1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ውህደት 30ኛ ዓመት

ማክሰኞ፣ መስከረም 26 2013

እንደ ዓመታዊው ዘገባ የቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች ኤኮኖሚ ከተቀረው ጀርመን በአንድ ሦስተኛ ዝቅ ያለ ነው።የምሥራቅ ጀርመኖች ገቢም በአስር በመቶ ያንሳል።የሥራ አጡም ብዛት ከፍተኛ ነው። ከውህደቱ በኋላ ብዙዎች ምሥራቅ ጀርመንን እየለቀቁ ወደ ምዕራቡ መሰደዳቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የዘለቀ አንዱ ችግር ነው።

EinheitsEXPO 30. Jahrestag Deutsche Einheit
ምስል picture-alliance/dpa/A. Gora

የጀርመን ውህደት 30ኛ ዓመት

This browser does not support the audio element.

አራት አሥርት ዓመታት ከዘለቀው የቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ነበር በጎርጎሮሳዊው ጥቅምት 3፣1990 ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን በይፋ የተዋሃዱት።ከውህደቱ አስቀድሞ በምሥራቅ ጀርመን እየበረታ በሄደው ተቃውሞ ጫና ሰበብ በጎርጎሮሳዊው ህዳር 9፣1989 ጀርመንን ለሁለት የከፈለው የበርሊን ግንብ ፈረሰ፣ድንበሩም ተከፈተ።ግንቡ ከፈረሰ ዓመት ሊሆነው ጥቂት ሲቀር የዛሬ 30 ዓመት የሁለቱ ጀርመኖች ውህደት እውን ሆነ። ከውህደቱ በኋላ ብዙ እድገቶች ተመዝግበዋል። ሆኖም አሁንም በምሥራቅ እና ምዕራብ ጀርመን መካከል የኤኮኖሚን ጨምሮ ሌሎችም ልዩነቶች አለመስተካከላቸው ውህደቱ በተከበረና በታሰበ ቁጥር ተደጋግሞ የሚነሳ ጉዳይ ነው ። ከውህደቱ በኋላ ብዙዎች ምሥራቅ ጀርመንን እየለቀቁ ወደ ምዕራቡ ክፍል መሰደዳቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የዘለቀ አንዱ ችግር ነው።ምንም እንኳን በምሥራቅ ጀርመን የጡረታ ደሞዝ አነስተኛ የነበረ ቢሆንም አሁን ከምዕራቡ ጋር እየተቀራረበ ነው እንደ ዶቼቬለዋ ማርሴል ፍፊዩርስተናው። ማርኮ ቫንደርቪትዝ የዛሬ 30 ዓመት ከምዕራብ ጀርመን ጋር የተዋሃዱት የምሥራቅ ጀርመን ፌደራል ግዛቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ናቸው።ከጎርጎሮሳዊው 1990 ወዲህ ሁለቱ ጀርመኖች በተለያዩ መንገዶች በጣም ተመሳሳይ ሆነዋል ይላሉ።በርሳቸው አስተያየት ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን ከሚለያዩዋቸው ይልቅ ብዙ የሚጋሩዋቸው ጉዳዮች አሉ።
«ጀርመን ከ1990 አንስቶ በተለያዩ መንገዶች ይበልጥ ተመሳስላለች።ይህንንም በተለያዩ መንገዶች ማወቅ ይቻላል።በቤተሰባዊ ሕይወት በመዝናኛ እንቅስቃሴዎችና በስራ ሰዓት መለካት ይቻላል። ማንም የትም ቢመለከት፣ከየትኛውም ቦታ አሃዛዊ መረጃዎችን ቢሰበስብ ከሚለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ይበዛሉ።»  
ታዲያ የአሁኒቷ ጀርመን ማርኮ ቫንደርቪትዝ  እንደገለጿት ትሆን?በመስከረም ወር ይፋ የተደረገው የጀርመን ውህደትን የተመለከተው ዓመታዊ ዘገባ ግን ቫንደርቪትዝ ካሉት የተለየ ነው።ሁሌም የሚነሳው የኤኮኖሚ አቅም አንዱ ልዩነት ነው።እንደ ዓመታዊው ዘገባ የቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች ኤኮኖሚ ከተቀረው ጀርመን በአንድ ሦስተኛ ዝቅ ያለ ነው።የምሥራቅ ጀርመኖች ገቢም በአስር በመቶ ያንሳል።የሥራ አጡም ብዛት ከፍተኛ ነው።የጀርመን መራሂተ መንግሥት የአንጌላ ሜርክል ወግ አጥባቂ ፓርቲ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ሕብረት በጀርመንኛው ምህጻር CDU አባል ቫንደርቪትዝ እነዚህን ጉድለቶች መኖራቸውን ያምናሉ።ሆኖም ምሥራቅ ጀርመኖች የተለያዩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ በማዋል መቀየር ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው።ለጀርመን የግራዎቹ ፓርቲ ቅርበት ያለው«ሮዛ ሉክሰምበርግ»የተባለው ተቋም ሃላፊ ዳግማር ኤንክልማንም የኤኮኖሚው ልዩነት እንዳለ ያምናሉ። ልዩነቱ እንዲስተካከልም  ብዙ ሥራዎች በፍጥነት መሠራት አለባቸው እንደ ኤንክልማን ።ችግሩን መወገድ የሚችልበት መንገድም መፈለግ አለበት ይላሉ። 
«እዚህ የተለያዩ መዋቅሮች አሉ።እነዚህም ለምሥራቁ ክፍል መጻኤ እድል የተለየ ልማት ትርጉም ያላቸው ናቸው።እንደሚመስለኝ አሁን የፌደራል ግዛቶች በልማትና የኤኮኖሚ መዋቅር ፖሊሲያቸው ይህን ችግር መፍታት የሚችሉበትን መንገድ ማሰብ ይገባል።»
አቶ ስዩም ሙሉጌታ ከጀርመን ውህደት 10 ዓመት በፊት አንስቶ እስካሁን ለ40 ዓመታት የበርሊን ነዋሪ ናቸው።የበርሊን ግንብ ሲፈርስ አይተዋል። ሁለቱ ጀርመኖችም ሲዋሃዱም እዚያው ነበሩ። የሁለቱ ጀርመኖች ውህደት ብዙ ለውጦችን አምጥቷል። በአቶ ስዩም ሕይወትም ላይ  ተጽእኖ ማሳደሩ አልቀረም።ከህውህደቱ በፊት ጀርመን የሚኖሩ የውጭ ዜጎች የሚያቋቁሟቸው ማህበራትን የሚያደራጅና የሚደግፍ ድርጅት ውስጥ ነበር የሚሰሩት።ከውህደቱ በኋላ መስሪያ ቤታቸው አያስፈልግም በመባሉ በሌላ ስራ ለመሰማራት ተገደዱ።በወቅቱ ርሳቸው በነበሩበት በበርሊን የታየውን ለውጥ እንዲህ ያስታውሳሉ።አቶ ስዩም ውህደቱ ያስከተላቸውን አሉታዊ ጎኖችም አንስተዋል።አቶ ስዩም አዎንታዊውም አሉታዊም ጎኖች ካሉት ከጀርመን ውህደት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌላው ዓለም ብዙ ሊማር ይችላል ብለዋል።

ምስል Tino Schöning/dpa/picture-alliance
ምስል Jana Kubasch/Lübecker Nachrichten

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW