የጀርመን ቤተክርስቲያን ትምህርት ቤት 50ኛ ዓመቱን አከበረ
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 26 2015
የጀርመን ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት ባለፈው ቅዳሜ 50ኛ ዓመቱን አክብሯል። ትምህርት ቤቱ የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸው እና የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስተምር ነው። ትምህርት ቤቱ ከ50 ዓመታት በፊት ሴቶችን የእጅ ሥራ ሙያ በማሰልጠን ሥራ የጀመረው በሁለት የሳር ቤቶች ነበር። ሐና ደምሴ ተጨማሪ ዘገባ አላት።
በ1964 በጀርመን መንግስት ድጋፍ የተቁዋቁዋመው የጀርመን ቤተክርስቲያን ትምህርት ቤት ቅዳሜ 26 ቀን 2015 የተመሰረተበትን 50ኛ አመት የወርቅ እዮቤልዪ በአል አክብሮዋል። የጀርመን ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት የተለያዩ የአካል ጉዳት እና የልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች በመቀበል ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር ተቀናጅተው የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነው።
በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች እና ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ብዙም ትኩረት ባልነበረበት ወቅት ተጨማሪ እገዛ የሚያሻቸውን ተማሪዎች ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር በመቀላቀል በማስተማር ፈር ቀዳጅ የሆነው ይህ የጀርመን ቤተክርስቲያን ትምህርት ቤት በተለይ በከተማዋ አዲስ አበባ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ህፃናትን በመቀበል እና በማስተማር ላለፉት 50 አመታት አገልግሎዋል። የጀርመን ቤተክርስቲያን ትምህርት ቤት የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ልጆች በማሰባሰብ ከሌሎች መደበኛ ተማሪዎች ጋር የሚያስተምር ትምህርት ቤት ነው
በአካባቢው ለሚኖሩ ሰዎች የማህበራዊ ስራ እድል ለመፍጠር እንደተከፈተ የተነገረው የጀርመን ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ትምህርት ቤት በወቅቱ በሁለት የሳር ቤቶች ሴቶችን በማሰባብሰብ የእጅ ስራ ሙያን በማሰልጠን ተጀመረ። ማእከሉ ከሁለት አመት በሁዋላ ወደ ትምህርት ቤትነት ተለወጠ። ከ13 አመት በሁዋላ በ 1981 ማየት የተሳናቸውን ህፃናትን አካቶ ማስተማር ጀመረ።
ትምህርት ቤቱ ባለው ጠባብ ቦታ ትምህርት መስጠት የሚያስችለውን ግብአቶች በማሙዋላት ልዩ አካል ጉዳተኛ ህፃናትን ጭምር እንደ የፍላጎታቸው እያስተማረ ሲሆን ወደፊት በውስጡ ያሉትን የተለያዩ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያግዙ ቁሳቁሶችን በማሟላት ተጨማሪ ተማሪዎችን የመቀበል እቅድ አንዳለው ምክትል ሀላፊው ተናግረዋል።
በጀርመን ቤተክርስቲያን ትምህርት ቤት የ50ኛ አመት የምስረታ በአል ላይ የቀድሞና የአሁን ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የተማሪ ወላጆች፣ የጀርመን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መጋቢዎች፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የጀርመን ተቁዋማት ተወካዮች፣ የትምህርት ቤቱ ደጋፊዎች እና ወዳጆች እንደዚሁም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የመጡ እንግዶች በተገኙበት በተለያየ ትረኢት ተከብሮዋል።
ሐና ደምሴ
እሸቴ በቀለ