1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጅማ ባህላዊ የሙዚቃ ውዝዋዜዎች እና ሸነን ጊቤ

እሑድ፣ የካቲት 27 2014

በጅማ ዛሬ ላይ ከተወሰኑ የውዝዋዜ ዓይነቶች ውጪ በአካባቢው ነዋሪዎች ብዙም አይታወቁም ወይም እየተረሱ መጥተዋል። የሆኖ ሆኖ በጅማ እና አካባቢው በተለይ የባህላዊ ዘፈኖቹን ከአልባሳቱ አዋዶ በመላ ሀገሪቱ ከማስተዋወቅ ባሻገር ለትውልድ በማስተላለፉ ረገድ ኃላፊነቱን የተሸከመው  ‹‹ሸነን ጊቤ››  የባህል ሙዚቃ ቡድን ነው፡፡

Äthiopien | traditionelle Musik
ምስል፦ Merga Tefera/Jimma

ጤና ይስጥልን የዝግጅታችን ተከታታዮች ለዛሬ በጅማ የአፋን ኦሮሞ ባህላዊ ጭፈራዎች እንዲሁም ጭፈራዉን ከአካባቢው አልፎ በክልሉ ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ላይ በሚገኘው የሸነን ጊቤ የባህልሙዚቃ ባንድ እንቅስቃሴን ከአካባቢው የባህላዊ ውዝዋዜ ማስተዋወቅ አንጻር እንቃኛለን ፤ አብራችሁን እንድትሆኑ የአክብሮት ግብዣችን ነው። 
መሸጋገሪያ 
ከበርካታ የጅማ ባህላዊ ጭፈራ እና ውዝዋዜዎች ውስጥ ኦልኦፌ፣ ጐና፣ ገቱሜ፣ ቆማንቀባ፣ ጅጅግሳና ገቱሜ የተሰኙት በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተሩ እና ተወዳጆች ናቸው። ከጉሮሮ በሚወጡ ጎርነን ባሉ ድምጾች የሚታገዙት ውዝዋዜዎቹ በተለያዩ ክብረ በዓላት እና  ባህላዊ ስነስረዓቶች በተለያዩ የዕድሜ ክልል ባሉ ሰዎች ይዘወተራሉ። 
ጅጅግሳ በወጣቶች ወደ ግራና ወደ ቀኝ ዘንበል በማለት ይጨፈራል፡፡ ብዙ ጊዜም ወጣቶች እና አዛውንቶች አብረው ሲጨፍሩ ወጣቶቹ አዛውንቶቹን ለማድከም ይጠቀሙታል፡፡ ጉልበት ስለሚጠይቅም በአዛውንቶች አይዘወተርም፡፡ ጐናም እንደዚሁ ጉልበት የሚጠይቅ ሲሆን፣ ከላይ እስከ ታች በመውረድ ቁጢጥ ብለው የሚጨፍሩት ነው፡፡
ገቱሜ ሙዚቃ 1


 ገቱሜ፣ ኦልኦፌና ቆማንቀባ ብዙም ጉልበት አያስፈልገውም፡፡ ዕድሜአቸው በገፋ ሰዎችም ይዘወተራል፡፡

‹‹ገሩሌ›› የተሰኘው ሙዚቃ ከሌሎቹ በተለየ መልኩ በሰርግ ወቅት በልጃገረዷ ቤተሰቦች ቤት የሚዘፈን የሙዚቃ ዓይነት ነው፡፡ ሴቶች ብቻ የሚጨፍሩበት ሲሆን፣ ገበታ ይዘውና ክብ ሠርተው በዝግታ እየተዟዟሩ ይወዛወዛሉ፡፡ ገሩሌ ልጅቷ የምታገባበት ቦታም ተደርጐ ይወሰዳል፡፡

ገሩሌ ሙሽሪት ልታገባ አንድ ሳምንት ሲቀራት ይዘፈናል፡፡ በዚህም ጊዜ አዶዬ (የአባት ጓደኛ) ቤቷ ስትገባ የሚያስፈልጋትን እንደ ቅቤ፣ እንጀራና ሌሎችም ነገሮች አቅም በፈቀደ አዘጋጅተው ያመጡላታል፡፡ ሳምንቱን ሙሉም ይዘፈናል፡፡ 

በጅማ ዛሬ ላይ ከተወሰኑ የውዝዋዜ ዓይነቶች ውጪ በአካባቢው ነዋሪዎች ብዙም አይታወቁም ወይም እየተረሱ መጥተዋል።፡፡ የጅማ ባህላዊ ሙዚቃ ተከፍቶ ዝብርቅርቅ ያሉና የማይታወቁ የጭፈራ ስልቶችን የሚቀላቅሉ የአካባቢውን ነዋሪዎች ማየትም እየተለመደ መጥቷል፡፡ ባህላዊ አለባበሱ ግን አሁን አሁን ነብስ እየዘራ ስለመምጣቱ በአንዳንድ የሰርግ እና የህዝብ በዓላት ላይ እየታየ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ይበል ያሰኛል። የሆኖ ሆኖ በጅማ እና አካባቢው በተለይ የባህላዊ ዘፈኖቹን ከአልባሳቱ አዋዶ በመላ ሀገሪቱ ከማስተዋወቅ ባሻገር ለትውልድ በማስተላለፉ ረገድ ኃላፊነቱን የተሸከመው  ‹‹ሸነን ጊቤ››  የባህል ሙዚቃ ቡድን ነው፡፡

ሸነን ጊቤ የሚለው  ስያሜ አምስቱ የጅማ ቀደምት ነገሥታት የሚያመለክት ነው፡፡ ጉና፣ ጐማ፣ ጌራ፣ ሊሙና ጅማ በሸነን ጊቤ ይካተታሉ፡፡ እኚህ የአካባቢ ነገሥታት በጅማው ንጉሥ አባ ጂፋር ይተዳደሩ ነበር፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ለመመካከርና ውሳኔ ለማሳለፍ ሲሹም ከጅማ ከተማ 50 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ‹‹ኦሞ ናዳ›› የተባለች ወረዳ ይጓዛሉ፡፡ ጉዳያቸውንም ከአንዲት የዛፍ ጥላ ሥር ተሰይመው ይቋጫሉ፡፡ አካባቢውም ሸነን ጊቤ ተብሎ ይጠራል፡፡

የሙዚቃ ባንዱ ታሪካዊ ስያሜ ይዞ የተነሳ ቢሆንም ባለፉት የሰላሳ ዓመታት ጉዞው በታሰበው ልክ ባህሉን በማሳየቱ ረገድ እንዳሰበው አልተሳካለትም፡፡ ባህላዊ የሙዚቃ ባንዱን በ90ዎቹ አጋማሽ እንደተቀላቀለ የሚናገረው አብዱለጢፍ መሐመድ በወቅቱ ባንዱ የጅማን የባህል ዘፈኖች በካሴት ጭምር እስከማሳተም የደረሰ ጠንካራ እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደነበር ያስታውሳል። በጊዜ ሂደት ግን ነገሮች አልጋ በአልጋ አልሆኑም እንጂ።
አብዱልለጢፍ 
ባንዱን በ90ዎቹ ስትቀላቀል ተወዛዋዥ እንደነበረች የምትናገረው የባንዱ አባል ወይንሸት /////// ደግሞ አሁን በተወዛዋዥ ሰልጣኝነት እና በድምጻዊነት እያገለገለች እንደምትገኝ ትናገራለች። የሙዚቃ ባንዱ በሚፈለገው ደረጃ ወደ ፊት እንዳይራመድ ካደረጉት ነገሮች የአካባቢው አስተዳደሮች ለባንዱ የሚሰጡት ድጋፍ መቀዛቀዙ እንደሆነ  ትገልጻለች ።

ምስል፦ Merga Tefera/Jimma

የሸነን ጊቤ የሙዚቃ ባንድ ምንም እንኳ በየጅማ ኦሮሞ ባህላዊ ሙዚቃዎችን ማስተዋወቅን አላማ በማድረግ ቢቋቋምም በጅማ እና አካባቢው በስፋት የሚኖሩት የሌሎች ብሄሮች እና ብሔረሰቦች ሙዚቃዎችንም የሚጫወቱ ድምጻዊያን እና ተወዛዋዦች አሉት ። ከዚህም በተጨማሪ በግላቸው ወጥተው የሙዚቃ አልበሞችን ማሳተም የቻሉ እንደነ ናፊሳ አብዱልሃኪም የመሳሰሉ ድምጻዊያን የተገሩበት ባንድም ነበር።

ብቸኛ ካሴታችንን ካሴት ያሳተምነው  በ1994 ዓ.ም. ነበር የሚሉት ደግሞ የባንዱ አስተባባሪ አቶ መርጋ ተፈራ ናቸው ፡፡  እንደ እርሳቸው ከሆነ ባንዱ የተወሰኑ ሥራዎችን አሰባስበው ለማሳተም ከተዘጋጁ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም  የሚደረገላቸው ድጋፍ እምብዛም በመሆኑ የተፈለገው ደረጃ ላይ ሊደርሱ አለመቻላቸውን ይገልጻሉ። 
የጅማው ሸነን ጊቤ ባንድ ታላቅ ህልም ሰንቆ የአካባቢውን ሙዚቃ እና ባህል ለተቀረው ሕብረተሰብ ለማስተዋወቅ እኩሌታ መንገድላይ ቆሟል። ተጠናክሮ ገፍቶ ካሰበበት መድረስ አልያም ህልሙ መክኖ ያሰበውንም ሳያሳካ ከመንገድ መቅረት ። ይህ እንዳይሆን ትኩረት እንሻለን ይላሉ የባህል ሙዚቃ ባንዱ አባላት። 
እንግዲህ አድማጮቻችን ለዛሬ ብለን የሸነን ጊቤ የሙዚቃ ባንድ ከጅማ የባህላዊ ሙዚቃ እና ውዝዋዜ ዕድገት አንጻር የቃኘንበትን የመዝናኛ ዝግጅታችን በዚሁ ያበቃል ፤ በዝግጅቱ ዘና እንዳላችሁበት ተስፋ እናደርጋለን ፤ ሳምንት በሌላ መሰናዶ እንጠብቃችኋለን፤ ከዝግጅቱ ጋር ታምራት ዲንሳ ነኝ ጤና ይስጥልኝ ። 
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW