1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ኢንቬስተሮች ለምን በአፍሪቃ ንግድ አስተማማኝ አይደለም ይላሉ?

ቅዳሜ፣ ኅዳር 21 2017

ስለ አፍሪቃ ላይ ያለው የተጋነነ የፖለቲካ፣ የፖሊሲ እና የኢኮኖሚ አመለካከት ከስጋቶቹ አንዱ ነው። አፍሪቃ በጀርመን ሚዲያ በፖለቲካ ያለመረጋጋት፣ በሙስና፣ በደካማ መሠረተ ልማቶች፣ በቢሮክራሲያዊ መሰናክሎች ያሉባት ስለመሆንዋ ነዉ የሚሰማዉ። ይህ በእርግጥ የጀርመን ባለሃብቶችን፤ የጀርመን መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችን ወደፊት እንዳይራመዱ ያግዳል።

የጀርመን ምክትል ቻንስለር ኖበርት ሃቤክ
የጀርመን ምክትል ቻንስለር ኖበርት ሃቤክ - በደቡብ አፍሪቃ 2022ምስል Bernd von Jutrczenka/dpa/picture alliance

ወደ ኬንያ የሚጓዙት የጀርመን ምክትል ቻንስለር እና የጀርመን አፍሪቃ የንግድ ትብብር ጉባዔ

This browser does not support the audio element.

በአፍሪቃ ንግድ አስተማማኝ አለመሆኑን የሚናገሩት የጀርመን ኢንቬስተሮች

የጀርመኑ ምክትል መራሔ መንግሥት እና የኢኮኖሚ ሚኒስትር ሮበርት ሃቤክ የፊታችን ሰኞ  የሚጀመረዉን የጀርመን አፍሪቃ የንግድ ልዉዉጥ ጉባዔ(GABS) ለመክፈት ወደ ኬንያ ይጓዛሉ።  ለሁለት ቀናት የሚዘልቀዉ የጀርመን አፍሪቃ የንግድ ልዉዉጥ ጉባዔ በምህጻሩ(GABS) በአህጉሪቱ በተለያዩ ሃገሮች የሚካሄድ ነዉ።  

GABS የንግድ ግንኙነቶችን ለማጠናከር እና የትብብር አቅምን ለመፈተሽ እንደ መድረክ የሚያገለግል ነዉ።  ምንም እንኳን የቀድሞ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በቅርብ ጊዜ ባሳተሙት "የነጻነት ትዝታዎች ከ 1954-2021" በተሰኘዉ መጻሕፋቸዉ ላይ እንደጠቀሱት፤ "ትልልቅ የጀርመን ኩባንያዎችን አብረዉኝ እንዲሄዱ ለማሳመን የተደረገዉ ጥረት ቀላል አልነበረም ብለዋል። አብዛኛዎቹ ኩባንያዎች በአፍሪቃ ገበያ ጥቂት እድሎች እንዳሉ ብቻ ነዉ የተረዱት ሲሉ ነዉ ያመላከቱት።  

ስለ አፍሪካ ግንዛቤ

በአፍሪቃ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት (APRI) የምጣኔ ሐብት ከፍተኛ ባለሞያ የሆኑት ሰርዋህ ፕሪምፔ "በአፍሪቃ ላይ ያለው የተጋነነ የፖለቲካ፣ የፖሊሲ እና የኢኮኖሚ አመለካከቶች አደጋዎች ናቸው ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።     

"ይህ በእርግጥ የጀርመን ባለሀብቶችን በተለይም ለጥቃቅን እና መለስተኛ ድርጅቶች (አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች) ላልዋቸዉ እና ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑት ያስደነግጣል" ሲሉ ፕሪምፔ ለDW ተናግረዋል።

ኬንያ ኦልካሪያ ጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ጣቢያምስል David Ehl/DW

እንደ ምሁርዋ አስተያየት፣ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑት ምላሽ ለሚሰጡት የጀርመን ባንኮች፤ በአፍሪቃ ለሚዉል መዋዕለ ንዋይ ከፍተኛ ወለድ ወይም በአፍሪቃ ለሚገኙ የግል የጀርመን ኩባንያዎች የገንዘብ ድጋፍ ባለማድረግ ምላሽ ይሰጣሉ።

"ስለ አፍሪቃ ላይ ያለው የተጋነነ የፖለቲካ፣ የፖሊሲ እና የኢኮኖሚ አመለካከት ከስጋቶቹ አንዱ ነው። አፍሪቃ በጀርመን ሚዲያ በፖለቲካ ያለመረጋጋት፣ በሙስና፣ በደካማ መሠረተ ልማቶች፣ በቢሮክራሲያዊ መሰናክሎች ያሉባት ስለመሆንዋ ነዉ የሚሰማዉ። ይህ በእርግጥ የጀርመን ባለሃብቶችን በተለይም የጀርመን መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችን ወደፊት እንዳይራመዱ ያግዳል። በጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅት እንዲሁም ኩባንያዎች ውስጥ ያሉትን፣ በተለይም ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑትን የጀርመን ባንኮችን ገሸሽ እንዲሉ ያደርጋል።"

ቀደም ሲል የነበሩት የጀርመን መንግስታት ለምሳሌ በአዉሮጳዉያኑ 2017 ጀርመን የቡድን 20 ፕሬዝዳንት በነበረችበት ወቅት የተቋቋመው እና አፍሪቃ ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ተጨማሪ የግል መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችን ለማፍለቅ አላማ ባለው እንደ «ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ» ባሉ ውጥኖች የጀርመን አነስተኛ ተቋማትን በማሳመን ብዙ ሙከራዎችን አድርገዋል። እንደ የአፍሪቃ ፖሊሲ ጥናት ተቋም APRI ጥናት ዘገባ ፤ በአጠቃላይ ጀርመን ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ በአፍሪቃ ውስጥ በፖለቲካዊም ሆነ በኢኮኖሚ ዘርፉ ንቁ ተሳትፎ አላደረገችም። በአፍሪቃ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም (APRI) ከፍተኛ የምጣኔ ኃብት ባልደረባ ሰርዋህ ፕሪምፔ እንደሚሉት፤ ለዚህ ምክንያቱ  የጀርመን ባለሀብቶች አደጋ ይደርስብናል በሚል ስጋት ፍላጎታቸዉ በመቀነሱ ነዉ።

«ብዙዎቹ በአፍሪቃ ኢንቨስት ከማድረጋቸው በፊት  «መዋዕለ ንዋይ ከማፍሰሳቸዉ በፊት» የመንግስትን ድጋፍ ለማግኘት ይፈልጋሉ። ይህ ድጋፍ የጀርመን መንግስት ያለውን ጥብቅ የበጀት አቋም እና የዜጎች ውስጣዊ ልማት ላይ እንዲያተኩሩ እና የበለጠ እንዲያወጡ የሚያደርጉትን ጫና ግምት ውስጥ በማስገባት ላይሳካ ይችላል።»

አዲስ ጅማሪ

የጀርመን ምክትል መራሄ መንግሥት ሮበርት ሃቤክ  እንደ አዉሮጳዉያኑ 2022 ደቡብ አፍሪቃን እና ናሚቢያን ለመጀመርያ ጊዜ ሲጎበኙ በጀርመን ፣ በአውሮጳ እና በአፍሪቃመካከል ያለው ግንኙነት እንደገና እንዲጀምር እና አዲስ አቀራረብ እንዲፈጠር ጥሪ አድርገዉ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ጀርመን 13.6 ሚሊዮን ዩሮ ማለትም (14.3 ሚሊዮን ዶላር) በናሚቢያ (ሃይፈንፕሮጀክት) ላይ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሰች ነዉ። ይህ መዋዕለ ንዋይ የከባቢ አየር ብክለትን የማያስከትል የፀሐይ ኃይል እና አረንጓዴ ሃይድሮጅን የብረት ማዕድንን ለመቀየር የሚያስችል ነዉ።

የጀርመኑ ምክትል መራሔ መንግሥት እና የኢኮኖሚ ሚኒስትር ሮበርት ሃቤክ ከፊታችን ሰኞ  ጀምሮ በኬንያ ሊያደርጉት ባቀዱት የሁለት ቀናት ጉብኝት፤ በቻንስለር ኦላፍ ሾልስ ቅድሚያ እቅድ ዝርዝር ውስጥ እደነበረው በአፍሪቃ ትልቁ የጂኦተርማል ተክል ከኦልካሪያ፣ የንግድ አጋሮች ጋር ይገናኛሉ።

ሾልዝ የሰሜን-ደቡብ አዲስ የግንኙነት ጅምር እንዲኖር እና ይህ ከብዙ የደቡብ ሃገራቶች ጋር በእኩል ደረጃ የጋራ አመለካከቶችን ለማዳበር ያስችላል ሲሉ ተናግረዉ ነበር።"

እንደ ኬንያዊው ኢኮኖሚ ጉዳይ ምሁር ጄምስ ሺኩዋቲ የጀርመን የኢንቨስትመንት አካሄድ በአፍሪቃ ብሎም በኬንያ ድርብ ቀውስ ውስጥ ነዉ የሚገኘዉ። የጀርመን መንግስት በአውሮጳ በሚታየዉ ቀዉስ ምክንያት ጫና ውስጥም ገብቷል።

የጀርመን ቻንስለር ኦላቭ ሾልዝ - ኬንያ ኦልካሪያ ጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ጣቢያምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

"የጀርመን የኢንቨስትመንት አካሄድ ኬንያን ጨምሮ በአፍሪቃ ድርብ ቀውስ ገጥሞታል። በመጀመሪያ ደረጃ ጀርመን የዉስጥ ቀውስ ውስጥ ነች። በአውሮጳ በሚታየዉ ግጭት ምክንያትም የጀርመን ኢኮኖሚ ጫና ውስጥ ገብቷል። ወደ አፍሪቃ ስንመጣ እምቅ የጀርመን ኢንቨስትመንቶች ከቻይና እና ከሌሎች የኢኮኖሚ ክፍሎች ፉክክር እየገጠማቸው ነው። በዚህም ምክንያት በአፍሪቃ ያላቸው የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት አካሄድ ጠበኛ አይነት እንዲሆን አድርጎታል።

የእድሎች አህጉር

አፍሪቃ ለጀርመን ኩባንያዎች ሰፋ ያለ ብዝሃነትን እና ጥገኝነትን በመቀነስ  ረገድ የዕድሎች አህጉር ተደርጋ ትታያለች።  በተለይም የከባቢ አየርን የማይበክል የአረንጓዴ የኃይል ምንጭ፣ የመሠረተ ልማት አውታሮች እና የመረጃ ቴክኖሎጂ «IT» ዘርፍ፤  ለመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ማራኪ ናቸው። ነገር ግን የኮቪድ ወረርሽኝ እና በአህጉሪቱ አዳዲስ ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላ በብዙ የአፍሪቃ ሀገራት ኢኮኖሚው ክፉኛ ተጎድቷል፣ የፋይናንስ በጀቶች ተለዋዋጭ ሆነዋል።

ለንግድ ዝግጁ የሆነችዉ አፍሪቃ

በጀርመን ከሚታየዉ የኤኮኖሚ ተግዳሮት በፊት እና ሃገሪቷ የዩክሬንን ጦርነት መዘዝ ከመጋፈጧ በፊት፣ አገሪቱ ለብዙ አሥርተ ዓመታት በቻይና፣ በምዕራብ አውሮጳ እና በአሜሪካ ኢንቨስት በማድረግ ጥሩ ተጠቃሽ ነበረች።

"በርካታ የጀርመን ኩባንያዎች በአፍሪቃ ውስጥ ያሉት ገበያዎች ውስብስብ እና ለብዙዎች የማይታወቁ ናቸው ብለዉ ለሚታቀድ የንግድ ስራ ስኬት አይሆንም የሚል አመለካከት ነበራቸው።"

ኬንያ ኢንስትራክተር ጂያንግ ሊፒንግ - እና ሆራስ ኦዊቲ በሞምባሳምስል Wang Guansen/Xinhua/IMAGO

የአፍሪቃ መንግስታት ክፍት እና ለንግድ ስራ ዝግጁ መሆናቸውን በአፍሪቃ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም (APRI) ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ባልደረባ ሰርዋህ ፕሪምፔ ገልፀዋል። አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገራት በጣም ንቁ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ እና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን በተለያዩ የማበረታቻ መረሃ-ግብሮች ባለሀብቶችን ለማምጣት እየሰሩ ነው ሲሉም አክለዋል።

"የጀርመን የተለያዩ የንግድ ኩባንያዎች ከእነዚህ የመንግስት ተቋማት ጋር መነጋገር አለባቸው"  የመንግስት ባንኮችን ጨምሮ የጀርመን የባንክ ዘርፍ ለአፍሪቃ ኢንቨስትመንቶች አዲስ የገንዘብ ድጋፍ ሞዴሎችን በአስቸኳይ ማዘጋጀት አለባቸው "አሁን ያለው አካሄድ ውጤታማ አይደለም." ሲሉ የአፍሪቃ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት (APRI) ከፍተኛ የምጣኔኃብት ባለሞያ ሰርዋህ ፕሪምፔ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል። 

አዜብ ታደሰ / ማርቲና ሺኮቭስኪ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW