የጀርመን ተቀናቃኝ ፓርቲ መሪዎች ክርክር
ሐሙስ፣ ጥቅምት 8 2005የዩሮ ሸርፍ ተጠቃሚ ሐገራት የገጠማቸዉ ምጣኔ ሐብታዊ ኪሳራ ጀርመን ዉስጥ በመጪዉ ዓመት የሚደረገዉ ምርጫ አብይ የመፎከካሪያ ርዕሥ መሆኑ ከወዲሑ እየታየ ነዉ።ለመራሔ-መንግሥትነቱ የሚወዳደሩት የሁለቱ ትላልቅ የፖለቲካ ማሕበራት እጩዎች ዛሬ በሐገሪቱ ምክር አባላት ፊት ቀርበዉ የምርጫ ዘመቻ ፉክክር የመሠለ የፊት ለፊት ክርክር አድገዋል።በሥልጣን ላይ ያሉት መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የዩሮን ኪሳራ ለማቃለል ተጣማሪ መንግሥታቸዉ የወሰደዉ እርምጃ ጥሩ ዉጤት አምጥቷል ባይ ናቸዉ። የዋነኛዉ ተቃዋሚ፥ የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ እጩ መራሔ መንግሥት ፔር ሽታይንማየር የሜርክል አቋምና የመንግሥታቸዉን እርምጃ አጣጥለዉ ነቅፈዉታል። ክርክሩን የታዘቡ እንዳሉት ቀኑ የሽታይንብሩክ ነበር። በሌላ በኩል የአዉሮጳ ኅብረት መሪዎች ብራስልስ ቤልጅግ ላይ ለሁለት ቀናት የሚያካሂዱትን ጉባኤ ርዕሰ ጉዳይ የፈረንሳይና ጀርመን ፍጭት ሊለዉጠዉ እንደሚችል እየተገነገረ ነዉ። የአዉሮጳ ማዕከላዊ ኃይሎች የሚባሉት ሁለቱ ሀገሮች ኅብረቱ የሀገራትን በጀት ይከታተል በሚለዉ የተግባቡ አይመስልም።
የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል የአዉሮጳ ኅብረት ለሀገራት ከሚተምነዉ ዓመታዊ የበጀት ጉድለት በታች በጀት የሚመድቡ መንግስታትን እንዲቆጣጠርና እንዲቀጣ የሚያስችለዉ ደንብና ስልጣን እንዲኖረዉ ይጠይቃሉ። የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦሎንድ በበኩላቸዉ በዛሬዉ ጉባኤ በጀትን የሚመለከት አጀንዳ የለም፤ ይልቁንም የአዉሮጳን ባንኮች ህብረት ማጠናከር በሚለዉ ላይ እናተኩር ባይናቸዉ። ሜርክልና ኦሎንድ ልዩነታቸዉን ለማጥበብ ከጉባኤዉ አስቀድሞ የብቻቸዉን ዉይይት እንደሚያደርጉ ተገምቷል። ከጉባኤ አስቀድመዉ ሜርክል በርሊን ላይ ለምክር ቤታቸዉ የዩሮን ቀዉስ አስመልክተዉ ባደረጉት ንግግር የጋራዉ ሸርፍ ለአዉሮፓ አለዉ ያሉትን አንድምታም በዚህ መልኩ ገልፀዋል፤
«ዩሮ ከሌሎች በርካታ መሣሪዎችና ርምጃዎች ጋ ሆኖ ለእኛ ጥንካሬ ነዉ፤ ይህ ዩሮ ከመገበያያ ነትም እጅግ የላቀ ነዉ፤ ይህ ዩሮ በመላ አዉሮጳ ከከፍተኛ ጥቅሙ ጋር በምጣኔ ሃብቱ፤ በማኅበራዊዉ እንዲሁም በፖለቲካዉ ተምሳሌት ሆኖ አዉሮጳን አንድ አድርጎ ይገልፃል።»
ሜርክል ኅብረቱ የገጠመዉን ቀዉስ ለመፍታት ርምጃዎች እንዲፋጠኑም ጠይቀዋል። የዩሮ ቀጣና ቀዉስ ከገጠመዉ ወዲህ የኅብረቱ መሪዎች ዛሬ እና ነገ የሚያካሂዱት ጉባኤ 22ኛቸዉ መሆኑ ነዉ።
ይልማ ሐይለ ሚካኤል
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ