1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታሪካዊው የጅማ ንጉስ አባጅፋር

ሐሙስ፣ ጥር 23 2016

የጅማ ሙዚየም አዲስ አበባ ከሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም በመቀጠል ትልቁ የታሪክ መሰነጃ ይባልለታል፡፡ መሃል ጅማ “ፈረንጅ-አራዳ” ተብሎ በሚጠራው ሰፈር አከባቢ የሚገኘው ይህ ሙዚየም በተለይም የጅማ ወርቃማ ዘመን በተባለው ወቅት ጅማን ሲያስተዳድሩ የቆዩት የዳግማዊ አባጅፋር አስተዳደራዊ ታሪክ ላይ ነፍስ የሚዘሩ ቅርሶችን አጠናክሮ ይዟል፡፡

የጅማ ሙዚየም
የጅማ ሙዚየምምስል Seyoum Getu/DW

ጅማ ሙዚየም በጉልህ የሚዘክረው የጅማን ታላቅ ሰው ንጉስ አባጅፋር ዳግማዊን ነው

This browser does not support the audio element.

ታሪካዊው የጅማ ንጉስ አባጅፋር፡ ከሙዚየም እስከ መካነ መቃብር


ኢትዮጵያ ውስጥ በ1972 ዓ.ም. የተመሰረተው የጅማ ሙዚየም አዲስ አበባ አምስት ኪሎ አከባቢ ከሚገኘው ከአንጋፋው ብሔራዊ ሙዚየም በመቀጠል ትልቁ የታሪክ መሰነጃ ይባልለታል፡፡ መሃል ጅማ “ፈረንጅ-አራዳ” ተብሎ በሚጠራው ሰፈር አከባቢ የሚገኘው ይህ ሙዚየም በተለይም የጅማ ወርቃማ ዘመን በተባለው ወቅት ጅማን ሲያስተዳድሩ የቆዩት የዳግማዊ አባጅፋር አስተዳደራዊ ታሪክ ላይ ነፍስ የሚዘሩ ቅርሶችን አጠናክሮ ይዟል፡፡ 


የጊቤ ነገስታት
ቀድሞ የጅማ ታሪክ ከአምስቱ የጊቤ ነገስታት ጋር በእጅጉ ይቆራኛል፡፡ አምስቱ የጊቤ ነገስታት የሚባሉትም በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጠቃላይ ጅማን በገዳ ስርዓት ያስተዳድሩ የነበሩ ይባልላቸዋል፡፡ ከ1800 ጀምሮ እስካ 1835 በጎርጎሳውያን ዘመን ቀመር ሊሙ ኢናርያ፣ ጉማ፣ ጎማ፣ ጅማ እና ጌራ የተሰኙ አምስቱ የጊቤ ነገስታት የራሳቸው መዋቅር እና ነገስታት ይዘው አጠቃላይ ጅማን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡ በ1830 የጎርጎሳውያን ኣመት ጅማን የመሰረቱ አባጅፋር ቀዳማዊ የዛሬዋን ጅማ መስርተው ጅማ አባጅፋር የሚል ስያሜ አሰጥተውአታል፡፡ በ1852 ዓ.ም. የተወለዱት በወል ስማቸው አባጅፋር በሚል የሚታወቁትና የጅማን ወርቃማ ዘመን መርተዋል የሚባልላቸው አባጅፋር ዳግማዊ 1926 ዓ.ም. በ74 ዓመታቸው ከዚህ ኣለም እስካለፉበት እለት ድረስ ከእድሜያቸው 55 ዓመታትን ያሳለፉት በመሪነት ነው፡፡ ገና የ15 ዓመት ታዳጊ እያሉ ወደ ስልጣን የመጡት አባጅፋር ዳግማዊ በንግስና ዘመናቸው በጅማ ብርቱ ታሪክ የጻፉ በሚል ይሞገሳሉም፡፡ 
ነጂብ ራያ በጅማ ከተማ የቱሪዝም ኮሚሽን ኃላፊ ናቸው፡፡ “አባጅፋር ስምንተኛው የጅማ ንጉስ ናቸው፡፡ ከሳቸው በኋላ የመጨረሻ የጅማ ንጉስ ሆነው ለስምንት ወራት ብቻ ያስተዳደሩት ሱልጣን አባጁራ አባዱላ” መሆናቸውን በማስረዳትም ጅማን ለሰፊው ጊዜ ስላስተዳደሩት አባጅፋር ዳግማዊ ታሪካዊነት ያስረዳሉ፡፡

የጅማ ነገስታት መካነ መቃብር ምስል Seyoum Getu/DW


የጅማ ሙዚየም ምስረታ ታሪካዊነት
ታዲያ በጅማ ከተማ 1972 ዓ.ም. የተቋቋመውና እለት በእለት በበርካታ ጎብኚዎች የሚጎበኘው የጅማ ሙዚየም በጉልህ የሚዘክረው እኝህን የጅማን ታላቅ ሰው ንጉስ አባጅፋር ዳግማዊን ነው፡፡ “ሙዚያሙ የዛሬ 150 ዓመታት ገደማ የነበሩ የጅማን ስልጣኔ በብዛት ይይዛል፡፡ የእንጨት ስራዎች፣ የአልባሳት እና ብረት ስራዎች በስፋት በዚህ ሙዚየም ይገኛሉ፡፡ በተለይም በአባጅፋር ዘመኑ 19ኛው መቶ ክፍለዘመን እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ተሻሽለው እንድስፋፉ የተደረገበት ስለሆነው በዚህ ሙዚየም ጎልቶ የሚታየው በዚሁ ዘመን የተሰሩና የተቀመጡ ቅርሶች ናቸው፡፡”
በዚህ በጅማ ሙዚየም አባጅፋርን አጉልተው ከሚዘክረው የዘመነ ንግስናቸው ስልጣኔ በተጨማሪ በአከባቢው ለዘመናት የነበሩ የኦሮሞ እና ከፋ ህዝቦች የዘመናት ስልጣኔ እና የምጠቀሙባቸው ቁሶች ተከማችተውበታልም፡፡ በተለይም ንጉስ አባጅፋር ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቁሳቁሶች ከወንበር እስከ አልጋቸው እና ሌሎችም ቁሶች በዚህ ሙዚያም ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቷል፡፡ የአባጅፋር ልዩ ልዩ ስጦታዎች እና ታሪካዊ መጽሃፍትም በዚህ ሙዚያም በብዛት ይገኛሉ፡፡ “ሙዚየሙ ዋነኛ ተግባሩ ቅርሶችን ማዳን፣ መሰነድና ታሪክን ለትውልድ ማስተላለፍ ነው፡፡ በተሌም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከቅርስ አያያዝ ጋር ተያይዞ በቅርቡ ትኩረት ተሰጥቶት ቅርሶችን የማዳን ስራ ላይ ተጠምዶ ይገኛል፡፡ የአባ ጅፋር ቤተመንግስት እድሳትን ከዚሁ ጋር አያይዞ ማንሳት ይቻላል፡፡ ሙዚየሙን ከአገር ውስጥ እና ከውጪ በርካታ ጎብኚዎች መጥተው የጎበኙታል፡፡” የበርካታ ጎብኚዎች ቀልብ የሚስቡ ታሪካዊ ቅርሶችን በውስጡ ያቀፈው የጅማ ሙዚም ባንድ ወቅት “ሙርቴ ዳንስ ቤት” በሚል የሚታወቅና ሆቴልም የነበረ ነው፡፡ ከዚያም በደርግ ዘመን ይህ ስፍራ የወተት ኃብት ልማት ቢሮም ሆኖ አገልግሎ ያውቃል፡፡ የጅማው ቱሪዝም ኮሚሽን ኃላፊው አቶ ነጂብ ከዚሁ በመነሳት አሁን ላይ በእድሳት ላይ ያለው የአባጅፋር ቤተመንግስት ታድሶ ስጠናቀቅ ቅርሶቹን ወደዚያ የማዘዋወር ውጥን መኖሩን አስረድተውናል፡፡ “አሁን ባለው ሁኔታ ቅርሶቹና የተቀመጡበት ቤት የሚገኛኙ አይደሉም፡፡ አባጅፋር ቤተመንግስት እድሳቱ ስጠናቀቅ ቅርሶቹ ህይወት እንዲዘሩም በመታመኑ ወደዚያው የምናዘዋውር ይሆናል፡፡” እስከዚያው ግን ቅርሶቹ  በቂ ጥበቃ እንዲደረግላቸው፤ ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንም ጋር በመነጋገር እንዳስፈላጊነቱ ቅርሶቹ ታሪካዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ እንድታከሙ ይሰራልም ነው የሚሉት፡፡ 

የጅማ ሙዚየምምስል Seyoum Getu/DW


የጅማ ሙዚየም ክፍሎችና ይዘቶቹ

የሆነ ሆኖ ግን የጅማው ሙዚየም የተለያዩ ክፍሎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው እና መግቢው ላይ የሚገን ክፍል ታሪካዊ የእንጨት ስራ ቁሳቆሶች በብዛት የሚገኙበት ነው፡፡ ቀጥሎም የባህል አልባሳት ክፍል ተብሎ የሚታወቀው የሙዚየሙ ክፍል የአባጅፋር የጦር ሜዳ አልባሳትን ጨምሮ በርካታ ታሪካዊ አልባሳት የተሰነዱበት ነው፡፡ “አባጅፋር በሼሪዓው መርህ መሰረት አራት ምስቶችን አግብተዋል፡፡ ሁለቱ ማለትም የመጀመሪያዋ እና አራተኛ ምስቶቻቸው ስሞቱባቸው ከከፋ እና ወልቂጤ ጉራጌ ተክተው ባጠቃላይ ስድስት ምስቶችን አግብተዋል ማለት ነው፡፡ ታዲያ በዚህ በታሪካዊ አልባሳት ክፍል የእነዚያ ባለቤቶቻው አልባሳት እና ለእሳቸውም ከተለያዩ አገራት በስጦታ የተላኩትን ጨምሮ የጦር አልባሳቶቻው ጭምር የሚገኙበት ነው ይህ ክፍል” ብለዋል፡፡
ሌላው በዚህ የሙዚየሙ ክፍል የሚገኘው አስገራሚው ነገር የዛንዚባር አልጋ ነው፡፡ ይህ የዛንዚባር አልጋ የዛሬ 110 ዓመት ገደማ በዛንዝባሩ የመጨረሻው ንጉስ ሱልጣን በርገሽ-ቢንሳ ለአባጅፋር በስጦታ ተልኮ ከዚያ ድረስ በሸክም ጅማ ብደርስም ሰውነታቸው እጅጉን ግዙፍ ለሆነው ለአባጅፋር ግን ለመኝታ አልበቃም፡፡ “አልጋው ከአባጅፋር የሰውነት ግዝፈት እኩል ባለመሆኑ ለመኝታ አልበቃቸውምና ለመቀመጫ ብቻ ይጠቀሙበት ነበር” ብለዋል አቶ ነጂብ፡፡ ይሕ የዛንዝባሩ አልጋ አንድ ሜትር ተኩል ብቻ ስረዝም እሳቸው ግን 2ሜትር ከ10 ሴንቲሜትር እንደሚረዝሙ ነው ታሪካቸው የሚያስረዳው፡፡ አባጅፋር በዘመናቸው ስጠቀሙባቸው የነበሩ የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልጌ ቁሳቁሶችም በሙዚየሙ ሌላኛው ክፍል ተሰንደዋል፡፡ “በዘመናቸው ስጠቀሙባቸው የነበሩ መጠጫዎች፣ ጫማዎች፣ ባህላዊ የቶር መሳሪያዎች እና ንጉስ ሚኒሊክን ጨምሮ ከአገር ውጪም ከተለያዩ አገራት የመጡላቸው የስጦታ እቃዎች በዚህ ይገኛሉ” ብለዋልም፡፡ አባጅፋር በጣሊያኑ የመጀመሪያ ዙር ወረራ ወቅት ለአደዋው ዘመቻ 500 ሰራዊት እና 60 ሺህ ማርትሬዛ ድጋፍ አድርገው ከማዋጣታቸው በተጨማሪ፤ ንጉሴ ነግስት አጼ ሚኒሊክ ዳግማዊወደ አደዋ ስዘምቱ አዲስ አበባ ተቀምጠው በአደራ አገር የማስተዳደር እምነት ተሰጥቶአቸውም እንደነበር ይነገራል፡፡ ታዲያ ይህን እና መሰል የጦር ታሪኮችንም የሚዘክሩ ቅርሶች በዚህ ሙዚየም ሌላኛው ክፍል ተከማችተው ይገኛሉ፡፡ የጅማ ቱሪዝም ኮሚሽን ኃላፊው አቶ ነጂብ ራያ እንደሚሉትም የንጉስ አባጅፋርን ገድል የሚዘክሩ የጦር መሳሪያዎች እና ልዩ ልዩ ስጦታዎች በዚህ በቅርስነት ተይዘው ይገኛሉ፡፡ “ጣሊያን ስሸነፍ በጅማ ላይ የተማረኩ በወቅቱ ዘመናዊ የነበሩ የጦር መሳሪያዎች በዚህ ይገኛሉ፡፡ አጼ ኃይለስላሴ ወደ ጅማ ስመጡ የተዘጋጀላቸው ውድ የክብር ዙፋንን ጨምሮ በርካታ የነገስታት ስጦታዎችም በዚሁ ይገኛሉ” ነው ያሉት፡፡ የፎቶ ክምችቶች፣ የብርሃና ጽሁፎች እና ደብዳቤዎች በብዛት በምገኙበት ክፍልም ከውጪ በወቅቱ ጅማን በስፋት ስጎበኙ የነበሩ ነጮች ታሪክን የሚያስረዱ እና ከንጉስ ሚኒሊክ ጋር የተጻጻፉአቸው የወዳጅነት ደብዳቤዎች በስፋት እንዳሉም ተነግሯል፡፡ የእስልምና እና ክርስትና ንዋዬ ቅድሳት እና መገልገያዎችም በዚህ ሙዚየም በስፋት ተቀምጠዋል፡፡ 
የንጉስ አባጅፋር ቤተመንግስት እድሳት

አቶ ነጂብ ራያ፤ የጅማ ቱሪዝም ኮሚሽን ኃላፊ ምስል Seyoum Getu/DW


ከዚህ ባሻገር ንጉስ አባጅፋር ታዋቂ ድፕሎማት እንደመሆናቸው ከተለያዩ አገራትም ነግስታትም ጭምር እንደ ሉዓላዊ ግዛት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያደርጉ እንደነበር ይገለጻል፡፡ ያም ሆኖ ግን ከአገር ውስጥም ከንጉሴ ነግስቱ ጋር ያላቸው ቁርኝነት በሰላማዊ እና መርህ ላይ የተመሰረተ ይባልለታል፡፡ አቶ ነጂብንም ስለዚሁ ጥያቄ አቀረብንላቸው፡፡ እሳቸውም ስመልሱ “ጅማ በተለያ አቅጣጫዎች ለሚሄዱ የንግድ መዳረሻዎች ማዕከል መሆኗ እና ከንጉስ ምኒሊክ ጋር ከመጀመሪያ በሰላማዊ መንገድ አብሮ መስራታቸው የሉዓላዊ ግዛት እውቅናን ስላሰጣቸው ከተለያዩ አገራት ጋር ግንኙነት የሚያደርጉት ከንጉሱ እውቅና ውጪ በነጻነት ነው” ብለዋል፡፡ በጅማ ታሪክ አዋቂ እና ነጋሪ በሚል የሚታወቁት አብዱልከሪም አባገሮም ስለጅማው ንጉስ አባጅፋር ታላቅነት ሲያስረዱ “እውቅ ዲፕሎማት” ይሏቸዋል፡፡ “አባጅፋር ብልህ እና አስተዋይ በመሆናቸው በሰላም አይደራደሩም፡፡ ከአጼ ሚኒሊክ ጋርም ባደረጉት ብልሃት የተሞላ ስምምነት የራሱ መንግስት ለው ሉዓላዊ ግዛት ሆነው ቆይተዋል” ብለዋል፡፡ ታዲያ እኚህን ታሪካዊ መሪ አጉልቶ የሚዘክረው የጅማ ሙዚየምን በዓመት በሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች እንደሚጎበኙት የሚዚየሙ አስተዳደር መረጃ ያሳያል፡፡ 
ሌላው በጅማ በጉልህ የሚታወቀውና የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስበው ታሪካዊ ቅርስ የአባጅፋር ቤተመንግስት ነው፡፡ ይህ ከጅማ ከተማ ወጣ ብሎ በዳር የሚገነው ታሪካዊ ቤተመንግስት አሁን ላይ በእድሳት ላይ በመሆኑ ለጉብኝት ዝግ ነው፡፡ የጅማው ታሪክ አዋቁ አብዱልከሪም መሰል የቅርሶች ጥገና ጥንቃቄ የታከለበት መሆን እንደሚገባው ይመክራሉ፡፡ 
“ቅርስ እድሳት እንደነበረ መልሶ ጥገና እንጂ መልኩን ቀይሮ ዘመናዊ ማድረግን አይጠይቅም፡፡ በዚሁ መሰረት ያም እድሳቱ ስጠናቀቅ ሌላው ትልቅ መስዕብ ተደርጎ ልወሰድ የሚችል ነው” ብለዋልም፡፡ 
የመስጊዳ አፉርታማ እና የእስልምና መነሻ በጅማ
ጅማለመጀመሪያ ጊዜ 40 የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ተሰባስበው ሶላት የፈጸሙነት ስፍራ መስጊዳ አፉርተማ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ታሪካዊ የሃይማኖት ስፍራ በስድስተኛው የጅማ ንጉስ አባቦቃ የተመሰረተ ብሆንም በኋላ ላይ አባጅፋር ከህንድ በመጡ ሙያተኞች መስጊዱን አንጸው የሚታወቅ ስፍራ አድርገውታል፡፡ 
ከዚሁ መስጊድ አቅራቢያ ላይ የሚገኘው የእስልምና መነሻ በጅማ ተብሎ የሚጠቀስ ቁባ ሼህ አብዱለሃኪም የታሪክ ቦታም የጎብኚዎች እና አጥኚዎች ትኩረት የሚስብ ነው፡፡ በዚህ ቦታ ከጎንደር ወልቃት አከባቢ የመጡቱ ሼህክ አብዱላሃኪም በአከባቢው የእስልምና አስተምዕሮን ለማስፋፋት ማእከላቸው ያደረጉት እና በኋላም አስከሬናቸው ብክብር ያረፈበት ታሪካዊ ስፍራ መሆኑንም የጅማ ቱሪዝም ኮሚሽን ኃላፊው ነጂም ራያ ይገልጻሉ፡፡ “ሼህ አብዱልሃኪም እስልምናን በጅማ ዙሪያ ከማስፋፋትም አልፈው የመጀመሪያውን ንጉስ አባጅፋር እስልምና እንዲቀበሉ ያደረጉ ናቸው፡፡ በዚህ ቦታ አርፈው ሃይማኖታቸው ትምህርትን ያስፋፉበት፤ በኋላም አስከሬናቸው ያረፈበት በመሆኑ አሁን ላይ የቱሪስት እና አትኚዎችንም ቀልብ የሚስብ ስፍራ ነው” ብለዋል፡፡
በዚሁ እጅግ በቀረበ ስፍራ ላይ ደግሞ የጅማ ነገስታት እና ቤተሰቦቻቸው የቀብር ስፍራ ይገኛል፡፡ ንጉስ አባጅፋር ዳግማዊን ጨምሮ በርካታ ቤተሰቦቻቸውም አስከረናቸው አርፎ የሚገኘው በዚሁ ታሪካዊ ስፍራ ነው፡፡ “ለአብነት በዚህ የሚገኘው የንጉስ አባጅፋር መካነ መቃብር ነው፡፡ እንደምትመለከቱትም እሳቸው እጅግ ግዙፍ እንደነበሩ በዚህ ረጅም ስፍራ ላይ ባረፈው መካነ መቃብራቸውም ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ከንጉሳውያኑ በተጨማሪም በዚያ ዘመን የነበሩ ዑላማዎችም የዘላቂ ማረፊያ ስፍራው እዚሁ ነበር” ብለዋል።

 

ስዩም ጌቱ 

አዜብ ታደሰ 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW