1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት አሸናፊዋ ከንቲባ

ፀሀይ ጫኔ
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 9 2017

የፍሪታውን ከንቲባ ኢቮኔ አኪ ሳውየር ለአሥርተ ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት የደቀቀችውን የሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታወንን ለኑሮ ምቹ ወደሆነች ከተማነት ቀይረዋታል። የመኖሪያ ቤቶች፣ የውኃ አቅርቦትና ቆሻሻ አሰባሰብ በእጅጉ አሻሽለዋል።ለዚህ ቁርጠኝነታቸውም የጀርመኑ አፍሪካ ፋውንዴሽን የ2024 የአፍሪካ ሽልማትን ሰጥቷቸዋል።

Preisverleihung des Deutschen Afrika-Preises an Yvonne Aki Sawyerr
ምስል Luisa von Richthofen/DW

የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት የ2024 አሸናፊዋ ከንቲባ

This browser does not support the audio element.


«ያደኩት አረንጓዴ ከተማ ውስጥ ነው።»ይላሉ ከንቲባ  ይቮኔ አኪ-ሳውየር ስለልጅነት ጊዚያቸው ሲናገሩ።
ከእነዚህ የልጅነት ትዝታዎቻቸው ጋርም የሴራሊዮንን ዋና ከተማ  ፍሪታውን ወደ ቀድሞ ክብሯ የመመለስ ራዕይ ይዘው ተነሱ። ይህ የአካባቢ ጥበቃ  ሀሳባቸው ለከንቲባነት እንዲወዳደሩ ገፋፋቸው።
«ያደኩት አረንጓዴ በሆነች ከተማ ውስጥ ነው። እንዳልኩት ያደግኩት  ዛፍ መውጣት በምወድበት ከተማ ነው።ማለቴ ያንን ያደረኩት ለተፈጥሮ ከፍተኛ ፍቅር ስለነበረኝ  ነው። እና በ2017 እና  በ 2018 ያ ሲወድም በማየቴ  እና  በዙሪያው የነበሩትን ከንፅህና አጠባበቅ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶችን ስመለከት ፤ ታውቃላችሁ እነዚያ ምክንያቶች ለምርጫ እንድወስን ገፋፉኝ።»ብለዋል።
አኪ-ሳውየር ወደ ከንቲባነት ሥልጣን የመጡት  ከስድስት ዓመታት በፊት ነው።ከዚያን ጊዜ  ጀምሮ፣ ለአሥርተ ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት የደቀቀችውን የሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታወንን  ለኑሮ ምቹ ወደሆነች ከተማነት ቀይረዋታል። የመኖሪያ ቤቶች፣ የውኃ አቅርቦትና ቆሻሻ አሰባሰብ በእጅጉ አሻሽለዋል።

በሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታወን በአውራ ጎዳናዎች ላይ ሰዎች ፍራፍሬ ሲሸጡምስል Seth/Xinhuapicture alliance

ፍሪታወን ፤የዛፎች ከተማ

የፍሪታውን የመጀመሪያዋ ሴት ከንቲባ ለመሆን አምስት ወንድ እጩዎችን ሲያሸንፉ፤ የአኪ-ሳይወር በአራት አመት እቅዳቸው «ፍሪታውንን መቀየር» የሚል ነበር የዘመቻቸው ቁልፍ ጉዳይ። የእሳቸው  ዕቅድ የከተማዋን ከባድ የቆሻሻ ችግሮችን ማስተካከል እና በፍሪታውን ኮረብታዎች ላይ በተጨፈጨፈው ደን ምትክ ዛፎችን መትከል ወደነበረበት መመለስ ነበር። አኪ ሳውየር አካባቢን ለመጠበቅ ቁርጠኛ ናቸው። እና መጭው ትውልድ  በልጅነታቸው የነበረችውን አረንጓዴዋን ፍሪታውንን እንዲያይ  ይፈልጋሉ።
ከንቲባዋ ምንም ይስሩ  ምን ነዋሪዎችን ያሳተፋሉ።ይህ ዜጋን ያማከለ የአስተዳደር ዘይቤ ለከንቲባ አኪ-ሳውየር በሀገር ውስጥም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን አግኝቶላቸዋል።ነገር ግን አሁንም ብዙ የሚቀረን ስራ አለ ባይ ናቸው ። 
«የከተማችን የህዝብ ቁጥር እድገት፣ የዕቅድ አለመኖር ፤ታውቃላችሁ፣ የሕንፃው አሰራር ፈቃድ በተማከለ ደረጃ  በመሆኑ ያሉት ተግዳሮቶች፣ ለአምስት ዓመታት ጠንክረን ብንሠራም፤ አሁንም ብዙ መሥራት ያለብን ነገር እንዳለ እያየን ነው።ነገር ግን የፍሪታውን ከንቲባ በመሆኔ ሁሌም ከእኔ ጋር  የሚያያዙ  ትሩፋቶች  ብዬ በእርግጠኝነት የምናገራቸው ሁለት ነገሮች አሉ።አንድኛው የተለመደው፤  ፍሪታውንን የዛፉ ከተማ ማድረግ።ታውቃላችሁ፣ አንድ ሚሊዮን ዛፎችን መትከል  የእኛ ውሳኔ  ቁርጠኝነት እና ኢላማ ነው።ሁለተኛው እና ትኩረት የሚስበው። የፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝ ነው።»
በጎርጎሪያኑ 2020 ዓ/ም መጀመሪያ ላይ አኪ-ሳውየር በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 1 ሚሊዮን ዛፎችን በፍሪታውን የመትከል ዓላማ ያለው የ«ፍሪታውን ዘ ትሪታውን» ወይም ፍሪታወን የዛፍ ከተማ የሚል ዘመቻ ጀመሩ።በዚህም 1 ሚሊዮን የሚጠጉ /977,000/  ዛፎችን በመትከል ዛሬ ላይ ደርሰዋል። በርካታ አዳዲስ ዛፎች የከተማዋን የአየር ሙቀት በመቀነስ የጎርፍ አደጋ የመቋቋም አቅምን እየጨመሩ ነው።

ከንቲባ ኢቮን አኪሳወር በፍሪታወን የአካባቢ ችግሮችን ለመፍታት ለአረንጓዴ የኢኮኖሚ ውጥኖች ቅድሚያ ሰጥተዋልምስል -/Artcolor/picture-alliance

የተሻለ የህይወት ጥራት

ከንቲባዋ የአካባቢ ችግሮችን ለመፍታት ለአረንጓዴ የኢኮኖሚ ውጥኖች ቅድሚያ ሰጥተዋል። ቆሻሻን ወደ ካርቦን-አልባ ማገዶ  የሚቀይረው አዲሱ ፋብሪካ በከተማው ውስጥ በሰፊው ጥቅም  ላይ ለሚውለው ከሰል አማራጭ ይሰጣል።
የቆሻሻ ውሃ ማጣሪያ ጣቢያ  እና 160 የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖች እንዲሁም የዝናብ ውሃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችም በከተማዋ ተዘርግተዋል። ከመጸዳጃ ቤት ከሚወጣው ቆሻሻ ማዳበሪያ፣፣ማሞቂያ እና ማገዶ ይዘጋጃል። ንፁህ ውሃ የሚያቀርቡ በፀሃይ ሃይል የሚሰሩ የውሃ ኪዮስኮችን የመሳሰሉ ሌሎች አዳዲስ መርሀግብሮችንም ዘርግተዋል። 

አኪ-ሳውየር የአካባቢ ችግሮችን መፍታት ብቻ ግባቸው  እንዳልሆነ  አፅንዖት ይሰጣሉ።ነገር ግን የአካባቢ ችግሮች የፍሪታውንን ነዋሪዎች ህይወት ላይ ተፅዕኖ እንዳላቸው ያምናሉ።«እና እነዚህ የአካባቢ ጉዳዮች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን ትልቅ መሻሻልም አምጥተናል።በተጨማሪም  የአየር ንብረት ለውጥ መቀጠሉ፣የሙቀት መጠን ፣የባህር ጠለል መጨመሩ፣የአየር ንብረት መዛባት እየተለመደ በመምጣቱ በከተሞች  ለሚኖሩ ሰዎች አሉታዊ ተፅእኖ ጭምር አላቸው።ስለ ሙገሳ  ግድ ከሌለዎት፤የበለጠ ስራ ይሰራሉ። ስራው ለፍሪታውን ህዝብ እንዲሰራ እንፈልጋለን። ስራው ላይ ስማችን እንዲቀመጥ አያስፈልግም። እንዲሁ ሊሰራ ያስፈልጋል።» በማለት ገልፀዋል።አኪ-ሳውየር የፈለገጉትን ያውቃሉ።በውስጣቸው የነበረውን እምነት ተከትለው በሰሩት ስራ በልጅነታቸው የሚያውቋት አረንጓዴዋን ከተማ ፍሪታወንን አሁን ለወደፊቱ ትውልድ እንድትሆን እያደረጉ ነው።የዜጎቻቸውን የኑሮ ደረጃ  ለማሻሻል ባደረጉት ጥረት  ፍሪታውን ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ  ከተማ መሆን ጀምራለች።ይህ ጥረታቸውም በውጭ አገር ሳይቀር እውቅና አግኝቶ፤ ያለፈው ረቡዕ አኪ-ሳውየር የ2024 የጀርመን አፍሪካ ሽልማትን በዋና ከተማ በርሊን ተሸልመዋል።

ኦቦን አኪሳወር ፤የሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታወን ከንቲባምስል Bryan Bedder/Getty Images for Bloomberg Philanthropies

የማያወላውል ቁርጠኝነት

የጀርመኑ አፍሪካ ፋውንዴሽን የ 2024 የጀርመን አፍሪካ ሽልማትን በመሸለም ለዘላቂ የከተማ ልማት እና ለአካባቢ ጥበቃ ያላቸውን ተሳትፎ  እንዲሁም ለ"የማያወላውል" ቁርጠኝነታቸው እውቅና ሰጥቷል።
የጀርመኑ የታችኛው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ባርቤል ባስ በበርሊን ሽልማቱን አበርክተዋል። ባስ እንዳሉት እንደ አኪ-ሳውየር ያሉ የሴት መሪዎች ለወደፊት ለሚመጡ ሴት ፖለቲከኞች ታላቅ አርአያ ናቸው።ፋውንዴሽኑ ከንቲባው ቢሮአቸው ከሚፈልገው በላይ ቁርጠኝነት እንዳላቸውም ገልጿል።
ከንቲባዋም ሽልማቱ የበለጠ ለመስራት ያነሳሳል ይላሉ።«በእውነት  ደስተኛ ነኝ። ይህ ሽልማት እንዳለ አላውቅም ነበር ። እና ባለፈው ጥር ኢሜል ሲደርሰኝ በጣም ነው የተደነኩት።የጀርመን መንግስት ፋውንዴሽን እና DW ለሥራችን የሰጡት እውቅና በጣም ሰፊ ይመስለኛል።በጣም የሚያስደስት እና የሚያበረታታ ነው።እናም ለመቀጠል እና የበለጠ ለመስራት ግብዓት ይሆነኛል።»

በውድድሩ ከአስር  በላይ እጩዎች የቀረቡ ሲሆን፤ አኪ ሳውየር የተመረጡት በዶቼ ቬለ የአፍሪካ ፕሮግራሞች ኃላፊ፤ ክላውስ ስቴከር በሚመራው እና 20 አባላት ባለው ገለልተኛ የዳኞች ቡድን ነው። የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን ከጎርጎሪያኑ 1993 ዓ/ም ጀምሮ በአፍሪካ በዲሞክራሲ፣ በሰላም፣በማህበራዊ ጉዳዮች፣ በሰብአዊ መብቶች፣ በዘላቂ ልማት፣ እንዲሁም በጥበብ እና ባህል ላይ የላቀ ጥረት ላደረጉ ሰዎች ሽልማት ሲሰጥ ቆይቷል።
ከንቲባዋ በሴራሊዮን እና በብሪታኒያ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን ለንደን ውስጥ የፋይናንስ ባለሙያ እና ኦዲተር ሆነው ከ25 አመታት በላይ ሰርተዋል።ሆኖም  በጎርጎሪያኑ 2014 ዓ/ም ሀገራቸው ሴራሊዮን  በኢቦላ ቀውስ ስትናወጥ፣የኢቦላ ማገገሚያ ቡድንን ለመምራት ነበር ከ1 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ወዳለሉባት እና የወደብ ከተማ  ወደሆነችው ፍሪታውን የተመለሱት።

ስማቸው ከፍሪታውን ለውጥ ጋር ፈጽሞ የተቆራኘው አኪ ሳወየር  በ2023 ለሁለተኛ ጊዜ ከንቲባ ሆነው ተመርጠዋል።ይህ ብቻ ሳይሆን የሲ40 ከተሞች /C40 Cities/ ተባባሪ ሊቀመንበርም ናቸው። ይህንን እንቅስቃሴ አሁን ከለንደን ከንቲባ ሳዲቅ ካን ጋር እየመሩ ነው። C40 የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም 100 የሚጠጉ በአለም መሪ የሆኑ ከተሞች ከንቲባዎች የሚገኙበት አለም አቀፋዊ ትስስር ነው።

ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ  

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW