1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የምዕራብ አፍሪቃ ጉብኝት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 13 2016

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በያዝነው ሳምንት ሁለት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራትን ጎብኝተዋል። ቅድሚያ ወደ ሴኔጋል ከዚያም ወደ ቡርኪናፋሶ ያመሩት አናሌና ቤርቦክ ዋነኛ ትኩረታቸው የጸጥታ ትብብር ጉዳይ ነበር።

አናሌነ ቤርቦክ በሴኔጋል
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌነ ቤርቦክ በሴኔጋል ጉብኝታቸው ንግግር ሲያደርጉምስል Britta Pedersen/dpa/picture alliance

የጀርመን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የምዕራብ አፍሪቃ ጉብኝት

This browser does not support the audio element.

 

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በያዝነው ሳምንት ሁለት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራትን ጎብኝተዋል። በቅድሚያ ሴኔጋል ደርሰው ወደ ኮትዴቩዋር የተሻገሩት አናሌና ቤርቦክ፤ በሳህል አካባቢ ሃገራት የታጣቂዎች ጥቃት እና ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትን ተከትሎ የሚታየው የጸጥታ ስጋት ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳቸው ነበር። በኮትዴቩዋር ቆይታቸውም ከማዕከላዊ ሳህል አካባቢተነስቶ የተስፋፋውን የሽብር እንቅስቃሴ ለመግታት ስልጠና የሚሰጥበትን የጸረ ሽብር ስልጠና አካዳሚን ጎብኝተዋል። ከዋና ከተማ አቢጃን 35 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ በሚገኘው በዚህ አካዳሚ የፈረንሳይ እና የአሜሪካ ባለሙያዎች የሚሳተፉ ሲሆን ጀርመን ለስልጠናው 2,5 ሚሊየን ዩሮ ገደማ ድንጋፍ አድርጋለች።

ሳህል አካባቢ የጸጥታ ስጋት

የታጣቂዎች ጥቃት እና ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በጠናበት አካባቢ የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የዚህ ወቅት ጉብኝት በዋናነት በጸጥታ ጉዳይ ያለውን ትብብር ማዕከል ያደረገ ነው።

በተጠቀሰው አካባቢ ጥቂት በማይባሉት ሃገራት ተከታታይ መፈንቅለ መንግሥታት ከተካሄዱ በኋላ ከምዕራቡ ዓለም መንግሥታት ጋር ግንኙነታቸው የቀጠለው ሁለት ሃገራት ሴኔጋል እና ኮትዴቩዋር ብቻ ናቸው። የማሊ፤ ቡርኪ ናፋሶ እና ኒዠር ጦር ኃይሎች ሥልጣን ይዘዋል። ሁሉም ይህን ለማድረጋቸው ያቀረቡት ምክንያት፤ መንግሥታቱ እስላማዊ ሽብርተኝነትን ለመቆጣጠር አልቻሉም የሚል ነው። ሦስቱም የፈረንሳይ እና የሌሎች ሃገራት ወታደሮችን ወደ የመጡበት መልሰዋል። ሆኖም ወታደሮቹ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ውጊያው መባባሱ ነው የሚነገረው።

ወታደራዊ ኃይላቸውን በማስተባበር የቆሙት ሦስቱ ሃገራት ወታደራዊ መሪዎች፤ የውጪ ጣልቃ ገብነት ከመጣ በጋራ ለመከላከል ዝግጁነታቸውንም ገልጸዋል። ቤርቦክ መሪዎቹ ከጥቃት እርምጃ እንዲታቀቡ ጥሪ አስተላልፈዋል። በሂደትም ከምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ትብብር አባልነት የታገዱት ሦስቱ ሃገራት ለቀረበላቸው የሰላም ጥሪ ምላሽ የሚሰጡ ከሆነ ወደ ኤኮኖሚ ትብብሩ ሊመለሱ እንደሚሉም መጠቆማቸው ተዘግቧል።

ኮትዴቩዋር ከዋና ከተማዋ ወጣ ብሎ የሚገኘው የጸረ ሽብር ማሰልጠኛ አካዳሚምስል Rosalia Romaniec/DW

የጀርመን የጸጥታ ትብብር

በሳህል አካባቢ ያለው የጸጥታ ይዞታ ለሀገራቸው ወሳኝ ነው ያሉት ቤርቦክ፤ ከኮትዴቩዋር ፕሬዝደንት አላሳን ዋታራ ጋር ባደረጉት ውይይት በዚህ ላይ በጥልቀት መነጋገራቸውን፤ እንዲሁም ጀርመን ለአካባቢው ጸጥታ  እንዴት አስተዋጽኦ ልታደርግ እንደምትችል መነጋገራቸውንም አስታውቀዋል።

ጀርመን ኒዠር ውስጥ በመከላከያ ኃይሏ የሚንቀሳቀሰውን የአየር ኃይል ጣቢያ በመጪው ነሐሴ ወር ለመልቀቅ በዝግጅት ላይ ነች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ እንደገለጹት ኒዠር ውስጥ ካለው መንግሥት አስተማማኝ ነገር ባለመኖሩ ሀገራቸው ጀርመን ስታደርገው የነበረው የጸጥታ ድጋፍ አይቀጥልም።

በአንጻሩ ሀገራቸው የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሂደት እያሳዩ ያሉ እንደ ሴኔጋል ባሉ ሃገራት የባለሃብቶችን ቀልብ መሳብ እንደቻሉም አመልክተዋል። ቤርቦክ በዚህ ጉብኝታቸው በርከት ያሉ የጀርመን የንግድ ልዑካንን አስከትለው ነው የተጓዙት። ባለሀብቱ ያለውን የሥራ እና የገበያ ዕድል በመገምገም፤ ለበርካታ የሁለቱ ሃገራት ወጣቶች ዕድል በሚፈጥሩ ዘርፎች ላይ ይሰማራሉ በሚል ተስፋ ተደርጓል። ቀድሞ የፖለቲካ እስረኞች የነበሩት አዲሶቹ የሴኔጋልን መሪዎች ሀገራቸው በእራስዋ የምትወስንና በራሷ የምትተማመን እንድትሆን ይፈልጋሉ። ለዚህም በሴኔጋል ጀርመን መዋዕለ ነዋይ እንድታፈስ ይሻሉ። ጉብኝታቸው ከበጎ አድራጎት ዘመቻ ባሻገር የሀገራቸውን ፍላጎት ያነገበ መሆኑን ያመለከቱት ቤርቦክ፤ በሳህል አካባቢ እያደገ የመጣው የቻይና፤ ሩሲያ እና ቱርክ ተጽዕኖን በማመልከት በመዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ሂደት ሊፈጠር ይችላል ያሉትን ጠቁመዋል።

«እኛ እንደ ዴሞክራሲ ሃገራትና እና አውሮጳ ምንም ሳናደርግ፤ ሌሎች መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሱ ጥገኞችን በመፍጠር፤ ምናልባትም በእኛ እና በጸጥታ ጥቅማችን ላይ በተቃራኒ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል።»

በአሁኑ ጊዜ የምዕራብ አፍሪቃ የባሕር ዳርቻ አካባቢ ባሉ ሃገራት አንጻራዊ መረጋጋት መኖሩን ያመለከቱት ሚኒስትሯ፣ እንደሴኔጋል ባሉ ሃገራት የኤኮኒሚ ማገገሚያው እውን መሆን ካልቻለ ተስፋ መቁረጥን አስከትሎ ወጣቶች በቀላሉ በወንጀለኛ ቡድኖች እጅ እንዲገቡ ሊያደርግ እንደሚችልም አሳስበዋል።

«ወጣቶች የሕይወት አቅጣጫ ከሌላቸው በወንጀለኛ ቡድኖች እና በአሸባሪዎች በቀላሉ ይመለመላሉ ከሀገራቸው ይሰደዳሉ፤ ይህም የአውሮጳን የስደተኞች ቀውስ ያባብሳል።»

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌነ ቤርቦክ ከኮትዴቩዋር ፕሬዝደንት አላሳን ዋታራ ጋሪ ሲወያዩምስል Luc Gnago/REUTERS

አስተማማኝ መረጋጋት

ጀርመን ለምን ከኒዠር ጋር ትብብሯን ማቋረጥ ፈለገች በሚል ቤርቦክ ኮትዴቩዋር ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ወታደራዊው ድጋፍ ብቻ እንጂ የሀገራቸው የልማት ትብብር እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በእርግጥም ከሳህል አካባቢ አንጻር ሲታይ የምዕራብ አፍሪቃ የባሕር ዳርቻ አንጻራዊ መረጋጋት ይታይበታል፤ ይህ ለምን ያህል ጊዜ ይዘልቃል የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ነው። የኮትዴቩዋር ፕሬዝደንት አላሳን ዋታራ ግን አሁን አስተማማኝ ሁኔታ ላይ ነን ነው የሚሉት።

«የለም የለም፤ ኮትዴቩዋር የተረጋጋች ሀገር መሆኗንና እንዲሁም እንደምትዘልቅ አረጋግጥላችኋለሁ። የዚህ መረጋጋት መንስኤው ደግሞ ሀገሪቱ በአግባቡ ስለምትተዳደር ነው እናም እኔ ይህን በትህትና እናገራለሁ። በእነዚህ ዘርፎች ላይ ሁሉ በቂ ትኩረት አድርገናል። በማኅበራዊው ዘርፍ ገንዘብ አፍስሰናል፤ በጣም ግልጽ ምርጫ አካሂደናል። ምርጫውን ለመታዘብ የፈለጉ ሁሉ ይህንኑ እንዲያከናውኑ ተጋብዘዋል። የምንፈራው ነገር የለም። በዚያም ላይ የሪፐብሊኩ ሠራዊትም እንዳለን እገልጻለሁ። በዚህ በኩል የሚያሰጋን ነገር የለም። ቀጣዮቹ ምርጫዎችም ዴሞክራሲያዊ እንደሚሆኑ ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ። ምርጫውን መታዘብ የሚፈልጉትን ሁሉ እንቀበላለን።»

 ሸዋዬ ለገሠ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW