የጃፓን አፍሪቃ ጉባዔ
ሰኞ፣ ነሐሴ 23 2014
ጃፓን "የበለጠ ጠንካራ" ኢኮኖሚዎችን ለማስፋፋት ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር በቅርበት ትሰራለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሲዳ ተናገሩ። የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን የተናገሩት ትናንት እሁድ በቱኒዝያ በተካሄደ ስምንተኛው የቶኪዮ ዓለምአቀፍ የአፍሪቃ ልማት ጉባዔ ማጠቃለያ ላይ ነዉ። ጃፓን በቀጣዩ ዓመት በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ያላትን ቦታ በመጠቀም አፍሪቃ በዓለሙ መድረክ ቋሚ መቀመጫን እንድታገኝ እንደምትሰራ ገልፀዋል። የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሲዳ ከተናገሩ ከአንድ ቀን በኃላ ሃገራቸዉ ለአፍሪቃ አህጉር የ30 ቢሊዮን ዶላር የህዝብና ለግል ድርጅቶች እንደምትሰጥ ይፋ አድርገዋል። በኮቪድ ህመም ምክንያት በአካል ጉባዔዉ ላይ ያልተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኪሲዳ፤ ከቶኪዮ ቪዲዮ አማካኝነት በቀጥታ ባደረጉት ንግግር ጃፓን "አፍሪቃውያን በሰላምና በደህንነት መኖር የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ትፈልጋለች" ብለዋል። የ55 አፍሪቃ ሃገራት ህብረት ሊቀመንበር የሆኑት የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል አህጉሪቱ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ከኪሲዳ የቀረበዉን ጥሪ ደግፈዋል። "እኛን የሚያደናቅፉና እንዳናድግ የሚከለክሉን ግጭቶች፤ ተልዕኮው በዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነትን ማስፈን በሆነዉ በፀጥታው ምክር ቤት ግምት ውስጥ መግባት አለበት" ሲሉ ማኪ ሳል ተናግረዋል። ያለ ዋስትና ልማት ሊኖር አይችልም ያሉት የአፍሪቃ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ግጭቶችን በመፍታት ረገድ የአፍሪቃ ሰላም አስከባሪዎች የበለጠ ሚና እንዲኖራቸውም ጠይቀዋል። የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪሲዳ ሃገራቸዉ በአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እንደምትሾምም አስታውቀዋል። ጃፓን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጂሃዲስቶች ጥቃት በወደመው በማሊ፣ በኒጄርና በቡርኪና ፋሶ መካከል ባለው በምዕራብ አፍሪቃዉ ሊፕታኮ-ጉርማ ባለ የሦስት ሃገራት ድንበር በወርቅ ማዕድን ኃብት የበለፀገ አካባቢ 8.3 ሚሊዮን ዶላር እንደምትሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪሲዳ አክለዋል ። በሳምንቱ መጨረሻ ቱኒዚያ ላይ በተካሄደዉ በስምንተኛው የቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪቃ ልማት ጉባዔ ላይ ወደ 20 የሚጠጉ የአፍሪቃ የመንግሥትና የመንግሥት ተጠሪዎችን ጨምሮ ከንግድና ከሌሎች ዘርፎች የተዉጣጡ ወደ 5,000 የሚጠጉ አፍሪቃዉያን የተገኙበት ነበር። በጉባዔዉ ላይ ለመገኘት የቱኒዝን የሚያቋርጡ ትላልቅ መንገዶች በተሽከርካሪቾች በመሙላታቸዉ ቅዳሜና እሁድ የትራፊክ መጨናነቅ ተከስቶ እንደነበርም ታዉቋል።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ