1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጀርመን መራኄ መንግሥት፦ ስለዩክሬን፣ ፕሬዚደንት ትራምፕ ዕቅድ እና አፍሪቃ ምን አሉ?

ማክሰኞ፣ ኅዳር 16 2018

በደቡብ አፍሪቃ ጁሐንስበርግ ከተማ በተካሄደው የቡድን 20 ጉባኤ ማጠቃለያ ላሽ የጀርመን መራኄ-መንግስት ፍሬድሪሽ ሜርትስ ዩናይትድ ስቴትስ ባለ 28 ነጥብ ዕቅድ በሚል ዩክሬንን በሚመለከት ስላቀረበችው የስምምነት ሐሳብ፤ ስለ አውሮጳውያን ምላሽ እና ሌሎች ጉዳዮችም ማብራሪያ ሰጥተዋል ።

የቡድን 20 አገራት 20 መሪዎች በደቡብ አፍሪቃ ጆሐንስበርግ ከተማ በተኪያኼደው ጉባኤ
የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርትስን ጨምሮ የቡድን 20 አገራት 20 መሪዎችና ተወካዮች በደቡብ አፍሪቃ ጆሐንስበርግ ከተማ በተኪያኼደው ጉባኤምስል፦ Michael Kappeler/dpa-Pool/dpa/picture alliance

አውሮጳ ተጽእኖ የማሳረፍ ምን አቅም አላት? ቃለ መጠይቅ ከጀርመን መራኄ መንግሥት ጋር

This browser does not support the audio element.

በደቡብ አፍሪቃ ጁሐንስበርግ ከተማ ለሁለት ቀናት ተካኺዶ እሁድ ኅዳር 14 ቀን፣ 2018 ዓ.ም በተጠናቀቀው የቡድን 20 ጉባኤ የተሳተፉት የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርትስ ከዶይቸ ቬለ የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርቦላቸው ነበር ። ፍሬድሪሽ ሜርትስ ዩናይትድ ስቴትስ ባለ 28 ነጥብ ዕቅድ በሚል ዩክሬንን በሚመለከት ስላቀረበችው የስምምነት ሐሳብ፤ ስለ አውሮጳውያን ምላሽ እና ሌሎች ጉዳዮችም ማብራሪያ ሰጥተዋል ።

ዩናይትድ ስቴትስ ሩስያ በዩክሬን የምታካሂደዉን ጦርነት ለማስቆም በሚል ከሰሞኑ ባለ 28 ነጥብ የሰላም እቅድ ማዘጋጀቷን ይፋ አድርጋለች ። የአዉሮጳ ኅብረት ይህን እቅድ ተቃውሞታል ። የራሴ ያለውን እቅድም አቅርቧል ። ተንታኞች ዩናይትድ ስቴትስ ከዩክሬይን ይልቅ ከሞስኮ ጋር የበለጠ  ወዳጅነት እንዳላት እና ዕቅዱ ይበልጥ ለሩስያ ያደላ ነው ሲሉ አስተያየት ሰንዝረዋል ።

የዶይቸ ቬለዋ ሚሻኤላ ኩይፍነር ጁሐንስበርግ ውስጥ ለመራኄ-መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርትስ ያቀረበችላቸውን ሙሉ ቃለ መጠይቅ እንደሚከተለው ተርጉመን አቅርበንላችኋል ። ሚሻኤላ ኩይፍነር ጥያቄዋን የምታንደረድረው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት የዩክሬን ጦርነትን ለማክተም ሲሉ ያቀረቡትን የዩክሬን ባለ 28 ነጥብ ዕቅድ በመጥቀስ ነው ።  

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን ባለ 28 ነጥብ ዕቅድ

«የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርትስ እዚህ አጠገቤ ይገኛሉ ። የማነጋግራቸው የG20 ጉባኤ እዚህ ጆሐንስበርግ ውስጥ ልክ እንደተጠናቀቀ ነው ። መራኄ-መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርትስ የG20 ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደባት የአፍሪቃ ምድር ረዥም ጊዜ የሰጡት ስለ ዩክሬን አንገብጋቢ ጉዳይ በማንሳት ነው ። ስለ G20 በኋላ ላይ እንወያያለን፥ ሆኖም እስኪ በቅድሚያ በዩክሬን ባለ 28 ነጥብ ዕቅድ የተነሳ በአሁኑ ወቅት በአውሮጳ ላይ የተደቀነውን ሥጋት መጠን ሊገልጡልን ይችላሉ?»

ፍሬድሪሽ ሜርትስ፦ «ደህና፦ ስለዚህ ባለ 28 ነጥብ ዕቅድ ያወቅነው ካለፈው ዐርብ ጀምሮ ነው ። ከጀርመን ከመውጣቴ ቀደም ብሎ ከፕሬዚደንት ትራምፕ ጋር በስልክ ተነጋግረናል ። በአንዳንዶቹ ጉዳዮች ላይ ልንስማማ እንደምንችል፤ ሆኖም ሌሎች ልንስማማባቸው የማንችላቸው ጉዳዮች እንዳሉም ነግሬቸዋለሁ ። እናም ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ከዩክሬን ጎን መቆማችንን፤ የአገሪቱ ሉዓላዊነት ሊጣስ እንደማይገባ፣ በአሁኑ ወቅት ጄኔቫ ውስጥ በሚካሄድ  ብርቱ ድርድር መሀል እንደምንገኝ ነግሬያቸዋለሁ ። እዚያ የሚገኙ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪዎቻችን ከአሜሪካ ልዑካን ጋር፤ ከዩክሬን ልዑካን ጋር  እየተነጋገሩ ነው፥ እናም  ከዚህ ንግግር ምን ውጤት ሊገኝ እንደሚችል ዐናውቅም ። ንግግሩ ሲጠናቀቅ  የዩክሬን ሉዓላዊነት ምናልባት ጥያቄ ውስጥ ላይገባ ይችላል ። »     

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን ባለ 28 ነጥብ ዕቅድ ውጤቱ ምን ይሆን?ምስል፦ Ron Sachs/Newscom World/IMAGO

ይህ ለአውሮጳ ምን ማለት ይሆን?

ፍሬድሪሽ ሜርትስ፦ «አሁንም ድረስ እየተሰቃየን ነው፤ በ... በዩክሬን መሪር ጦርነት የተነሳ ካለፉት አራት ዓመታት ግድም ጀምሮ እየተሰቃየን ነው ። ጦርነቱ ለሁላችንም ሥጋት ነው ። በመሠረተ-ልማቶቻችን ላይ ብርቱ ጥቃቶችን ዕያየን ነው ። በሳይበር ደኅንነታችን ላይ ከፍተኛ ጥቃቶችን ዕያየን ነው ። ስለዚህ ይህ ማለት...ይህ ማለት ለመላው የአውሮጳ አኅጉር  አጠቃላይ የፖለቲካ መዋቅር ጥልቅ የሆነ ሥጋት ነው ። በዚያም የተነሳ ነው እጅግ ጠልቀን የገባንበት ። ለዚያም ነው ይህን አሰቃቂ ጦርነት ለማክተም እየሞከርን ያለነው ።»  

ሚሻኤላ ኩይፍነር፦ «ይህ እስከ ሐሙስ በቀላሉ ሊሆን የማይችል ነው ሲሉ ማስጠንቀቅዎትን እንደቀጠሉ ነው ። ሐሙስ በዩናይትድ ስቴትስ የምስጋና ቀን ነው ። ያን ቀነ-ገደብም ነው  ዶናልድ ትራምፕ ማየት የሚሹት ። የራስዎትን ምክረ_ሐሳብ እንደሚያዘጋጁም ፍንጭ ሰጥተዋል ። አነስ ያለ ርምጃ ብጤ ነው ። ያን ሊያብራሩልን ይችላሉ?» 

ፍሬድሪሽ ሜርትስ፦ «እንደሚመስለኝ በሁሉም ባለ 28 ነጥቦች ዕቅድ እስከ ሐሙስ ድረስ መስማማቱ የሚሳካ አይደለም ።  ለዚህም ነው የዕቅዱ የትኛው ክፍል ያለአንዳች ተቃውሞ በአውሮጳውያን፤ በአሜሪካውያን እና በዩክሬናውያን በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሩስያውያን ሊሳካ ይችላል የሚለውን ለማጤን እየሞከርን ያለነው ። ይህንን እጅግ ውስብስብ የሆነውን ነገርም ነው እያጤንን ያለነው ።  ግን ደግሞ ቀደም ሲል እንዳልሁት፦ ወደፊት መጓዝ፤ ይህን አስከፊ ጦርነት ማቆም ይገባናል ። ለዚያም ነው እስከ ሐሙስ ድረስ አሸማጋይ ጉዳዮችን ለማቅረብ እየሞከርን ያለነው ። እናም አሁን ፕሬዚደንት ትራምፕ እስከ ሐሙስ ድረስ ቢያንስ አሸማጋይ ውጤት ለማግኘት  የምር መጓጓታቸውን ገልጠዋል ። ሁላችንም ለማሳካት የምንጥረው ያንኑ ነው ።» 

አውሮጳ  ተጽእኖ የማሳረፍ ምን አቅም አላት?

ሚሻኤላ ኩይፍነር፦ «ይህ ከአውሮጳውያን ርእሳነ-ብሔር፤ ውጪ፤ ከአውሮጳውያን መሪዎች ውጪ፤ ያለ አውሮጳውያን ስምምነት ሊሆን የማይችል ነው ብለዋል፤ ግን ደግሞ በዚያ ረገድ አውሮጳ  ተጽእኖ የማሳረፍ ምን አቅም  አላት?»

ፍሬድሪሽ ሜርትስ፦ «እንግዲህ እዚህ ዕቅድ ውስጥ በአውሮጳውያን በኩል ስምምነትን የሚሹ በርካታ ጉዳዮች አሉ ። አብነቶችን ልጠቅስልሽ እችላለሁ፦ ብራስልስ ውስጥ የሚገኘው የሩስያ ሐብት ለአሜሪካኖች ተከፋይ ሊሆን አይችልም ። ያ የማይታሰብ ነው ። ስለዚህ ይህ እቅድ የሚተገበር ከሆነ የአውሮጳውያን ድጋፍ እጅጉን ያስፈልጋል ። በዚያም የተነሳ ነው ለድርድር ጠረጴዛው ፊት የተቀመጥነው ።»  

ሚሻኤላ ኩይፍነር፦ «ቀደም ሲል ንግድ ላይ ለሚያተኩረው የG20 ጉባኤ  እንግዳ በሆነ መልኩ አሁን በእዚህ የG20 የወቅቱ ፕሬዚደንት ጉባኤ መዝጊያ  ዓለም አቀፍ ሕግ፤ የሰብአዊነት ሕግ፤ ደንቦችን መሰረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ሥርዓት አጽንዖት ተሰጥቶባቸው ነው የተጠናቀቀው ። ሲሪል ራማፎሳ በአጠቃላይ መግለጫ በመስጠት ዩናይትድ ስቴትስን ተቋቁመዋል ። ይህች አፍሪቃ ብዙ አቅም ያላት ናት። አፍሪቃውያን ከእንዲህ ዓይነቱ አብሮነት ምን ያገኛሉ?»  

በደቡብ አፍሪቃ ጆሐንስበርግ ከተማ በተኪያኼደው የቡድን 20 ጉባኤ የተነሳ የዓለም የተለያዩ መሪዎች ፎቶምስል፦ Gianluigi Guercia/AFP/Getty Images

የቡድን 20 ጉባኤ በደቡብ አፍሪቃ ጆሐንስበርግ ከተማ 

ፍሬድሪሽ ሜርትስ፦ «ይህ ደቡብ አፍሪቃ ጆሐንስበርግ ከተማ ውስጥ የተካኼደው የG20 ጉባኤ አፍሪቃን በተመለከተ ስለ ተሰሚነቷ ባለን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ላይ ጥልቅ ለውጥ አስመዝግቧል ። አፍሪቃ  በመጻዒ ጊዜው ከፍ ያለ ሚና መጫወት እንደሚገባት ጥልቅ ግንዛቤ ሳይኖረው ከዚህች አገር የወጣ ማንም የለም ። ይህች ወጣት የበዛበት ሕዝብ ያላት በፍጥነት እያደገች ያለች አኅጉር ናት ። ለንግድ እጅግ ሳቢ ናት፤ ግን ደግሞ ወደ ድርድሩ ቀርበዋል፤ እዚያ ይገኛሉ፤ እናም ከባለፈው ይልቅ ይበልጥ ከፍ ያለ ሚና ይጫወታሉ ።»

ሚሻኤላ ኩይፍነር፦ «እናም በስተመጨረሻ፦ የቻይና ጠቅላይ ሚንሥትር ሊ ሺያንግን አነጋግረዋልና ዩክሬንን በተመለከተ ቻይና ሩስያን በማግባባቱ ረገድ ስለሚኖራት ሚና ምን ተስፋ ሰንቀዋል?»

ፍሬድሪሽ ሜርትስ፦ «በሚቀጥለው ዓመት ወደ ቻይና ለሚኖረኝ ጉብኝት እየተዘጋጀሁ ነውና ቀደም ሲል ከቻይና ጠቅላይ ሚንሥትር ጋር ዘለግ ያለ ውይይት አድርገናል ። ቻይና ሚና ልትጫወት ትችላለች ። ይህን ጦርነት ለማክተም ቻይና ሩስያ ላይ ጫና ማሳደር ትችላለች ። እናም ከቻይና መንግሥት ጋር በነበረኝ ንግግር ወቅት ያ አንዱ የንግግራችን አካል ነበር፤ ካስፈለገም በሚቀጥለው ዓመት ከቻይና ፕሬዚደንት ጋር የሚኖረኝ ንግግር አካል ሆኖም ወደፊትም ይቀጥላል ። አንድ ነገር ግን እጅግ ተስፋ የማደርገው፤  በሚቀጥለው ዓመት ንግግራችን ላይ ጥላውን እንዳያጠላ፤  በዚህ ጦርነት ላይ ቢያንስ አስቀድሞ ተኩስ አቁም እንደሚኖር ነው ።»

 ሚሻኤላ ኩይፍነር፦ «መራኄ-መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርትስ፤ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ ።»

ፍሬድሪሽ ሜርትስ፦ «እኔም አመሰግናለሁ ።»

ማንተጋፍቶት ስለሺ/ሚሻኤላ ኩይፍነር

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW