1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ፣ የአዉሮጳና የፋርስ ተቀናቃኞች የአፍሪቃ ጉብኝት

ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 2 2016

ኢራን በ2020 ከአፍሪቃ ጋር የነበራት የንግድ ልዉዉጥ 579 ሚሊዮን ዶላር ነበር።በ2022 ወደ 1.28 ቢሊዮን ከፍ ብሏል።ዘንድሮ ደግሞ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ይደፍናል ተብሎ ይጠበቃል።ዋናዋ ደቡብ አፍሪቃ ናት።

ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራይሲና ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴ ቬኒ-ዩጋንዳ
የኢራን ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራይሲ ከዩጋንዳዉ አቻቸዉ ዩዌሪ ሙሴ ቬኒ ጋር ምስል Mashreghnews

ትኩረት በአፍሪቃ፣ የጀርመንና የኢራን መሪዎች የአፍሪቃ ጉብኝት

This browser does not support the audio element.

                   

ከጋዛ-እስከ የመን ባለዉ እልቂት፣አዉሮጳና እስያ በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት፣ከብራስልስ እስከ ኒዮርክ አንዴ በኑክሌር መርሐ ግብር ሌላ ጊዜ በርዕዮተ-ዓለም ጠብ የሚዛዛቱ-የሚወጋገዙት የአዉሮጳና የፋርስመሪዎች ሠሞኑን ካንዱ የአፍሪቃ ርዕሰ ከተማ ወደ ሌላዉ ሲባትሉ ሰንብተዋል።የብሪታኒያ ንጉስ ቻርለስ ሳልሳዊ ኬንያን፣ የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ታንዛኒያን፣ የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ናጄሪያና ጋናን፣ የኢራን ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራይሲ ደቡብ አፍሪቃን፣የጀርመን የሐገር ዉስጥ ሚንስትር ሞሮኮን ጉብኝተዋል። ጎብኝተዋል።

የጉብኝት፣ ዉይይት፣ ስምምነቱ ጥቅል ይዘት በአብዛኛዉ የየጎብኚዎቹን መንግስታት ጥቅም ለማስከበር መሆኑ አያነጋግርም።ይሁንና አስተናጋጆቹ የአፍሪቃ መንግስታትም አጋጣሚዉን የየራሳቸዉን ጥቅም ለማስከበር አይጠቀሙበትም ማለት አይደለም።በየተራ ግን ባጫጭሩ እንየዉ።

                       የኢራንና የደቡብ አፍሪቃ ግንኙነት

 

የሁለቱ ሐገራት ግንኙነት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ነዉ።ይሁንና በ1979 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች ስልጣን ሲይዙ ኢራን በደቡብ አፍሪቃ ጥቁር ሕዝብ ላይ የሚፈፀመዉን ግፍ በመቃወም ከደቡብ አፍሪቃዉ የነጭ ዘረኞች መንግስት ጋር የነበራትን ግንኙነት አቋረጠች።ማዕቀብ ጣለችም።

በ1994 ደቡብ አፍሪቃ ሁሉን ዘር አቀፍ መንግስት ስትመሰርት የሁለቱ ሐገራት ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ ግንኙነት ቀጥሎ የንግድ ልዉዉጣቸዉም እያደገ መጣ።ደቡብ አፍሪቃ ወደ ኢራንየምትልከዉ ሸቀጥ በ2007 ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በልጧል።በዚያዉ ዓመት ደቡብ አፍሪቃ ከኢራን ወደ 21 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ነዳጅ ዘይት ገዝታለች።

ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራይሲ ባለፈዉ ነሐሴ ደብብ አፍሪቃ ባስተናገደችዉ የBRICS ጉባኤ ላይ ተካፍለዋ።በዚያዉ ወቅት ደቡብ አፍሪቃና ኢራን የጋራ የትብብር ኮሚሽን (JCC) ያሉትን ትብብር መስርተዋልም።

የኢራኑ ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራይሲና የዚምባቤዌዉ ፕሬዝደንት ኤምርሰን ምናንጋግዋምስል Iran's Presidency/Mohammad Javad Ostad/WANA/REUTERS

ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ቻይና ሕንድና ደቡብ አፍሪቃን በአባልነት የሚያስተናብረዉ ማሕበር በመጪዉ ጥር በአባልነት ከሚቀበላቸዉ 6 ሐገራት ኢራን አንዷ ሆናለችም።የእስላማዊ ማዕከል ለአፍሪቃ የተሰኘዉ አጥኚ ተቋም የበላይ ኃላፊ ሳይድ ሆሴይኒ እንደሚሉት የኢራኑ ፕሬዝደንት ሰሞኑን በደቡብ አፍሪቃ ያደረጉት ጉብኝትም የሁለቱን ሐገራት ግንኙነት ከማጠናከር አልፎ እስላማዊቱ ሪፐብሊክ ለብሪክስና አባል ሐገራትና ለአፍሪቃ ያላትን ሥልታዊ ጠቀሜታም ለማሳየት ያለመና ለማጠናከር የሚረዳ ነዉ።

«ኢራን ለመካከለኛዉ ምስራቅ፣ ለደቡብ እስያ እጅግ ስልታዊ በሆነ ሥፍራ ትገኛለች።ሕንድና ሩሲያን በደቡብ-ሰሜን መተለላፊያ በኩል ማገናኘት ትችላለች።ቻይናንም ከፋርስ ባሕረሰላጤ ጋር አገናኝታ፣ ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ ጋር ደቡብ አፍሪቃንና የተቀረዉን ዓለም ታገናኛለች።»

                                    የራይሲ የዉጪ መርሕ

በ2021 ሥልጣን የያዙት ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራይሲ በሰበብ አስባቡ ሐገራቸዉን ከሚወነጅል፣ ከሚቃጣና ከሚያሳጣዉ ከምዕራቡ ዓለም ጋር መነታረኩን እያሉ ግንኙነታቸዉን ከቻይና፣ከሩሲያ፣ከሌሎች የእስያ ሐገራት፣ከደቡብ አሜሪካና ከአፍሪቃ ሐገራት ጋር ለማጠናከር እየተጣጣሩ ነዉ።

ከ2005 እስከ 2013 ሥልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዝደንት ማሕሙድ አሕመድኒጃድ ተመሳሳይ የዉጪ መርሕ ለመከተል ሞከረዉ ነበር።ይሁንና  ያኔ ኢራን የኑክሌር ቦምብ ለመስራት ታታሴራለች፣ አሸባሪዎችን ታስታጥቃለች፣ በሌሎች ሐገራት የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ ትገባለች የሚለዉ የዋሽግተን-መራሹ ዓለም ዉንጀላና ጫና ሌላዉን ዓለም ስላስፈራ የቴሕራች ጥረት ብዙም ተቀባይነት አላገኘም ነበር።

ኢራንና ኃያላኑ መንግስታት የቴሕራንን የኑክሌር መርሐ-ግብርን ለማስቆም በ2015 የተፈራረሙትን ስምምነት ዩናይትድ ስቴትስ በ2018 ካፈረሰች ወዲሕ ግን ጠቡን  ከሩቅና በፍርሐት ይከታተል የነበረዉ ዓለም ኢራንን ይበልጥ እያቀረበና እየተቀበላት ነዉ።ፕሬዝደንት ራይሲም ሐገራቸዉ በተለይ ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳዳግ አጋጣሚዉን እየተጠቀሙበት ነዉ።

                                       ኢራንና አፍሪቃ

የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳስታወቀዉ አምና የማሊ፣የታንዛኒያ፣የደቡብ አፍሪቃና የኒዤርን ጨምሮ የ47 የአፍሪቃ ሐገራት ባለሥልጣናት ቴሕራን ጎብኝተዋል።ፕሬዝደንት ራይሲ በበኩላቸዉ ባለፈዉ ሐምሌ ኬንያ፣ዩጋንዳና ዝምባቡዌን ጎብኝተዋል።በጉብኝቱ ወቅት ኢራን ከ3ቱ የአፍሪቃ ሐገራት ጋር 21 የትብብር ስምምነቶችን ተፈራርማለች።

ኢራን በ2020 ከአፍሪቃ ጋር የነበራት የንግድ ልዉዉጥ 579 ሚሊዮን ዶላር ነበር።በ2022 ወደ 1.28 ቢሊዮን ከፍ ብሏል።በ2023 ደግሞ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ይደፍናል ተብሎ ይጠበቃል።ዋናዋ ደቡብ አፍሪቃ ናት።የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሆሴይን አሚር-አብዶላሒያን በቅርቡ እንዳሉት ሐገራቸዉ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት በሁሉም መስክ ማሳደግ ትፈልጋለች።

«የኢራን እስላማዊት ሪፐብሊክ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር በሳይንስ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂን በማሳደግ፣ በቴክኖሎጂ፣ በባሕል፣ በሐገር ጉብኝት፣ በምጣኔ ሐብት፣ በንግድ፣ በኃይል ምንጭ ልዉዉጦችና በሁሉም  መስኮች ያላትን ትብብር ለሁለቱ ሐገራት በሚጠቅም መልኩ ያለምንም ገደብ ማሳደግ ትፈልጋለች።»

ዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮችዋ ኢራንን አሸባሪዎች ትደግፋለች፣ እስራኤልን ትጠላለች፣ ከሩሲያ ጎን ተሰልፋለች ወዘተ እያሉ አሁንም እየወነጀሏት ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ የጣለችባት ተደጋጋሚ ማዕቀብም እልተነሳም።ኢራን በምዕራባዉያን መንግስታት በምትወነጀል፣ በምትቀጣና በምትወገዝበት መሐል ከአፍሪቃ በጣሙን ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ግንኙነቷን ማጠናከሯ የዶቸ ቬለዉ ቱሶ ኹማሎ እንደዘገበዉ የብዙችን ቅንድብ ሽቅብ ማስገለጡ አልቀረም።ይሁንና ባለፈዉ ወር ቴሕራንን የጎበኙት የደቡብ አፍሪቃዋ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚንስትር ናሌንዲ ፓንዶር እንዳሉት ቴሕራንና ፕሪቶሪያ ከራሳዋ ጋር ሠላም ከፈጠረች ዓለም ዉጪ ሌላ አይመኙም።

«ዓላማችን፣ ሁለታችንም፣ እንደ ደቡብ አፍሪቃም፣ እንደ ኢራን እስላማዊት ሪፐብሊክም፣ ዓለም ከራሷ ጋር ሰላም እንድትፈጥር ማበረታት ነዉ።ለሰዉ ልጆች በሙሉ የሰላምና የደሕንነት ድባብ እንዲፈጠር ማበረታት ነዉ።»

                          የጀርመን መሪዎች የአፍሪቃ ጉብኝት

የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር ከበርሊን ቁል ቁል ወደ ታንዛኒያ ወርደዉ ጀርመን ታንዛኒያን ቅኝ ትገዛ በነበረበት ዘመን በታንዛኒያ የነፃነት ተፋላሚዎች ላይ ለፈፀመችዉ ግድያና ግፍ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።የጀርመን የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ናንሲ ፌዘር በፋንታቸዉ የሜድትራኒያን ባሕር ተሻግረዉ ከሞሮኮ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል።

ወይዘሮ ፌዘር ከሞሮኮ ባለስልጣናት ጋር ያደረጉት ዉይይት «የሁለቱ ሐገራትን ግንኙነት ለማጠናከር» በሚል ጥቅል ርዕስ ቢሸፋፈንም ዋና አላማዉ የሜድትራኒያንን ባሕር አቋርጠዉ አዉሮጳ የሚገቡ በአብዛኛዉ የአፍሪቃ ስደተኞችን ሞሮኮ እንድታግድ፣ አዉሮጳ ከገቡ በኋላ መመለስ የሚገባቸዉን ሞሮኮ እንድትቀበል የራባት ባለስልጣናትን ለማግባባት በገንዘብ ለማባበልም ነበር።ታዛቢዎች እንደሚሉት የሚንስትሯ ጥረት ከግማሽ በላይ ብዙም የተሳካ ዓይነት አይደለም።

የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስና የናጄሪያዉ ፕሬዝደንት ቦላ ቲኑቡምስል Nosa Asemota/Nigeria State House/AP/picture alliance

መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ደግሞ ምዕራብ አፍሪቃ ነበሩ።ናጄሪያና ጋና።የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፖለቲከኛ ኦላፍ ሾልስ ሐቻምና ታሕሳስ የመራሔ መንግስትነቱን ሥልጣን ከያዙ ወዲሕ የአፍሪቃ ሐገራትን ሲጎበኙ የሰሞኑ ሶስተኛቸዉ ነዉ።

ያሁኑ ጉብኝት ከፖለቲካ ዲፕሎማሲዉ ይልቅ ምጣኔ ሐብታዊ በጣሙን ደግሞ የናጄሪያን ነዳጅ ዘይትና ጋስ ሸመታ እንደሆነ በግልፅ እየተዘገበ ነዉ።ሾልስ ራሳቸዉም አቡጃ ናጄሪያ ዉስጥ ባደረጉት ንግግር  የጉብኝታቸዉ ዓብይ ዓላማ ጀርመን ከናጄሪያ ጋር ያላትን የንግድ ልዉዉጥ ለማሳደግ እንደሆነ አረጋግጠዋል።

«ናጄሪያ ለጀርመን ምጣኔ ሐብት በጣም አስፈላጊና የቅርብ ሸሪክ ናት።ባለፉት ዓመታት የሁለቱ ሐገራት የንግድ ልዉዉጥ በ50 ከመቶ ጨምሮ፣ ከ2 ወደ 3 ቢሊዮን ዩሮ ከፍ ብሏል።ይሕ ጥሩ ምልክት ነዉ።ግን ከዚሕ በላይ መጨመር አለበት።ኩባንዮቻችን የንግድ ልዉዉጡን ይበልጥ የማሳደግ አቅም እንዳላቸዉ እገነዘባለሁ።»

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ከአምና የካቲት ጀምሮ የአዉሮጳ ትልቅ ኤኮኖሚ ጀርመን ከሩሲያ ጋስ ጥገኝነት ለመዉጣት የተለያዩ አማራጮችን እያማተረች ነዉ።ከአፍሪቃ በርካታ  ነዳጅ ዘይትና ጋስ የምትሸጠዉ ናጄሪያ የበርሊን ፖለቲከኞችንና ኩባንዮችን ትኩረት መሳቧም ብዙ አላስደነቀም።ሾልስ መጀመሪያ ናጄሪያ ቀጥለዉ ወደ ጋና የሔዱትም በተለይ በነዳጅ ዘይት፣ጋስና በመሰል የኃይል ምንጮች ላይ የሚሰሩና የሚነግዱ የበርካታ የኩባንያ ባለቤቶችንና ተጠሪዎችን አስከትለዉ ነዉ።

የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ታንዛኒያን በጎብኙበት ወቅትምስል Bernd von Jutrczenka/dpa/picture alliance

                       ነዳጅ ዘይትና ጋስ 

ሾልስ አቡጃን የጎበኙት የአፍሪቃዋ የሕዝብ አንደኛ ሐገር ናጄሪያ በፀጥታ መታወክ፣ በሙስናና በፖለቱካ ምስቅልቅል ምጣኔ ሐብቷ ባሽቆለቆለበት፣የመሠረተ ልማት አዉታሯ በጣሙን የጋስና የነዳጅ ዘይት ማምረቻና ማጓጓዢያ ተቋማትዋ ጥገና በሚሹበት ወቅት ነዉ።

ናጄሪያ ከምጣኔ ሐብቷ ማሽቆልቆል በተጨማሪ እንደ ምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ECOWAS) መሪ ሐገር ከማሊ እስከ ኒዤር የሚገኙ የአካባቢዉን ሐገራትን ያመሰቃቀለዉን መፈንቅለ መንግስት ለመግታት በምትጣጣርበት መሐል ከአዉሮጳ ትልቅ ኢኮኖሚ ሸማች ሲመጣላት «ሳይደግስ አይጣላም» ዓይነት የማትልበት ምክንያት የለም።ፕሬዝደንት ቦላ ቲኑቡ ደስታቸዉን አልሸሸጉም።

«የበርካታ የግል ኩባንያ መልዕክተኞችም መጥተዋል።እዚሕ ናጄሪያ ዉስጥ መወረት ይፈልጋሉ።ይሕ አስደሳች ነዉ።ናጄሪያ የአፍሪቃ ትልቅ ኤኮኖሚ በመሆንዋ ከአዉሮጳ ትልቅ ኤኮኖሚ ማለትም ከጀርመን ሪፐብሊክ ጋር መሻረክ ትፈልጋለች።»

መራሔ መንግስት ኦልፋ ሾልስ የመሩት የመልዕክተኞች ጓድ ከጋና አስተናጋጆቹ ጋር ያደረገዉ ዉይይትም በምጣኔ ሐብቱ ትብብርና በንግድ ልዉዉጡ  ላይ ያተኮረ ነዉ።በ2022 ጀርመን 315 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሸቀጥ ወደ ጋና ልካለች።ሾልስ ከጋናዉ ፕሬዝደንት ናና አኩፎ አዶ ጋር ባደረጉት ዉይይት የንግድ ሽርክናዉን ለማሳደግ የሚረዱ ሐሳቦችን ተለዋዉጠዋል።

ሾልስ በጋና ጉብኝታቸዉ ምስራቃዊ ጋና ዉስጥ ከሚገኘዉ ከአሼሲ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር ባደረጉት ዉይይትም ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር እንደምትሻ ለተማሪዎቹ አስረድተዋል።

የጀርመን መራሔ መንግስት ከጋና ፕሬዝደንት ጋርምስል picture alliance/dpa

ጀርመን የአፍሪቃ ሕብረን በገንዘብ ከሚደገፉ ምዕራባዉያን መንግስታት ግንባር ቀደሟ ናት።የወቅቱን የቡድን 20ን የሊቀመንበርነት ሥልጣን የያዙት ሾልስ ከሁለት ሳምንት በኋላ በርሊን ዉስጥ የሚደረገዉን የቡድን 20ና የአፍሪቃ ሐገራት የመሪዎች ጉባኤን ያስተናግዳሉ።ታዛቢዎች እንደሚሉት ሾልስም ሆኑ ፕሬዝደንት ቫልተር ሽታይንማየር ከጉባኤዉ በፊት አፍሪቃን መጎብኝታቸዉና ስለ አፍሪቃ ያስተላለፉት በጎ መልዕክት አፍሪቃዉያንን ለማማለል ጠቃሚ ነዉ።

«አፍሪቃ ጎረቤታችን አሐጉር ናት።ይሕ ለኛ ለመላዉ ዓለምም ትልቅ ትርጉም አለዉ።ናጄሪያ ደግሞ ከአሐጉሪቱ በርካታ ሕዝብ የሚኖርባት ሐገር፣ አፍሪቃ ዉስጥና በመላዉ ደቡባዊ ክፍለ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደር ናት።በሁለቱ ሐገሮቻችን መካከል ያለዉ ግንኙነት ጥሩ ነዉ።በዚሕ ጉብኝቴ ደግሞ በጀርመንና በናጄሪያ መካከል ያለዉን ይሕን ግንኙነት ይበልጥ ለማስፋትና ለማጠናከር እሻለሁ።»

የብሪታንያ፣ ኢራንም ሆኑ፣ ጀርመን መሪዎችና ሚንስትሮች በየደረሱበት የአፍሪቃ ሐገራት የሚሉትን ብለዉ ወደየ ሐገራቸዉ ተመልሰዋል።ከተነገሩት ብዙ ገቢር የሚሆነዉን ስንትነት በርግጥ ጊዜ ነዉ በያኙ።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW