1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲስ መንግሥት ምስረታ ዝግጅት

ማክሰኞ፣ መስከረም 18 2014

ኤስ.ፔ.ዴ.ም ሆነ ሴ.ዴ.ኡ የመረጧቸው አረንጓዴዎቹና የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ አቋም የተለየየ መሆኑ በጥምር መንግሥት ምሥረታ ድርድር ላይ መግባባት መቻላቸው አስግቷል።አረንጓዴዎቹ የመንግሥትን ሥልጣን  በቀጥታ ለለውጥ ተጽእኖ እንዲያደርግ ግልጽ አቋም ነው ያላቸው።ነጻ ዴሞክራቶቹ ደግሞ የመንግሥት ስልጣን እንዲገደብ አቋማቸው ጠንካራ ነው።

Bundestagswahl 2021 | Olaf Scholz (L) und Armin Laschet (R) am Wahlabend
ምስል Wolfgang Rattay/Reuters & Martin Meissner/AP/picture alliance

የጀርመን ምርጫ ውጤትና የአዲስ መንግሥት ምስረታ ዝግጅት

This browser does not support the audio element.

ከትናንት በስተያ የተካሄደው የጀርመን ብሔራዊ ምርጫ አሸናፊ የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ኤስ.ፔ.ዴ እና የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ ሴ.ዴ.ኡ በየፊናቸው የመንግሥት ምስረታ ሙከራ ላይ መሆናቸውን ትናንት አስታውቀዋል።ሁለቱም ፣ከሁለት ተመሳሳይ አነስተኛ ፓርቲዎች ጋር ተጣምረው  መንግሥት መመስረት እንደሚፈልጉም ይፋ አድርገዋል።በዚህ የተነሳም ተሰናባቿን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ማን ሊተካ እንደሚችል ለጊዜው አልታወቀም ።
ባለፈው እሁድ በተካሄደው የጀርመን ብሔራዊ ምርጫ በጠባብ ልዩነት ያሸነፈው መሀል ግራው  የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ፣ ኤስ.ፔ.ዴ ለተፈጥሮ ጥበቃ ከሚሟገቱትና በአሁኑ ምርጫ 14.4 በመቶ ድምጽ ካገኙት ከአረንጓዴዎቹና 11.5 በመቶ ድምጽ ካሸነፉት ከነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲ ጋር ተጣምሮ መንግሥት የመመስረት ፍላጎት እንዳለው ጠቁሟል።በምርጫው ሁለተኛ ደረጃ ያገኘው ወግ አጥባቂዎቹና መሀል ቀኞቹ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረትና የክርስትያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲ ጥምረትም ከነዚሁ ሁለት ፓርቲዎች ጋር መንግሥት መመስረት የሚያስችል ንግግር ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ብሏል። ለሦስት የስልጣን ዘመናት ታላቁን ጥምረት መስረትው ሀገሪቱን የመሩት ሁለቱ አንጋፋ ፓርቲዎች በምርጫው ማግስት ተለያይተው መንግሥት ለመመስረት ዝግጅት ላይ ነን ማለታቸው የሜርክልን ተተኪ ለመገመት አዳጋች አድርጎታል።ኤስ.ፔ.ዴ ዛሬ እንዳስታወቀው ደግሞ ከአረንጓዴዎቹና ከነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ጋር በጥምር መንግሥት ምስረታ ላይ ንግግር ይካሄዳል ብሎ ተስፋ ያደርጋል። በብዙ ጉዳዮች ላይ የተለያየ አቋም ያላቸው አረንጓዴዎቹ እና ነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ደግሞ ከኤስ.ፔ.ዴም ይሁን ከሴ.ዴ.ኡ ጋር ድርድር ከመጀመራቸው በፊት ሁለቱ ለብቻቸው እንደሚነጋገሩ አስታውቀዋል። ይህን የሁለቱን ፓርቲዎች ሃሳብ ኤስ.ፔ.ዴ እንደሚደግፍ በጀርመን ፓርላማ የኤስ.ፔ.ዴ ፓርቲ መሪ ሮልፍ ሙትሰኒሽ ዛሬ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ሙትሰኒሽ እንዳሉት 25.7 በመቶ ድምጽ ያገኘው ኤስ.ፔ.ዴ ሁለቱን ፓርቲዎች ለድርድር ጋብዟል።
«አረንጓዴዎቹና ነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ፍላጎታቸው ከሆነ የጥምር መንግሥት ምስረታ ድርድር በዚህ ሳምንት እንዲጀመር ጋብዘናቸዋል። እነዚህ ሁለት ትናንሽ ፓርቲዎች ከአራት ዓመት በፊት ያስመዘገቡት ውጤት ከሚጠብቃቸው ሃላፊነት ጋር የሚመጣጠን እንዳልነበረ ማወቅ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። ቶሎ ወደ ስምምነት ላይ እንደርሳለን ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ።»
በአሁኑ ምርጫ ከ5 በመቶ በላይ ድምጽ አግኝተው በጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መቀመጫ ያገኙት 6 ታዋቂ ፓርቲዎችና ከሰሜን ጀርመኑ የሽሌሽቪግ ሆልሽታይን ፌደራዊ ክፍለ ሀገር አናሳ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወክሎ የተወዳደረውና በምክር ቤቱ አንድ መቀመጫ ያገኘው ኤስ.ደብሊው.ደብሊው  የተባለው ፓርቲ ነው። የጀርመን የፖለቲካ ፓርቲዎች እዚህ የሚታወቁበት መለያ ቀለም አላቸው። የሴ.ዴ.ኡ መለያ ቀለም ጥቁር፣ የኤስ.ፔ.ዴ ቀይ፣ የአረንጌዴዎቹ አረንጓዴ ፣የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ቢጫ የግራዎቹ ሮዝ እንዲሁም የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ መለያ ሰማያዊ ነው። በዚህ መለያ መሠረት አሸናፊው የኤስ.ፔ.ዴ መሪ ኦላፍ ሾልዝ ለመመስረት የሚፈልጉት ጥምር መንግሥት የትራፊክ መብራት ይባላል። አረንጓዴ መለያቸው የሆነው አረንጓዴዎች፣ በቢጫ ቀለም የሚታወቁት የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ እንዲሁም የባለ ቀይ ቀሉሙ ኤስ.ፔ.ዴ ጥምረት ከተሳካ የሚመሰረተው የሦስት ፓርቲዎች ጥምር መንግሥት በeራፊክ መብራት ይመሰላል። በምርጫው 24.በመቶ ድምጽ በማሸነፍ  ሁለተኛውን ደረጃ ያገኘው  የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ መሪ ላሼት ትናንት እንደተናገሩት ፣ከአረንጓዴዎቹ እና ከነፃ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ጋር ጃማይካ በሚል ስም የሚጠራውን ጥምረት መመስረት የሚያስችል ንግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል። ጥምረቱ ጀማይካ የሚባለው በጃማይካ ባንዲራ ላይ የሚገኙትን ፣ የሴ.ዴ.ኡ መለያ ጥቁር ቀለም የአረንጓዴዎቹን አረንጓዴና የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ቢጫ ቀለማት ስለሚካትት ነው። በምርጫው ማግስት የርሳቸው ፓርቲም ከሁለቱ አነስተኛ ፓርቲዎች ጋር ተጣምሮ መንግሥት ለመመስረት ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት ላሼት እንዳሉት  ማንም የመንግሥት ምስረታ የሚመለከተው እኔ ብቻ ነኝ ሊል እንደማይችል ጠቁመዋል።
«ማንም ፓርቲ ለመንግሥት ምስረታ ብቸኛው ወሳኝ እርሱ ብቻ እንደሆነ ማስመሰል የለበትም።ለዚህም ነው አጋር ሊሆኑ ይችላሉ ከሚባሉት ጋር አሁን መወያየት አስፈላጊ የሆነው። በበኩላችን በክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረትና በክርስቲያን ሶሻል ኅብረት የሚመራ መንግሥት ለሀገራችን የተሻለ ነው ብለን እናምናለን።ይህም ድምጽ ከሰጠን ህዝብ የተገኘ ነው።ለዚህም ነው ትናንት ጥምር መንግሥት የመመስረት ፍላጎት እንዳለን ያሳወቅነው።» 
ኤስ.ፔ.ዴም ሆነ ሴ.ዴ.ኡ ከነርሱ ጋር እንዲጣመሩ የመረጣቸው አረንጓዴዎቹ ና የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ አቋም የተለየየ መሆኑ በጥምር መንግሥት ምሥረታ ድርድር ላይ በአላሉ መግባባት ላይ መድረሳቸው ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም።አረንጓዴዎች የመንግሥትን ሥልጣን  በቀጥታ ለለውጥ ተጽእኖ እንዲያደርግ ጥቅም ላይ እንዲውል ግልጽ አቋም ነው ያላቸው።ነጻ ዴሞክራቶቹ ደግሞ የመንግሥት ስልጣን መገደቡ ጠንካራ አቋማቸው ነው። ለምሳሌ ቀረጥ መጨመርንና የመንግሥት ብድርንም ከፍ ማድረግ በጥምር መንግሥት ምስረታው ቀይ መስመር ብለው የያዙት ጉዳይ መሆኑን አስቀድመው ተናግረዋል።የኤፍ.ዴ.ፔ. አቋም ይህ ቢሆንም ከግራ ክንፍ ፓርቲዎች ውስጥ የሚደመሩት አረንጓዴዎቹም ወደ መሀል እያዘነበሉ ስለሆነ ለመግባባት ችግር ላይፈጥር ችግር ላይሆን ይችላል የሚል ግምት አለ። ይህ ማለት አረንጓዴዎች ከገበያ መፍትሄዎች እስከ ተፈጥሮ ጥበቃ ባሉት ጉዳዮች ላይ ከኤስ.ፔ.ዴ ጋር በሚደረገው ጥምረት አቋማቸውን ለማለዘብ ይገደዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። በምርጫው ውጤት መሰረት ኤስ.ፔ.ዴ አረንጓዴዎቹና ኤፍ.ዴ.ፔ. ቢጣመሩ በጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ውስጥ የሚይዙት መቀመጫ አብላጫ ነው የሚሆነው።በሌላ በኩል ሴ.ዴ.ኡ ከነዚህ ሁለት ፓርቲዎች ጋር ሊጣመርም ይችላል። ማንም ይሳካለት ማን እንደሚጠበቀው ከአውሮጳውያኑ ገና በፊት መንግሥት ምስረታ ይሳካል ብለው የሚያምኑ ጥቂቶች ናቸው ።ግን ማን መንግሥት ምስረታው ይሳካለታል ተብሎ ይታመናል? ትውልደ ኢትዮጵያዊው የፖለቲካ ተንታኝና ጋዜጠኛ አቶ ክፍለ ማርያም ገብረወልድ ከሴ.ዴ.ኡ ይልቅ ኤስ.ፔ.ዴ የተሻለ እድል አለው ይላሉ።ሆኖም ዋናው ጉዳይ ከአነስተኛዎቹ ፓርቲዎች ጋር የሚካሄደው ድርድር ውጤት ነው።
በምርጫው ውጤት መሠረት የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መቀመጫዎች ከእሳካሁኑ ከፍ ብሏል። ተሰናባቹ ፓርላማ ከነበረው 709 መቀመጫ ወደ 735 ምክንያቱ አቶ ክፍለማርያም አስረድተዋል። 
ሙሉውን ዝግጅት ለማዳመጥ ከታች የሚገኘውን የድምጽ ማዕቀፍ ይጫኑ
ኂሩት መለሰ 

ምስል Michael Sohn/AP/picture alliance
ምስል Martin Meissner/AP/picture alliance
ምስል Annegret Hilse/REUTERS
ምስል Christoph Soeder/dpa/picture alliance

አዜብ ታደሰ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW