1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ውህደት 32ተኛ ዓመት አከባበር በአዲስ አበባ

ዓርብ፣ ጥቅምት 4 2015

የጀርመን መንግሥት የኢትዮጵያን መንግሥት በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ ለመደገፍ የግንኙነት ማሻሻያ ማድረጉን የገለፁት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አዎር ይህንን የአንድነታችንን በዓል ስናከብር የጀርመን ሕዝብ ለዴሞክራሲ እና ለነፃነት ያደረገውን ተጋድሎ እናስባለን ብለዋል።

የጀርመን አምባሳደር ሽቴፋን አወር በአዲስ አበባ  የጀርመን ኤምባሲ
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ሽቴፋን አወር በአዲስ አበባ የጀርመን ኤምባሲ በተከበረው የጀርመን ውህደት 32ተኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ ንግግር ሲያደርጉምስል Solomon Muchie/DW

የጀርመን ውህደት

This browser does not support the audio element.


ጀርመን ዳግም የተዋሀደበት 32ተኛ ዓመት ትናንት ምሽት በአዲስ አበባ የጀርመን ኤምባሲ ግቢ ውስጥ ተከብሯል። ጀርመንን ለሁለት ከፍሎ የቆየው በ1961 የተሰራው ግንብ ከፈረሰ በኋላ ጀርመን አንድ ስትሆን በአውሮጳ ቀዳሚውን ባለ ጠንካራ ኢኮኖሚ አገር መፍጠር አስችሏል።በየዓመቱ ኤምባሲው ያከብረው የነበረው ይህ እለት በኮሮና ተኅዋሲ መዛመት ምክንያት ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ ነበር። የጀርመን ውህደት መታሰቢያ ቀን  ሲከበር የጀርመን ሕዝብ ለዴሞክራሲ እና ለነፃነት ያደረገውን ተጋድሎ እናስባለን ሲሉ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አዎር ተናግረዋል። ጀርመን የምንጊዜም የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገር መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደሩ የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት በሰላም እንዲፈታ መንግሥታቸው ፍላጎት እንዳለውም በዚሁ ወቅት ተናግረዋል። 
የጀርመን ውህደት 32 ኛ ዓመት በዓል በአዲስ አበባው የጀርመን ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በድምቀት ሲከበር የኢትዮጵያ የትምህርት የሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና በርካታ የተለያዩ ሀገራት የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦች ተገኝተዋል።በበዓሉ አከባበር ስነ ስርዓት ላይ፣ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የተሻገረው የኢትዮጵያ እና የጀርመን መልካም ግንኙነት ከ2019  ጀምሮ ደግሞ የጀርመን መንግሥት የኢትዮጵያን መንግሥት በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ ለመደገፍ የግንኙነት ማሻሻያ ማድረጉን የገለፁት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አዎር ይህንን የአንድነታችንን በዓል ስናከብር የጀርመን ሕዝብ ለዴሞክራሲ እና ለነፃነት ያደረገውን ተጋድሎ እናስባለን ብለዋል።
በዚህ ጊዜ በሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ ቀጥሏል፣ በሌሎች አካባቢዎችም ብዙዎች በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች እየተጎዱ ይገኛሉ፣ አፍሪካ በኢ- ሕገ መንግሥታዊ አኳኋን የመንግሥት ግልበጣዎች እየተደረጉባት ፣ አውሮፓም በራሺያ እና በዩክሬን ጦርነት ችግር ውስጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።
"ግንኙነታችን በጽኑ መሠረት ላይ ያለ ነው። ለዚህም ነው አሁን ላይ ያለው ችግር እያለ ይህ የሆነው፣ በግንኙነታችን ላይም መተማምን ያለን።
ጀርመን ሙሉ በሙሉ እንደገና ግንኙነቷን ለማጠናከር ዝግጁ ናት። ይህ ይሳካ ዘንድ ግን በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ሰፍኖ እና ሰብአዊ ችግሮች ተቀርፈው ማየት፣ ሁሉንም የሚያካትት ተዓማኒ እና ግልጽ ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የተሳተፉ አጥፊዎች ተጠያቂ ሆነው ማየት እንሻለን። 
የአፍሪካ ሕብረትን ከምንጊዜውም በላይ አሁን እንፈልገዋለን። በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት እና ችግር እንዲቀረፍ የሚረዳውን ብሔራዊ ውይይት እና ቀድሞ የተጀመረውን የሰላም ሂደት የመምራት ኃላፊነት ስላለው" የጀርመን ዳግም ዉሕደት ቀን
ጀርመን በአውሮጳ የኢትዮጵያ ቡና ዋነኛ መዳረሻ መሆኗን፣ በኢትዮጵያ ማህበረ ኢኮኖሚ መስተጋብር ውስጥ ከፍተኛ እመርታ ያለው የሁለትዮሽ ድጋፎችን በትምህርት፣ በግብርና ፣ በሰብዓዊ ድጋፍ እና በመልካም አስተዳደር ዘርፍ እያደረገች መሆኑን በሥነ ስርዓቱ ላይ የተናገሩት የኢትዮጵያ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ ፣ጀርመንና የአውሮጳ ሕብረት የኢትዮጵያን የተወሳሰበ የፖለቲካ እና የፀጥታ ነባራዊ ሁኔታ በወጉ ይገነዘባሉ ብለን እናምናለን ብለዋል። እጅግ በጣም ጥሩ ሲሉ የገለፁት የሁለቱ ሀገሮች የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፀና እምነት እንዳላቸውም ገልፀዋል።
"ባለፉት ዓመታት ከውስጥም ከውጭም ሀገሬ ኢትዮጵያን በርካታ ችግሮች ገጥመዋታል። በነዚህ ጊዚያት ሁሉ ምንም እንኳን የምንገነዘባቸው ጥያቃዎች ቢኖሩም ጀርመን አልተለየንም ነበር።አስምሬ መናገር የምፈልገው የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን ያለውን ግጭት ዘላቂ ሰላም በሚያመጣ እና የግዛት አንድነቷን በጠበቀ ሁኔታ ለማቆም የሚያስችሉ ማናቸውንም እርምጃዎች ለመውሰድ ዝግጁ ነው። በዚህ ረገድ ሁሉንም ወዳጆቻችን በተለይም ጀርመንና የአውሮጳ ሕብረት በጠቅላላ የአፍሪካ ሕብረት በያዘው የሰላም ጥረት ሂደት ላይ ገንቢ ሚና እንዲያበረክቱ ጥሪየን አቀርባለሁ።"
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የጀርመንን ውህደት በሥእል ለተሳታፊዎች መልእክቱን ሲያስተላልፍ የነበረው ሰዓሊ እያዩ ገነት፣ "እንዲህ ያለው የአንድነት ታሪክ ሊነገር የሚገባው ነው" ይላል። የተባበረች ጀርመንን የመመስረት ዓላማን ለማሳካትና ሀገራቸውን የአውሮጳ ታላቅ ኃይል ለማድረግ የተንቀሳቀሱት ኦቶ ፎን ቢስማርክ ውጥናቸው ተሳክቶላቸው በ1989 ሁለት ሆነው የነበሩትን የጀርመን ሀገሮች ነጣጥሎ የቆየው ግንብ ሲፈርስ እውን ሆኗል።

በአዲስ አበባ የጀርመን ኤምባሲ በተከበረው የጀርመን ውህደት 32 ተኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ የተገኙ እንግዶች ምስል Solomon Muchie/DW

ሰሎሞን ሙጬ 

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW