የጀርመን መሪዎች የአፍሪቃ ጉብኝትና ይቅርታ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 21 2016የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር በ ሀገራቸው የቅኝ ግዛት ዘመን ታንዛኒያ ውስጥ ለተፈጸመው ወንጀል ዛሬ በይፋ ይቅርታ ጠየቁ። ሽታይን ማየር በውቅቱ በተፈጸመው ወንጀል ማፈራቸውን በመግለጽም ጀርመን ውስጥ ስለድርጊቱ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል። ታንዛኒያ ከጎርጎሪዮሳዊው 1905 እስከ 1907 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት በጀርመን ሥር ከነበሩና በታሪክ ደም አፋሳሽ ጸረ ቅኝ ግዛት አመጽ ከተካሄደባቸው የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት አንዷ ናት። በወቅቱም የማጂ ማጂ አመጽ ተብሎ በሚታወቀው የጸረ ቅኝ አገዛዝ አመጽ ከ200 እስከ 300 ሺህ የሚገመቱ ነባር የአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸውን የታሪክ ምሁራን ይገልጻሉ። «ጀርመኖች በቀደምት አያት ቅድመ አያቶቻችሁ ላይ ለፈጸሙት ይቅርታ እጠይቃለሁ» ያሉት ሽታይን ማየር፤ ያለፈው ታሪክ በተመለከተ ሀገራቸው ከታንዛኒያ ጋር አብራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኗንም ተናግረዋል። ጀርመን እና ታንዛኒያ የሚጋሩት ታሪክ እንዳለም በማመልከት በሶንጋ ከተማ በማጂ ማጂ ቤተመዘክር የተመለከቱትን ወደ ሀገራቸው ወስደው ለህዝባቸው እንደሚያጋሩም ገልጸዋል። የጀርመን ፕሬዝደንት ሦስት ቀናት የታንዛኒያ ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁም፤ በቅኝ ግዛት ዘመን ወደ ጀርመን የተወሰዱ የሀገሪቱን ቅርሶች ለመመለስ የሚያስችል መንገድ መክፈታቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
በተያያዘ ዜና የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ በናይጀሪያ እና ጋና ያደረጉትን ጉብኝት ጨርሰው መመለሳቸው ተሰምቷል። ሾልስ የጉብኝታቸው ማጠናቀቂያ በሆነችው ጋና ትናንት ባደረጉት ንግግር ሀገራቸው ጀርመን እና የአውሮጳ ኅብረት በጋራ የምዕራብ አፍሪቃን ጸጥታ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን፤ ጅሃዲስቶች የሚያደርሱትን ጥቃት ለመከላከልም የስልጠና እና የመሣሪያ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። በቅርቡ በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት በተከታታይ የተካሄዱት መፈንቅለ መንግሥታት በሃገራት መካከል የነበረውን ትብብር እንዳቀዘቀዘው በማመልከትም፤ አጋጣሚው ለታጣቂዎች ዕድል እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ይልማ ኃይለ ሚካኤል/ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ