1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመንና ፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትሮች ጉብኝት በኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ ጥር 4 2015

የአውሮጳ ሁለቱ ጠንካራ ሀገሮች የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለሥራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ ገቡ። ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከርእሠ ብሔር ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች መነጋገራቸው ታውቋል።

Äthiopien Adama | Getreidelager UN-Welternährungsprogramm | Annalena Baerbock & Catherine Colonna AUFGEHELLT
ምስል Florian Gaertner/photothek/picture alliance

ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል

This browser does not support the audio element.

የአውሮጳ ሁለቱ ጠንካራ ሀገሮች የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለሥራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ ገቡ። ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከርእሠ ብሔር ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች መነጋገራቸው ታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከፈረንሳይ የአውሮፓ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎንና እና ከጀርመን የፌደራል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ባየርቦክ ጋር እንደተነጋገሩ እና ያደረጉት «ጥልቅ እና ፍሬያማ» ያሉት ውይይት «ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ እና ከጀርመን ጋር ያላትን ጠንካራ እና የቆየ ግንኙነት የሚያንፀባርቅ ነው» ብለዋል። ሁለቱ የአውሮጳ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዛሬ ከቀትር በኋላ ዩክሬን ለኢትዮጵያ የለገሰችው ስንዴ ጨምሮ ሌሎች ሀገሮች የለገሰት የእርዳታ እህል የተከማቸበትን አዳማ የሚገኘውን የአለም የምግብ ፕሮግራም ( WFP ) ትልቁ የኢትዮጵያ መጋዘንን በጋራ ጎብኝተዋል። በነገው እለት ደግሞ ከአፍሪካ ኅብረት ባለስሥልጣናት ጋር ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል። 

የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት የሰላም ስምምነት ማድረጋቸውን ተከትሎ አውሮፓ በኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱን ለሁለቱም ሀገሮች አስፈላጊ ነው ሲሉ ዛሬ ከፈረንሳይ አቻቸው ጋር አዲስ አበባ የገቡት የጀርመን የፌደራል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ባየርቦክ ተናግረዋል። 

የጀርመን እና የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትሮች ከጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ጋርምስል Florian Gärtner/imago images/photothek

ከርእሠ ብሔር ሳኅለ ወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር የተወያዩት ሚኒስትሯ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና የአውሮፓ ህብረት እ.ኤ.አ. በ2018 በጀመሩት የሰላም፣ የዲሞክራሲ እና ቀጣይነት ያለው ልማት ኢትዮጵያን እንዴት ሊደግፉ እንደሚችሉ ለመወያየት አላማ ይዘው እዚህ መምጣታቸውን ቀድመው ተነግረዋል።

በአዳማ ዩክሬን ለኢትዮጵያ የለገሰችውን ጨምሮ የሌሎች ሀገሮች እና ረጂ ድርጅቶች የሰብዓዊ ድጋፍ የተከማቸበትን በአለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) የኢትዮጵያ ዋናውን መጋዘን በጎበኙበት ወቅት ይህንኑ ገልፀዋል።

በአፍሪካ ህብረት እና በአውሮፓ መካከል ያለውን አጋርነት አጠናክረን መቀጠል እንፈልጋለን ያሉት ሚኒስትሯ አውሮፓን የሚያስጨንቀው ነገር ብዙውን ጊዜ በአፍሪካ አህጉር ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ እንዳለውና በዩክሬን ላይ የሩስያ የጥቃት ጦርነት ያስከተለው የምግብ ዋጋ መናር በተጨማሪም የአየር ንብረት ቀውስ ያስከተለውን ተጽእኖ በግልጽ እንደሚታይ ይህንንም በጋራ በመሥራት ብቻ ነው መቆጣጠር እንደሚገባ ነው የገለፁት። 
የፈረንሳይ ሪፐብሊክ የአውሮፓ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና ኢትዮጵያን በመጎብኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ የጉዟቸው አላማችን የሰላሙን ሂደቱን እና መልሶ ግንባታን ለመደገፍ ነው ብለዋል። 

የጀርመን እና የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትሮች የዓለም ምግብ መርኃ ግብር የእህል መጋዘንን ሲጎበኙምስል Florian Gaertner/photothek/picture alliance

የሁለቱም ሀገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሩሲያ በዩክሬንን ላይ የከፈተችው ያሉት ጦርነት ኢትዮጵያን ጨምሮ መላውን አለም በምግብ እጥረት እንዲቸገር ማድረጉን ገልፀዋል። ጀርመንና ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ በሌሎች ዘርፎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እና በተለይ በጦርነት፣ በድርቅ፣ እና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ለችግር የተጋለጠውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ለማገዝ እንዲችል ለአለም ምግብ ፕሮግራም እገዛቸውን እንደሚያጣናክሩ ቃል ገብተዋል። 

ዩክሬን ለሶማሊያ የለገሰችውን ስንዴ ለማጓጓዝ ፈረንሳይ፣ በተመሳሳይ ዩክሬን ለኢትዮጵያ የለገሰችውን ስንዴ ለማጓጓዝ ደግሞ ጀርመን የትራንስፖርት ወጪዎችን መሸፈናቸው ይታወሳል።

ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ማምሻውን ከኢትዮጵያ ምክትል እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በጋራ በጉብኝታቸው ዙሪያ መግለጫ ይሰጣሉ። በነገው እለት ደግሞ ከአፍሪካ ሕብረት ባለስሥልጣናት ጋር ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ  

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW