በአማራ ክልል ጃራ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ስጋት
ማክሰኞ፣ መስከረም 13 2018
ከኦሮሚያ ክልል ከአራቱም የወለጋ አካባቢዎች እና ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለደኅንነታቸው በመስጋት ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተፈናቀሉት እነዚህ ወገኖች የመጠለያ ጣቢያቸው አሁን ወታደራዊ ማሰልጠኛ መሆኑ ደኅንነታችንን ስጋት ላይ ጥሎታል ይላሉ።
የጃራ መጠለያ ጣቢያ ነዋሪዎች ስጋት
ያነጋገርናቸው በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሀብሮ ወረዳ ጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙት ወገኖች ለዓመታት በመጠለያ ስፍራ ከነቤተሰባቸው ባስቸጋሪ ሁኔታ ኑሯቸውን እየገፉ ነው። አዛውንት፤ ሴቶች እና ሕጻናትን ይዘው በአፋር እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢ በሚገኘው ጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ሌሎች ችግሮችን ተቋቁመው ከመኖር የተሻለ አማራጭ ማጣታቸውን ይናገራሉ።
ከኦሮሚያ ክልል በተለይም ከአራቱም የወለጋ አካባቢዎች ማለትም ምሥራቅ ወለጋ፤ ምዕራብ ወለጋ እና ሆሮጉዱሩ ወለጋ እንዲሁም ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከዓመታት በፊት በጸጥታ ስጋት ምክንያት ያቀኑትን አካባቢና ቤት ንብረታቸውን እየተው የተፈናቀሉት እነዚህ ወገኖች የተጠለሉበት ስፍራ ወታደራዊ ማሰልጠኛ መሆኑ አሁን ለሌላ ስጋት ዳርጎናል ይላሉ።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በጃራ የተፈናቃይ ወገኖች መጠለያ ባለፈው ዓመት የፌደራል መንግሥት ወታደሮች ለወራት በስልጠና በስፍራው ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ስፍራው ላይ የክልሉ መንግሥት ሚሊሻዎች በእግራቸው ተተክተዋል። በዚህ መሀልም ባለፈው ሳምንት መስከረም ስድስት ቀን 2018 ሌሊቱን የታጠቁ ኃይሎች በማሰልጠኛው ስፍራ ጥቃት ፈጽመው ጉዳት እንደደረሰም ገልጸዋል። ላለፉት ሦስት ዓመታት በዚህ መጠለያ ስፍራ መኖራቸውን የገለጹልን ሌላኛው ተፈናቃይ በበኩላቸው ሁኔታውም ለደኅንነታቸው አስተማማኝ እንዳልሆነ ነው የአይደለም ይላሉ።
የተፈናቃዮቹ የኑሮ ሁኔታ
ወደዚህ መጠለያ ሲገቡ ለስድስት ወራት ብቻ እንደሚቆዩበት ተነግሯቸው እንደነበር ያመለከቱት እኝህ የመጠለያው ነዋሪ የሚያድሩባቸው የሸራ ድንኳኖች ባለፈው ሐምሌ ወር በተከሰተው ኃይለኛ ንፋስ ተገነጣጥለው ለችግር መዳረጋቸውንም ገልጸውልናል። ሁኔታው የተመለከቱ ሁለት ግብረሠናይ ድርጅቶች የተወሰኑትን ድንኳኖች ቢቀይሩላቸውም በሺህዎች የሚቆጠሩትን ወገኖች ማዳረስ እንዳልቻሉም ጠቁመዋል።
ከሁለት ግብረሠናይ ድርጅቶች ሌላ በቋሚነት አማራ መልሶ ማቋቋም ልማት ድርጅት የምግብ እርዳታ እንደሚሰጣቸው የሚናገሩት እነዚህ ወገኖች ከሰብአዊ እርዳታው ችግር በአሁኑ ጊዜ የባሰባቸው የጸጥታ ስጋት መሆኑን ተናግረዋል። ከእርዳታ አቅራቢዎቹ በወር በነፍስ ወከፍ 15 ኪሎ በቆሎ፤ አንድ ኪሎ ተኩል ክክ፤ 0,45 ሊትር ዘይት እንደሚያገኙ የገለጹልን የመጠለያ ጣቢያው ነዋሪዎች ከዚያ ውጪ በቋሚነት የሚያገኙት ሰብአዊ እርዳታ እንደሌለም ተናግረዋል። እነሱ እንደሚሉት በተጠቀሰው ጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ስፍራ ከስምንት ሺህ በላይ ወገኖች ይገኛሉ።
ተፈናቃዮቹ ያነሱትን የደኅንነት ስጋት በተመለከተ ከሚመለከታቸው የአማራ ክልል ባለሥጣናት ማብራሪያ ለማግኘት ደጋግመን ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም።
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ