1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመናዊዉ ሊቅ ሂዮብ ሉዶልፍና የአባ ጎርጎርዮስ ወዳጅነት

ሐሙስ፣ ጥቅምት 21 2017

የጀርመናዊዉ ሂዮብ ሉዶልፍ እና አባ ጎርጎርዮስ ወዳጅነት፤ በምዕራቡ ዓለም እና በኢትዮጵያ መካከል ረጅም ወዳጅነት እንደነበር የሚያሳይ ነዉ። ሁለቱ ልሂቃን የተዋወቁት የአጼ ሱስኒዩስ አስተዳደር ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ወደ ካቶሊክ በመቀየሩ፤ የካቶሊክ ሃይማኖታቸዉን መለወጥ የማይፈልጉ ኢትዮጵያዉያን መነኮሳት ወደ ጣልያን ቫቲካን ተሰደዉ ሳለ ነዉ።

ፎቶ ፤ በጎታ ኤርፎርት የሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ ዓመት ልደት በዓል ጉባy ላይ የቀረበ
ጀርመናዊዉ ሂዮብ ሉዶልፍ እና ኢትዮጵያዊዉ አባ ጎርጎርዮስምስል Azeb Tadesse Hahn/DW

የጀርመናዊዉ ሊቅ ሂዮብ ሉዶልፍና የአባ ጎርጎርዮስ ወዳጅነት

This browser does not support the audio element.

«ይህ ጉባዔ በ 17ኛዉ ክፍለዘመን ጀርመን ሃገር የተወለደ እና ሂዮብ ሉዶልፍ የተባለ ሰዉ ትልቅ ስራን የሰራ ጀርመናዊ ምሁር ነዉ፤ ይህን ሊቅ ስመጥር ያደረገዉን ስራ ሊሰራ የቻለበት ምክንያት፤ አባ ጎርጎርዮስ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ካህንን ፤ ሮም ከተማ ላይ አግንኝቶ ቀደም ብሎ የጀመረዉን የግዕዝ ቋንቋ ጥናት፤  ከአባ ጎርጎርዮስ አሻሽሎ እና በደንብ ተምሮ፤ የኢትዮጵያ ጥናት በምዕራቡ ዓለም፤ ትልቅ ፈር ቀዳጅ ስራን እንዲሰራ ስላደረገ ፤ በጀርመን ሃገር ኤርፉት ከተማ ላይ ምሁራን የሂዮብ ሉዶልፍን አስተዋፅኦ ለማክበር ባዘጋጁት የሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ ዓመትን ዝግጅት ላይ ነዉ የተገኘሁት። በዚሁ አጋጣሚ በተለይም እሱ በሰራዉ የሰዋስዉ መጽሐፍ፤ በላቲን ቋንቋ የግዕዝ ሰዋስዉ ፤ እንዲሁም ደግሞ ግዕዝ ላቲን፤ አማርኛ ላቲን መዝገበ ቃላትን ጽፏል። በጉባኤዉ ላይ ሂዮብ ሉዶልፍ ያበረከተዉን ስራ ነዉ ያቀረብኩት»

በ 17 ኛዉ ክፍለዘመን በአንድ ጀርመናዊ እና ኢትዮጵያዊ ምሁር መካከል የተፈጠረ ትዉዉቅ ለእስከዛሬዉ የኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ እና ከአዉሮጳ/ዓለም የጋራ የምርምር ስራ ከፍተኛ አበርክቶት ማድረጉን የነገሩን፤ በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስትያን የአዲስ አበባ አገረስብከት ካህን እና በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ሥነ-ልሳን እና ፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር፤ አባ ዶ/ር ዳንኤል አሰፋ ነበሩ።

አባ ዶ/ር ዳንኤል አሰፋ - በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ሥነ-ልሳን እና ፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ምስል Azeb Tadesse Hahn/DW

አባ ዶ/ር ዳንኤል አሰፋ ይህን የተናገሩት ባለፈዉ ሰሞን ኦርቢስ ኢቶፒኩስ ማለትም ዉርሰ ኢትዮጵያ የተባለዉ የኢትዮጵያዉያን ማኅበር ጀርመን ኤርፉርት ጎታ ከተማ ላይ የኢትዮጵያ ጥናት አባት የሚባሉትን የጀርመናዊዉን ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የትዉልድ ዓመት በማስመልከት በተዘጋጀዉ የሦስት ቀናት ጉባዔ ላይ ነበር።  ጤና ይስጥልኝ አድማጮች እንደምን ሰነበታችሁ። በዚህ ዝግጅት ላይ አዲስ አበባ ከሚገኘዉ ከጀርመን የባህል ማዕከል ከጎተ ተቋም በተገኘ ከፍተኛ ትብብር በሦስቱ ቀናት ጉባኤ ላይ ለመገኘት ከአባ ዶ/ር ዳንኤል አሰፋ ጋር ከአዲስ አበባ ወደ ጀርመን የመጡት እና በጉባኤዉ ላይ የጥናት ጹሑፋቸዉን ያቀረቡት ፕሮፌሰር ሽፈራዉ በቀለ ሌላዉ የታሪክ ምሁር እንግዳ ነበሩ።  ፕሮፌሰር ሽፈራዉ በቀለ በተለይ ስለ ጀርመናዊዉ የኢትዮጵያ ጥናት አባት ስለ ሂዮብ ሉዶልፍ እና ስለ አባ ጎርጎርዮስ ታሪክ በስፋት አጥንተዋል። በጀርመን ሃገር በታሪክ፤ ስነ-ሕብረተሰብ ጉዳዮች ላይ የዶክትሪት መመረቅያ ዲግሪያቸዉን ለመስራት ለሚማሩ ተማሪዎችም እገዛ ያደርጋሉ። በሃንቡርግ እና ፍራንክርት ከተማ ከሚገኙ የቋንቋ ጥናት ተቋማት ጋርም ይሰራሉ።

ጀርመናዊዉ ሂዮብ ሉዶልፍ እና የኢትዮጵያዊዉ የአባ ጎርጎርዮስ ካርታምስል Azeb Tadesse Hahn/DW

በአጼ ሱስኒዩስ ዘመን መንግሥት አስተዳደሩ ሃይማኖትን ከተዋህዶ ወደ ካቶሊክ በመቀየሩ ብሎም ቆየት ብሎ ይህን ተሽሮ ወደ ተዋህዶ ሃይማኖት በመመለሱ፤ የካቶሊክ ሃይማኖት እምነታቸዉን መለወጥ የማይፈልጉ ኢትዮጵያዉያን መነኮሳት ወደ ጣልያን ቫቲካን ተሰደዉ እንደነበር የነገሩን ፕሮፌሰር ሽፈራዉ፤ በአገሩ ጀርመን ላይ ግዕዝን ማጥናት የጀመረዉ ጀርመናዊዉ ሊቅ ሂዮብ ሉዶልፍ ወደ ቫቲካን ተጉዞ፤ አባ ጎርጎርዮስን መተዋወቁና በሁለቱ ሊቆች መካከል ወዳጅነት በዚህ መንገድ መመስረቱን አስረድተዋል።

እና ለዘርፉ ጥናት አበርክቶቱ ትልቅ ነዉ ይላሉ?    

ፕሮፌሰር ሽፈራዉ በቀለ ሌላዉ የታሪክ ምሁርምስል Azeb Tadesse Hahn/DW

«በእርግጥ አበርክቶቱ እጅግ ከፍተኛ ነዉ። በግዕዝ ቋንቋ ጥናት ብዙ መጽሐፍትን ጽፏል። መዝገበ ቃላትን አዘጋጅቷል። የግዕዝ ጽሑፎችን ወስዶ ተርጉሞ፤ ታሪካዊ አመጣጣቸዉ እና አዉዳቸዉን፤ አሳትሟል። የኢትዮጵያን ታሪክም ጽፏል። ከሂዮብ ሉዶልፍ በፊት የቋንቋ ጥናትን ያደረገ፤ የብራና ጽሁፍ ጥናትን ያካሄደ የለም። ስለዚህ የመጀመርያዉ ሊቅ በቋንቋ ዘርፋ ያጠና ሂዮብ ሉዶልፍ ነዉ። ለዚህም ነዉ የኢትዮጵያ ቋንቋ መስራች ነዉ የምንለዉ።»

ወደ ጀርመን ተጋብዘዉ የነበሩት ሁለቱ ኢትዮጵያዉያን የታሪክ ምሁራን ዉርሰ ኢትዮጵያ ባዘጋጀዉ ጉባኤ ላይ መገኘት እንዲያስችላቸዉ አዲስ አበባ የሚገኘዉ የጀርመን ባህል ማዕከል የጎተ ተቋም ሙሉ ወጭዉን በመሸፈን በጀርመን ኤርፉርት ጎታ ከተማ በተዘጋጀዉ ጉባዔ  ላይ መገኘት መቻላቸዉን ፕሮፌሰር ሽፈራዉ በቀለ ተናግረዋል።     

በኢትዮጵያ የካቶሊካዊት ቤተ-ክርስትያን የአዲስ አበባ አገረስብከት ካህን እና በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሥነ-ልሳን እና ፊሎሎጂ ትምህርት መምህር፤ አባ ዶ/ር ዳንኤል አሰፋ፤ የኢትዮጵያ ጥናት አባት በመባል የሚታወቁት የጀርመናዊዉን ሊቅ የሂዮብ ሉዶልፍ እና የአባ ጎርጎርዮስን ሥራ ማስታወሱ፤ ለዛሬ ትምህርት ጥናት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለዉ ተናግረዋል።

የጎተ ተቋም አዲስ አበባ ምስል Goethe-Institut Ethiopia

ዘንድሮ 400 ኛ የትዉልድ ዓመትን ለመዘከር ከሳምንታት በፊት ወደ ጀርመን ተጋብዘዉ የነበሩት ሁለቱ ኢትዮጵያዉያን የታሪክ ምሁራን ዝግጅቶቻቸዉን አጠናቀዉ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። የጀርመናዊዉ ሊቅ የሂዮብ ሉዶልፍ  እና የአባ ጎርጎርዮስን ወዳጅነት እንዲሁም የሂዮብ ሉዶልፍ ሥራዎች በጀርመን በተለያዩ ተቋማት እና ዩንቨርስቲዎች  እየታሰበ ነዉ። አድማጮች  አባ ዶ/ር ዳንኤል አሰፋ እና ፕሮፌሰር ሽፈራዉ በቀለ ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ DW ስም በማመስገን ሙሉ ዝግጅቱን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ዩሐንስ ገብረእግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW