1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ዓለም ዓቀፍ ሚና

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 29 2009

«ጀርመናውያን በክብ ጠረጴዛ መነጋገር ሁሉንም ችግር ያስወግዳል ብለው አያምኑም ፤እንደዚሁ ሁሉ መተኮስም መፍትሄ ነው ብለውም አያስቡም» የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር

Frankreich Merkel und Putin
ምስል Getty Images/S. Gallup

የጀርመን ዓለም አቀፍ ሚና

This browser does not support the audio element.

በአሁኑ ጊዜ የጀርመን ዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ ተሳትፎ እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል ። ሆኖም ሀገሪቱ በዓለም ዓቀፉ መድረክ እንዲኖራት የምትፈልገውን ሚና አሁንም ገና ቅርፅ እያስያዘች ይመስላል ። ለመሆኑ አሁን የጀርመን ሚና በዓለም አቀፍ መድረክ እንዴት ይገመገማል ?
ጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር  ከጥቂት ወራት በፊት ባቀረቡት ጽሁፍ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት  ሀገራቸው በዓለም አቀፍ መድረክ የምትጫወተው ሚና በእጅጉ እንደተለወጠ አስታውቀው ነበር። ሽታይንማየር  በአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩረው «ፎሪይን አፌይርስ» በተባለው የአሜሪካን መጽሄት ላይ እንዳስነበቡት ሁለቱ ጀርመኖች ከተዋሃዱበት ከጎርጎሮሳዊው 1990 ወዲህ ኤኮኖሚዋ ትልቅ እምርታ ያሳየው ጀርመን በውጭ ፖሊሲዋ ረገድ እምብዛም ጎላ ብሎ የሚታይ ቦታ አልነበራትም ብለዋል ።ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ መለወጡን ነው ሽታይንማየር በጽሁፋቸው የገለጹት ።ከጎርጎሮሳዊው 1998 አንስቶ በአራት የጀርመን ካቢኔዎች ውስጥ ያገለገሉት ሽታይንማየር  ጀርመን አሁን በዓለም መድረክ አዲስ ሚና እየተጫወተች ነው ይላሉ። በዓለም ዙሪያ የሚካሄዱ በርካታ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በሚካሄዱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ውስጥም ሀገራቸው የበኩሏን አስተዋአጽኦ እንደምታደርግ በዚህ ረገድ  በተደጋጋሚ ከኢራን ዩክሬን ኮሎምብያ ኢራን ሊቢያ ማሊ ሶሪያ እና በባልካን ሀገራት የተፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት ሀገሪቱ ያካሄደቻቸው የተካሄዱት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን ያስረዳሉ ። ከአውሮጳ በኤኮኖሚ እድገት ግንባር ቀደሙን ስፍራ የምትይዘው ጀርመን ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወታደራዊ ተሳትፎዋ ዝቅተኛ መሆን ያስወቅሳታል ። የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርን የህግ ባለሞያ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ጀርመን ከፍተኛ ተፅእኖ ማድረግ የምትችል ሀገር በመሆንዋ ይስማማሉ ። እርሳቸውም የወታደራዊ ተሳትፎዋን ድክመት ሳያነሱ አላለፉም ። ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ጦርነት የሚለውን ቃል ከመዝገበ ቃላቷ የሰረዘች ያህል የምትቆጠር የነበረችው ጀርመን ከጦርነቱ በኋላ ዓለም አቀፍ ኃይሎች በተሳተፉባቸው ሁለት ጦርነቶች ብቻ ነው የተካፈለችው ። በኮሶቮ እና በአፍጋኒስታን ። በኢራቁ ጦርነት ግን አልተካፈለችም ።ሀገሪቱ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ተሳትፎዋ ተገድቦ የቆየበት ምክንያት ምን ይሆን ? ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ይህ ተለውጧል ። የጀርመን ዓለም አቀፍ ተሳትፎ በሂደት እያደገ ነው ።በወታደራዊ ተሳትፎዋ መቀነስ የምትተቸው ጀርመን አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟን አጉልተው የሚያወጡ እና የሚያስመሰግኗት ተግባራት አሉ ።  ከምትመሰገንባቸው መካከል ባለፈው ዓመት በርካታ ስደተኞችን ማስገባትዋ እና ከ8 ዓመታት በፊት የጋራው ገንዘብ ዩሮ የገጠመውን ቀውስ ለመፍታት የሄደችበት መንገድ ይገኙበታል ። የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሁለት ሳምንት በፊት ፓሪስን ለመጎብኘት አቅደው ነበር ። ይሁን እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ስለ ሩስያ በሰጡት አስተያየት ምክንያት ፑቲን ጉዞአቸውን ሰርዘው በርሊን መጡ ። ሞስኮ ክሪምያ የተባለችውን የዩክሬን ግዛት ገንጥላ ከወሰደች ከጎርጎሮሳዊው 2014 በኋላ ፑቲን በርሊን ሲመጡ የዛሬ 15 ቀኑ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው ። ባለፉት ጊዜያት የዩክሬንን እና የሩስያን ውዝግብ ለመፍታት ጀርመን እና ፈረንሳይ ባለፉት ጊዜያት በጋራ ዓለም አቀፍ ጥረቶች ሲያካሂዱ ቆይተዋል ። ይሁን እና ውዝግቡን ለመፍታት ሚኒስክ ላይ ዩክሬን እና ሩስያ የተስማሙበት የተኩስ አቁም ስምምነት የትም አልደረሰም ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጉዳዩን እንደገና ለማንቀሳቀስ  ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ከሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ ጋር በርሊን ውስጥ ያካሄዱት ውይይት ጀርመን በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትጫወተው ሚና አንድ ምሳሌ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ። ጀርመን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሳትፎዋን ለማሳደግ የተገደደችባቸው ምክንያቶች አሉ ይላሉ ዶክተር ለማ ይናገራሉ ። በጎርጎሮሳዊው 1946 የተመድ ሲመሠረት ተሸናፊዋ ጀርመን ምንም ሚና አልነበራትም የሚሉት ዶክተር ለማ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ተሸናፊ በመሆንዋ ሀገሪቱ በፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ውስጥ ቦታ እንዳልተሰጣት ያስረዳሉ ። ጦርነቱ ትቶት ያለፈው ጠባሳ ጀርመኖች ለተወሰኑ ዓመታት አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዳይሄዱ ማድረጉንም ያስታውሳሉ ። አሁን ኤኮኖሚዋ የተጠናከርዋና በአውሮፓ ህብረትም ሆነ በዓለም መድረክ ተሰሚነትዋ እየጎላ የሄደው ጀርመን ፣የፀጥታ ጥበቃ ምክርቤት አባልነትን ለማግኘት ግፊት ማድረግ ከጀመረች ዓመታት አልፈዋል ። ግን ይህ ምኞትዋ እስካሁን አልተሳካላትም ።ምክንያቱ ምን ይሆን ? 
የጀርመን ዓለም ዓቀፍ ሚና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ፣ሽምግልና ንግግር አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ ማስፈራራት ጭምር ሊሆን ይችላል ።« ጀርመናውያን በክብ ጠረጴዛ መነጋገር ሁሉንም ችግር ያስወግዳል ብለው አያምኑም እንደዚሁ ሁሉ መተኮስም መፍትሄ ነው ብለው አያስቡም» ሲሉ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በ ፎሪን አፌይርስ በተባለው መፅሄት ላይ ባወጡት ጽሁፍ አስነብበዋል ።በሌላ አባባል «የጀርመን የውጭ ፖሊሲ ሚዛኑን የጠበቀ አሠራር መከተል ነው »ብለዋል 

ምስል picture-alliance/robertharding/A. Cavalli
ምስል picture alliance/AA/A. al Ahmed

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW