዚቃን አስመልክተን ባለሞያዎችን ያነጋገርንበት ሙሉ መሰናዶ እንዲከታተሉ እንጋብዛለን። 

ምስል Christoph Köstlin für Viva con Agua


አዜብ ታደሰ 
ኂሩት መለሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW