1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የአፍሪቃ የፖለቲካ መርህና ተግዳሮቶቹ 

ማክሰኞ፣ ጥር 25 2013

ቻይና እና ቱርክ በአፍሪቃ ብዙ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሱ ነው።ሁለቱ ሃገራት በአፍሪቃ የባቡር ሃዲድና መንገድ በመሳሰሉ የመሠረተ ልማቶች ግንባታዎች በስፋት ተሰማርተዋል።የጥሬ ሃብት ምንጮችንም እየተቆጣጠሩ ነው። ይህም ጀርመንና ሌሎች የአውሮጳ ሃገራት በአፍሪቃ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ሊያስገድዳቸው ይችላል ተብሎ ይታመናል።

Deutschland Berlin | Konferenz Compact with Africa | Angela Merkel, Bundeskanzlerin | Gruppenbild
ምስል Reuters/F. Bensch

የጀርመን የአፍሪቃ የፖለቲካ መርህና ተግዳሮቶቹ 

This browser does not support the audio element.

ጀርመን፣ያለፈው ጎርጎሮሳዊው 2020 ለአፍሪቃ ልዩ ትኩረት የምትሰጥበት ዓመት እንደሚሆን ዓመቱ ሳይገባ አስታውቃ ነበር። ይሁንና በገርጎሮሳዊው 2019 ዓም መጨረሻ ተከስቶ ዓለምን በአጭር ጊዜ ውስጥ ያደረሰው የኮሮና ወረርሽኝ እቅዱን አሰናክሎታል። የጀርመን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ለጎሮጎሮሳዊው 2020 ዓም ካቀዷቸው ዐበይት ጉዳዮች  አንዱ የአፍሪቃ መንግሥታትና የጀርመን የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የሚያካሂዱት ጉባኤ ነበር።ይሁንና ከጎርጎሮሳዊው 2017 ዓም አንስቶ በየዓመቱ በርሊን ሲካሄድ የቆየው ይህ ጉባኤ ዓለማችንን ባዳረሰው በኮሮና ወረርሽኝ ሰበብ እንደታቀደው አልተካሄደም። ኮሮና በጉባኤው ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍሪቃ ለመወረትና ወረታቸውን ለማስፋፋት በተዘጋጁ የጀርመን ኩባንያዎች ላይም ተጽእኖ አሳድሯል። ብሬመን ጀርመን  በሚገኘው ያኮብስ በተባለው ዩኒቨርስቲ የኤኮኖሚ ፕሮፌሰር ቲሎ ሃላሶቪች ያካሄዱት ጥናት የዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ሃላሶቪች ከጠየቋቸው በአፍሪቃ መዋዕለ ንዋያቸውን ካፈሰሱ አንድ መቶ ጀርመናውያን ባለሀብቶች 75 በመቶው በ2020 በክፍለ ዓለሙ ሥራቸውን የማስፋፋት እቅድ ነበራቸው። ሆኖም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ከመካከላቸው 13 በመቶው ብቻ ናቸው ይህን ሊያሳኩ የቻሉት። ሃላሶቪች ወረርሽኙ ሲያበቃ በአፍሪቃ የመወረቱ ፍላጎት ሊጨምር ይችላል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።ለዚህም ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚገባ አሳስበዋል።
«እኔ በመሠረቱ የምመኘው በአነስተኛ ደረጃ አስተዳደራዊ ጫናዎችን በመቀነስ ፈጣን ድጋፍ ለማድረግ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ ነው። ፍላጎቱ ይኖራል። ወረርሽኙ ሲቆም ስጋቱም ከፍተኛ መሆኑ አይቀርም። ለጀማሪ ወራቾች ብዙ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል።መሰረተ ልማቶችን መገንባት እና ግንኙነቶችን እንደገና ማጠናከርም ያሻል።»
ጀርመን በአፍሪቃ ተግባራዊ ልታደርግ የምትሞክረው የፖለቲካ መርህ ላይ ኮሮና ባለፈው 2020 ተጽእኖ ማድረጉ ባይካድም መርሁ ግን አስቀድሞም ቢሆን ድክመቶች እንዳሉበት ከበርሊን ጀርመን የኤኮኖሚ እድገት መምህር ተመራማሪና አማካሪ እንዲሁም የተለያዩ መጻሕፍት ደራሲ ዶክተር ፈቃዱ በቀለ ያስረዳሉ። በዶክተር ፈቃዱ አስተያየት ጀርመንም ሆነች ሌሎች የአውሮጳ ሃገራት  በጥቅሉ በጽሁፍ የሚያስቀምጡት እና ተግባራዊ የሚያደርጉት መለያየቱ  ነው አንዱ ችግር። ይህን ወደ ኃላ ላይ እንመለስበታለን። ከዚያ በፊት የጀርመን የአፍሪቃ የፖለቲካ መርህ ምንድነው? ይዘቱን የሚያስረዳውን የዶክተር ፈቃዱ በቀለን ማብራራያ እናስቀድም።ዶክተር ፈቃዱ እንደሚሉት የፖለቲካ መርሁ ስድስት መሪ ሃሳቦችን አካቷል 
የጀርመን መንግሥት በአፍሪቃ የግል መዋዕለ-ንዋይን ለማበረታታት በሚል በቅርብ ዓመታት የተለያዩ መርሐ-ግብሮች ነድፏ ሲንቀሳቀስ ነበር።ከመካከላቸው ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ የተባለው በአፍሪቃ የግል መዋዕለ-ንዋይን ማበረታቻ እንዲሁም «የአፍሪቃ ማርሻል ፕላን» መርሃ ግብሮች ይገኙበታል።ይሁንና በመርሃ ግብሮቹ ላይ የጀርመን ኩባንያዎች ፍላጎት በማነሱ በአፍሪቃ ተጨባጭ ለውጥ ሊመጣ አለመቻሉን ተችዎች ይናገራሉ። በዶክተር ፈቃዱ አስተያየት ለጀርመን የአፍሪቃ የፖለቲካ መርህ ስኬት የጀርመን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃ መንግሥታት ፍላጎትም በግልጽ መታወቁ ወሳኝ ነው።ጀርመን በአፍሪቃ ተግባራዊ ማድረግ የምትፈልገው የፖለቲካ መርህ እንደታሰበው አልተራመደም።
የዚህ አንዱ ምክንያቱ  ዶክተር ፈቃዱ እንደሚሉት፣ የአፍሪቃ መንግሥታት ፖሊሲ ድክመት ነው።የአፍሪቃ መንግሥታት ለህዝባቸው ተቆርቋሪ አለመሆናቸውም  መርሁ ውጤታማ እንዳይሆን ካደረጉት ውስጥ ይደመራል።
በአሁኑ ጊዜ በዓለም በቴክኖሎጂና በውጭ ንግድ ከፍተኛ ቦታ እየያዘች የመጣችው ቻይና እንዲሁም ቱርክ በአፍሪቃ ብዙ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሱ ነው።ሁለቱ ሃገራት በአፍሪቃ የባቡር ሃዲድና መንገድ በመሳሰሉ የመሠረተ ልማቶች ግንባታዎች በስፋት ተሰማርተዋል።የጥሬ ሃብት ምንጮችንም እየተቆጣጠሩ ነው።የሁለቱ ሃገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ ጠልቆ መግባት ምናልባት፣ ጀርመንና ሌሎች የአውሮጳ ሃገራት በአፍሪቃ ደካማ ሆኖ የቆየውን የመዋዕለ ንዋይ ፍሰታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ሊያስገድዳቸው ይችላል ተብሎ ይታመናል እንደ ዶክተር ፈቃዱ። ይህ እንዲሳካም የአፍሪቃ መንግሥታት ለመዋዕለ ንዋይ እንቅስቃሴ አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር አለባቸው። 

ምስል Reuters
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Euler
ምስል Getty Images/AFP/J. Macdougall

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW