የጀርመን ፕሬዝደንት ይቅርታ ጠየቁ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 21 2016
የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማይር ሐገራቸዉ ታንዚያን ቅኝ ትገዛ በነበረበት ዘመን በታዚኒያ ሕዝብ ላይ ባደረሰችዉ ግፍ «ማፈራቸዉን» አስታወቁ።ጀርመን የዛሬዋን ታንዛኒያን ቅኝ በገዛችበት ዘመን የጀርመን ጦር ለነፃነት ያመፁ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የሐገሬዉን ተወላጆች መገደሉ ተረጋግጧል።ታንዛኒያ እንደምትለዉ በተለይ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ1905 እስከ እስከ 1907 ድረስ ቅኝ ገዢዉ ጦር በከፈተዉ ጥቃት እስከ 300 ሺሕ የሚደርሱ የታንዛኒያ ዜጎች በግፍ ተገድለዋል።ከትናንት ጀምሮ ታንዛኒያን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት ሽታይማየር ዛሬ በርካታ ሰዎች ከተገደሉባቸዉ አካባቢዎች ሶንጌ የተባለዉን አካባቢ ሲጎበኙ የጀርመን ቅኝ ገዢዎች ላደረሱት ግፍ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። ሽታይንማየር የጀርመን ቅኝ ገዢ ጦር የረሸናቸዉን የያኔዉን ባላባት የሶናጌ ምባኖና የ66 ተከታዮቻቸዉን የልጅ-ልጅ ልጆችና ዘመዶች አነጋግረዋልም።በታንዛኒያ የነፃነት ንቅናቄ ስም ማጂ፣ ማጂ ተብሎ የተሰየመዉን ቤተ-መዘክርም ጎብኝተዋል።ጀርመን፣ የተገደሉ ሰዎች ዝርያዎችን ሐዘን እንደምትጋራና ሐዘኑን እንዲወጡ አብራቸዉ እንደምትቆም ፕሬዝደንቱ አረጋግጠዋል።ጀርመን በመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ስትሸነፍ የዛሬዎቹን ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳና ብሩንዲን የሚያስተናብረዉ «የጀርመን የምስራቅ አፍሪቃ« ይባል የነበረዉ የቅኝ ግዛት ዘመንም አብሮ አብቅቷል።
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ