የጀርመን አፍሪቃ ግንኙነት በሜርከል ዘመን
ዓርብ፣ ኅዳር 24 2014በአፍሪቃ የኢኮኖሚ ልማት ትብብር የተሻለ ሰርተዋል የሚባሉት፤ ተሰናባቿ የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርከል፤ በስልጣን በቆዩባቸው 16 ዓመታት ከቀደምት መሪዎች የበለጠ ለበርካታ ጊዜያት ወደ አፍሪቃ በመጓዝ ከአህጉሪቱ መሪዎች ጋር ብዙ ውይይቶችንና ስምምነቶችን ማድረጋቸው ይነገራል።ያለፈው ነሐሴ 2021 ዓ/ም ደግሞ ሜርክል በርካታ የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶችን ወደ ጀርመን ዋና ከተማ በርሊን በመጋበዝ የስንብት ስብሰባ አድርገዋል።በዚህ የስንብት መርሃ ግብር የታደሙት በደቡብ አፍሪካ የአለም አቀፍ ጉዳዮች ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ሚነህሌ ኔን እንደሚሉት ሜርክል ከአፍሪካ ጋር ያደረጉት ግንኙነት በተለይ የአህጉሪቱን ኢኮኖሚ ልማት በተመለከተ የሚደነቅ ነው።
« በጀርመን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና የልማት አጀንዳ አፍሪካን ማዕከል እንድትሆን በማድረግ አስደናቂ ስራ ሰርታለች። በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ አፍሪካን ለማስተዋወቅ ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነቷ በግልጽ ታይቷል። ከአፍሪካ መሪዎች ጋር የነበራት ግንኙነት እና በክልሉ የነበራት ተሳትፎም እንዲሁ። ለ«ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ» መርሃ ግብርም አንቀሳቃሽ ሃይል ሆናለች።»
የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንዉሚ አዴሲና በበኩላቸው ለሜርክል አድናቆት አላቸው።አዴሲና እንደሚሉት ሜርከል ለአህጉሪቱ ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት እና ልማት ታማኝ ወዳጅ ነበሩ።
በተለይ በጎርጎሪያኑ 2017 ዓ/ም ጀርመን የቡድን 20 ሀገራትን የፕሬዝዳንት መንበር በያዘችበት ወቅት «ኮምፓክት አፍሪቃ» ተብሎ ለሚጠራውና ጀርመንን ጨምሮ በቡድን 20 ሀገራትና እና በ12 የአፍሪካ ሀገራት መካከል ለነበረው የኢኮኖሚ ትብብር የሜርከል አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ሃላፊው ገልፀዋል።
ተመራማሪዋ ሚነህሌ ኔን «ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካን» እንደ ስኬት ይመለከቱታል። አብዛኞቹ የጀርመን ኩባንያዎች በአፍሪካ መዋዕለንዋይ ለማፍሰስ ፍቃደኛ አልነበሩም።የሚሉት ተመራማሪዋ ለዚህ ትብብር ምስጋና ይግባውና በቀጣናው የተሻለ ሁኔታ እየተሳተፉ ነው ብለዋል።
ይሁን እንጅ በሜርከል የአመራር ዘመን አፍሪካ በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ የበለጠ ሚና ተጫውታለች ብለው አያስቡም።
«አንጌላ ሜርክል ከአፍሪካ ጋር የነበራት ግንኙነት ትኩረት የሚስብ ነው ብዬ አስባለሁ።በአፍሪካ የጀርመን የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በእሷ አመራር በመጠኑ ተስፋፍቷል። በእሷ የአመራር ጊዜ አፍሪካ በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ የበለጠ ሚና ተጫውታለች ብዬ ግን አላምንም። »
በርሊን የሚገኘው ግሎባል ፐብሊክ ፖሊሲ የተባለ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ጌሪት ኩርትዝ ግን የሜርክልን ጅምር የተሳካ አልነበረም ሲሉ ይተቻሉ።
ኩርትዝ ከሚተቹት የሜርከል ፖሊሲ ውስጥ የጀርመን ልማት ትብብር "የተሃድሶ አጋርነት ይገኝበታል።ይህ አጋርነት የጀርመን መንግስት በመልካም አስተዳደር ላይ የተለየ መሻሻል ለሚያደርጉ የአፍሪካ ሀገራት የሚያደርገው ተጨማሪ እርዳታ ሲሆን፤ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከ2019 ጀምሮ የለውጥ አጋር ሆና ቆይታለች።ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ከሚታየው የሀገሪቱ ቀውስ ጋር በማያያዝ ትብብሩን ውጤት አላመጣም ይላሉ።
በኢኮኖሚው ረገድም ቢሆን ፤ጀርመን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚደረግ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በአፍሪቃ 1% ብቻ ትሸፍናለች።በተጨማሪም በአህጉሪቱ ወደ 800 የሚጠጉ የጀርመን ኩባንያዎች ብቻ ናቸው የሚሰሩት።በዚህ የተነሳ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ረገድም ትብብሩ የተሳካ አይደለም ባይ ናቸው።
«ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ »' የተባለው ትብብር የጀርመንን የግል የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በአፍሪካ የማስተዋወቅ ግቡን ሙሉ በሙሉ አላሳካም። ውጤቱ መራሂተ መንግስቷ እራሳቸው ከጠበቁት ያነሰ ነበር."
በሌላ በኩል በ2016 ዓ/ም የሜርክል የአፍሪቃ ጉዞ ቢጨምርም፤የጀርመን የስደተኞች ቀውስ እየተባለ ከሚጠራው ከአንድ ዓመት በኋላ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሀገሪቱ በመግባታቸው ወደ አውሮፓ የሚደረገውን መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ለመገደብ የተወሰዱ ርምጃዎች በአንዳንድ የጀርመን አፍሪካ ፖሊሲዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል ብለዋል።
እሳቸው እንደሚሉት በሜርከል አመራር ወቅት የጀርመን ፍላጎት ከምስራቅ አፍሪካ ወደ ምዕራብ አፍሪካ በመጠኑም ቢሆን ተሸጋግሯል። ለጀርመን አስፈላጊ ከሆኑት ኬንያና ኢትዮጵያ ን ከመሳሰሉ የምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት ይልቅ ፤ ማሊ፣ ሞሪታኒያ፣ ቻድ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀርን ወደ መሳሰሉት የሳህል ግዛቶች ትብብሯን በከፍተኛ ሁኔታ አስፋፍታለች።ያም ሆኖ የሳህል ክልል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በእስላማዊ ታጣቂዎች እና በታጣቂ ቡድኖች የሚሰነዘረው ጥቃት እየጨመረ መጥቷል።
በመሆኑም አፍሪካ የሜርክልን ለሚተኩት ኦላፍ ሾልስን ምን ያህል ጠቀሜታ እንደሚኖራት ግልፅ አይደለም። ነገር ግን ጀርመን ለአፍሪካ ቁርጠኛ እንደምትሆን ተስፋ ያደርጋሉ።
“የጀርመን አፍሪካ ፖሊሲ የጀመረው በጣም ዝቅተኛ በሆነ ደረጃ ነው። እንደ ታላቋ ብሪታንያ፣ ፈረንሣይ ወይም አሜሪካ ካሉ በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ተዋናዮች በተቃራኒ ።ነገር ግን ጀርመን ከአፍሪካ ጋር የምር የሆነ አጋርነትን የመፍጠር ዕድል አላት። ይህ ደግሞ የሜርክል የአፍሪካ ፖሊሲ ትሩፋት ቢሆን ኖሮ ስኬት ሊሆን ይችል ነበር። »
ያም ሆኖ አንጌላ ሜርክል አፍሪካ በጀርመን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ያላትን ፋይዳ ከፍ ለማድረግ ረድተዋል ይላሉ። የቀደሙት መንግስታት አፍሪካን እንደ ልማት አጋር አድርገው ይመለከቱ እንደነበር ጠቁመው፣ ሜርክልም ይህንን በማስፋት ኢኮኖሚያዊ እይታውን እንዲጨምር አድርገዋል።ሆኖም ጀርመን በአፍሪካ ከምታደርገው ተሳትፎ ጀርባ ግልፅ የሆነ የግል ጥቅም ፍላጎት መኖሩን ሳይጠቁሙ አላለፉም ።
ፀሀይ ጫኔ/ማርቲና ሽዋኮቭስኪ
ነጋሽ መሀመድ