የጀርመን ቤተ ክርስቲያን ት/ቤት ለተማሪዎቹ ምገባ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቱ
ረቡዕ፣ ሰኔ 18 2017
ትምህርት ቤቱ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ለሚያስተምራቸው ታዳጊዎች ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ምግብ ማግኘት የሚችሉበትን ሥራ ለማስጀመር ዛሬ በኢትዮጵያ ከጀርመን ኤምባሲ የ20 ሺህ ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎለታል።
አዲስ አበባ የሚገኘው ይህ ትምህርት ቤት፣ በሚገኝበት አካባቢ ሦስት ኪሎ ሜትር ዙሪያ የሚገኙ አቅመ ደካማ ወላጆች ልጆችን ደረጃውን የጠበቀ ነፃ የትምህርት ዕድል ይሰጣል። የትምህርት ቤቱ ድሬክተር አቶ ተክሉ ታፈሠ እንደሚሉት ትምህርት ቤቱ ከመደበኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ድጋፍ ያደርጋል። በአሁኑ ወቅትም 300 ያህል ተማሪዎች ያሉት ሲሆን ስድሳ ያህሉ አካል ጉዳተኛ እና ዐይነ ስውራን ናቸው።
እሱባለው ሳሙኤል በዚህ ትምህርት ቤት የ5ኛ ክፍል ተማሪ ነው። በትምህርት ቤቱ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ጀርመንኛ ቋንቋ መማር የሚችሉበት ዕድል መኖሩንም በማሰብ በርትቶ እንደሚማር ግልጿል። አብሳላት ወንደወሰን 13ት ዓመቷ ነው። በትምህርት ቤቱ ታታሪ ከሚባሉ ተማሪዎች አንዷ ስትሆን ያገኙት ዕድል ከመደበኛው ትምህርት በተጓዳኝ ግብረገብነትንም እንዲቀስሙ አግዞናል ብላለች።
በዚህ ትምህርት ቤት ለተማሪዎቹ ወርሃዊ የኪስ ገንዘብ፣ የመማሪያ ቁሳቁስ፣ ጀርመን ከሚኖሩ ደጋፊ ሰዎች ጋር ማስተሳሰርን ጨምሮ ዕለታዊ ምገባም ይደረጋል። ትምህርት ቤቱን የሚያስተዳድረው የቤተክርስቲያኑ የበላይ ኃላፊ ፓስተር የርገን ክላይን ተማሪዎቹ ግብረ ገብን በላቀ እንዲላመዱም ይደረጋል ብለዋል።
«ይህ ማኅበራዊ ሥራ ለአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም በአካታች ትምህርት አርዓያ ትምህርት ቤት ነን። ከ300 ተማሪዎች ውስጥ 65ቱ ዐይነ ስውራን ወይም የአካል ጉዳት ወይም ሌላ ችግር ያለባቸው ልጆች አሉን»።
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር የንስ ሃኒፊልድ ይህ ትምህርት ቤት በግቢው ለሚያስተምራቸው የመጀመርያ ደረጃ ተማሪዎች በየዕለቱ ምግብ እንዲቀርብላቸው የሚያስችል መሠረተ ልማት ለመገንባት የሚያስችል የ20 ሺህ ዩሮ ማድረጋቸው ችግረኛ ቤተሰቦች ያላቸውን ልጆች ሕይወት ለማቃናት ይረዳል ብለዋል።
«ለአዲስ አበባ እና ለኢትዮጵያም አርዓያ መሆን የቻለ ትምህርት ቤት እዚህ አለ ። ከሌሎች አገሮች ጋር በተለይም እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የጀርመንኛ ተናጋሪ አገሮች ጋር በመሆን ድጋፋችንን ለማስቀጠል እንጥራለን»።
ከ53 ዓመታት በፊት ልጃገረዶችን ለማስተማር በጀርመንኛ ተናጋሪ የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ድጋፍ የተመሰረተው ይህ ትምህርት ቤት እስከዛሬ ያስተማራቸው በመልካም ሥራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙም ገልጿል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር